አስቴር ኤልያስ

ስፍራው ሞቃታማ ቢሆንም ቅጥር ጊቢው ግን በቡና ችግኞችና በተለያዩ የፍራፍሬ ዛፎች በመሙላቱ ለአይን አርንጓዴነቱ ደምቆ፤ ለአፍንጫ ደግሞ መልካም መዓዛው ዘልቆ ስለሚመጣ ለጎብኚው ማየትም መማግም ግዴታ ሳይሆን በውዴታ የሚያጣጥመው ነገር ነው። ወዲህ ለቡና ተክሉ የተስተካከለ ውሃ ይደርሰው ዘንድ አዲስ የሆነና የውሃው ልክ በኮምፒውተር የሚታዘዝበት ቴክኖሎጂ ያለበት አንድ ክፍል ይታያል፤ ወዲያ ደግሞ ወደ 750 ሜትር ኪዩብ ውሃ የሚይዝ የውሃው ሪዘርቫይር ይስተዋላል ፤ ቦታው በምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ ልዩ ስሙ ደበቃ እርሻ ልማት ነው።

Image may contain: 1 person, sitting

የቀርጫንሼ እርሻዎች አስተባባሪ ስራ አስኪያጅ አቶ ደጀኔ ዳባ እንደሚሉት፤ በቀርንጫንሼ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ቀደም ሲል ጥራቱን የጠበቀ ቡና ወደ ውጭ አገር በመላክ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ በግንባር ቀደምትነት እየሰራ ነው። ከንግዱ በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወደዚህ ጎን ለጎን በቡና እርሻ ልማት ተሰማርቷል። ድርጅቱ፣ በዓለማችን ላይ ዘመናዊ የሆነ በቡና ማምረት ቴክኖሎጂ ጫፍ ከደረሱ እንደብራዚል ካሉት አገራት ባልተናነሰ ዘመናዊ ቴክሎጂን ወይም ዲሪፕ እሪጌሽንን በመጠቀም ወደቡና ልማት እርሻ የገባ ነው።

የቡና እርሻው የሚገኘው በምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ ልዩ ስሙ ደበቃ እርሻ ልማት ሲሆን፣ያረፈው ደግሞ በ72 ሄክታር መሬት ላይ ነው። በዚህም ላይ 110 ሺህ የቡና ችግኞችን በመተክል ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም በአንድ ሄክታር ላይ ዘመናዊ የቡና ማፍያ የችግኝ ጣቢያ ወይም ዲጂታል ስፕሪንግ ክለር እሪጌሽ በመጠቀም 600 ሺህ ችግኞችን በማፍላት ለአካባቢው ህብረተሰብም ጭምር ለማደል ወደ ስራ መግባታቸውን ይናገራሉ። ቀደም ሲል በአገራችን ያለው አስተሳሰብ ቡናን ያለጥላ ዛፍ ማልማት አይቻልም የሚል ኋላ ቀር አስተሳሰብ ሲሆን፣ ይህን አስተሳሰብ በአዲስ አስተሳሰብ ለመቀየር እየሰራን ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

በድርጅቱ አግሮኖሚስት ሆነው የሚሰሩት የሆርቲካልቸር ባለሙያው አቶ ጉተማ ጎቤ በበኩላቸው፤ በድሪፕ እሪጌሽን (ጠብታ መስኖ) በአንድ አይነት መልኩ ውሃ ለቡናው እንዴት ሆኖ ይሰራጫል የሚለውን እንደሚከታተሉ ይናገራሉ። ውሃው ለችግኙ ሲደርሰው ለእያዳንዱ ቡና እኩል የሆነ የውሃ መጠን ነው በሜትር ኪዩብ የተለቀቀው ውሃ ወደ ቡናው ሲሄድ የሚደርሰው በሚሊ ሊትር ተቀይሮ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ይህ ቴክኖሎጂ የነበረውን ተልምዷዊ አሰራር ያለዛፍ ቡና መብቀል አይችልም የሚል አስተሳሰብን የሰበረ ነው። ቀደም ሲል ዛፍ ያስፈልግ የነበረው ብዙ ውሃ ስለማይጠጣ የዛፍ ጥላው ያለውን ውሃ እርጥበቱን ጠብቆ እንዲሄድ ስለሚያርገው ነው ይላሉ።

አጠቃላይ የቀርጫንሼ ካምፓኒ ስራ አስፈጻሚ አቶ እስራኤል ደገፋ፣ ካምፓኒው የሚሰራው አጠቃላይ የአገራችን ኢኮኖሚ በሚፈልግበት በግብርናና ማኑፋክቸሪንግ ላይ መሆኑን ይገልጻሉ። በግብርናው ላይ ወደ 26 ሺህ የስራ እድሎችን በመፍጠር እንዲሁም ከ56 ሺህ አርሶ አደሮች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር የሚሰራ ድርጅት እንደሆነም ያመለክታሉ።

