በትግራይ ክልል ውስጥ “በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ምክንያት ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ” አንድ የመንግሥት ባለስልጣን መናገራቸውን ከእርዳታ ሠራተኞች ጋር ከተደረገ ስብሰባ ላይ ሾልኮ የወጣ ማስታወሻ ላይ የሰፈረ ጽሁፍ አመለከተ።

በመንግሥት የሚመራው የትግራይ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል በክልሉ የተካሄደውን ግጭት ተከትሎ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በተመለከተ ጥናት ያካሄደ ነው።

የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ በትግራይ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ መጠናቀቁ መገለጹ ይታወሳል።

ነገር ግን አልፎ አልፎ ውጊያ እንደሚካሄድ የተነገረ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በክልሉ ያለውን የሰብአዊ ሁኔታ “የከፋ” ሲል ገልጾታል።

ጨምሮም “ምግብ አለመኖር ወይም በገበያዎች ላይ ያለው አቅርቦት ውስን መሆን እየባሰ የሚሄድ የምግብ እጥረት አደጋን እየፈጠረ መሆኑን ሪፖርቶች እያመለከቱ ነው” ብሏል።

በተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ላይ እንደተጠቀሰውና የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል እንደሚለው በትግራይ ክልል 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል።

ታኅሣስ 30/2013 ዓ.ም በትግራይ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል አማካይነት በተካሄደው ስብሰባ ላይ በአንድ ተሳታፊ አማካይነት የተነሱ ነጥቦች የሰፈሩበትና ሾልኮ የወጣው ማስታወሻ እንደሚያሳየው፤ የማዕከላዊ ትግራይ ክፍል የጊዜያዊ አስተዳደሪ አንድ ባለሥልጣን እንዳለው “በስፍራው ያለው ሁኔታ በጣም የከፋ ነው” ብሏል።

“ምግብና ምግብ ያልሆኑ ነገሮች ወይም ሌሎች ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ተዘርፈዋል ወይም ወድመዋል። ጨምሮም አስቸኳይ እርዳታ ካልቀረበ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ሊሞቱ ይችላሉ።”

ጥር 01/2013 ዓ.ም በተካሄደ ስብሰባ ላይ ሌላ ባለሥልጣን የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎትን በተመለከተ ተናገረ ተብሎ በማስታወሻው ላይ እንደሰፈረው “የተለያዩ ቦታዎችን ለመጎብኘት በተጓዝንበት ጊዜ አብረውን የነበሩ አጃቢዎቻችንን ብስኩት ይጠይቋቸው ነበር” ብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው አሁን ድረስ ወደ ተወሰኑ የትግራይ አካባቢዎች ለመግባት ውስንነት ቢኖርም የተወሰነ የእርዳታ ድጋፍ ግን እየገባ ነው።

አንዲት ልጅ ያዘለች እናት

የስልክና የኢንትርኔት አገልግሎቶች በአብዛኛው የትግራይ ክፍል የተቋረጡ በመሆናቸው የሚወጡ ሪፖርቶችን ትክክለኝነት ለማረጋገጥ አዳጋች አድርጎታል።

አርብ ዕለት ለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ ላይ የአገሪቱ ባለሥልጣናት እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ለመርዳት እንደሚፈልጉ ገልጿል።

“የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰብአዊ እርዳታና የልማት አጋራሮች ጋር በመተባበር በችግር ላይ ላሉ ሰዎች የሚቀርበው እርዳታ ደኅንነቱ ተጠብቆ በውጤታማና በተገቢው ሁኔታ እንዲደርስ ለማድረግ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኛ ነው” ብሏል።

የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል በሚገኘው ሠራዊቱ ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ ነበር ወታደራዊ ዘመቻ የከፈተው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ሠራዊታቸው በክልሉ ሕግና ሥርዓትን ለማስከበርና “ወንጀለኛውን ቡድን” ለሕግ ለማቅረብ የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ እንደሆነ ገልጸዋል።

የፌደራሉ ሠራዊት የክልሉን ዋና ከተማ ከተቆጣጠረ በኋላ ውጊያውን እንደሚቀጥሉ ያሳወቁትን የህወሓት አመራሮችን ለመያዝ አሰሳ እያካሄደ ይገኛል። እስካሁንም በርካቶች መያዛቸውንና መገደላቸው የአገሪቱ ሠራዊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

BBC aMHARIC

Leave a Reply