አቶ እስራኤል እንደሚሉት፤ ላለፉት አራት አምስት ዓመታት ትልቁን የአገሪቱን የቡና ኤክስፖርት ከሁለት አኃዝ በላይ ድርሻ በመውሰድ የሚልከው ይኸው የቀርጫንሼ ኩባንያ ነው። በየትኛውም የኢትዮጵያ ቡና አብቃይ ክልሎችም ሆነ ወረዳዎች ይገኛል። አጠቃላይ ወደ 57 ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ደግሞ ወደ አምስት እርሻዎችን በቡናው ሴክተር ላይ ማኔጅ ያደርጋል።

ጉብኝት የተደረገበት የደበቃ እርሻ ጣቢያ፣ ኩባንያው ካሉት እርሻዎች ሁሉ አነስተኛው ነው ያሉት አቶ እስራኤል፣ ነገር ግን እንዴት አድርገን ግብርናን ከተለምዶ አሰራራችን መቀየር አለብን ሲሉ በማሰብ በቡናው ፋርም ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ አገሮችን ተሞክሮ ከእነእስራኤልና ብራዚል መውሰድ ላይ መሆናቸውን ያመለክታሉ። የወሰዱትም ቴክኖሎጂ ድሪፕ ኢሪጌሽን ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት በዓለም ላይ የመጨረሻው የሚባለው በግብርናው ዘርፍ የተገኘና ውጤታማ የሆነ የመስኖ ሲስተም ነው ይላሉ። ከዚህ አንጻር በደበቃ ያለው የተሻለው ቴክኖሎጂ  እንደሚያሰኘው ያስረዳሉ።

አርሶአደሩ በተለምዶ በሄክታር ቡና የሚያገኘው ከስድስት ኩንታል የዘለለ አይደለም የሚሉት አቶ እስራኤል፣ እኛ በዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቅመን ግን በሄክታር እስከ 35 ኩንታል ማሳካት ችለናል ብለዋል። ይህ ሙከራ ደግሞ የመጀመሪያው ሲሆን፣ የሚጠበቀው በሄክታር እስከ 65 ኩንታል ድረስ ነው ብለን እየሰራን ነው ሲሉ ተናግረዋል። ያንን ማሳካት ከቻልን የአገራችንን የውጭ ምንዛሬ ማሳደግ እንዲሁም የአርሶ አደሮችን ገቢ ከፍ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።

የእኛ ትልቁ እቅዳችን የራሳችን ማሳ ላይ ትልቁን ምርት ማምረት ላይ ብቻ አይደለም። በአቅራቢያው የሚገኙ የአርሶ አደሮችንም ማሳዎች ወደእኛ ቴክኖሎጂ በመቀየር እነርሱም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መሰረት ማደላደልና በፋይናንስም ለመደጎም ሲሆን፣ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ዲዛይን አድርገን ጨርሰናል ይላሉ።

በዕለቱ ቀርጫንሼ ትሬዲግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ኤክስፖርት ስታንዳርድ የቡና ላቦራቶሪን የመረቁት የግብርና ግብአትና ግብይት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ እና የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ሲሆኑ፣ ሚኒስትር ዴኤታዋ በዕለቱ እንደተናገሩት፤ የድርጅቱን የቡና ማዘጋጃ መጋዘንና የቡና መቅመሻ ላቦራቶሪ እንዲሁም እርሻዎቹን ጎብኝተናል። ከዚህ ደርጅት ባለቤት ጋር አርሶ አደሮችም አብረው ነው ያሉት። ለምርት መሻሻል ደግሞ ዋናው አርሶ አደሮቻችን ከባህላዊ የቡና አመራረት ዘዴ በመጠኑም ቢሆን በመቀየር የቡናን ምርታማነት ሊቀየሩ የሚችሉ አሰራሮችን ተግባራ እያደረጉ ነው ያሉት።

ቡሌ ሆራ ላይ እንደማየውና ሞዴል አርሶአደሮችም እንዳረጋገጡልን በምርትም፣በአቅርቦትም ሆነ በገበያ ትስሰርም የተሻለ እድል ያለበት አካባቢ መሆኑን ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ እዚህ የሚሰሩ ባለሀብቶች የአርሶአደሩንም ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ስለመሆናቸው ማስተዋል መቻላቸውን ይናገራሉ።

እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ እንደግብርና ሚኒስቴር የበለጠ ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድግ የሚችል ስራ ይሰራሉ። ቡና ወደውጭ በመላክ ረገድ በተለይ ቀርጫንሼ ላለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት የቀዳሚነት ድርሻውን እየተወጣ ነው። በመጋዘን ውስጥ የተመለከትነውም ደረጃውን የማያስለቅቅ ለአገርም ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል ክምችት የያዘ ቡና መኖሩን ነው፤ ለዚህም በጣም ደስተኞች ነን።

አርሶአደሮቹ ጥሩ የቴክኖሎጂ ስራ ካላቸው ከግል ሴአልሚዎች ጋር በመቀናጀት ምርታቸውን እንዲያሳድጉ ለማድረግ የሚያስችል የአሰራር ማዕቀፍ መዘርጋት ነው። የተሻለ ገበያ እንዲያገኝ ከማድረግ አኳያ የተዘረጉ አሰራሮች አሉ፤ ትልቁ ነገር አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት ቀጥታ ወደ ገበያ ለማድረስ የሚያስችለው አቅም ገበያ የማፈላለግ ችሎታ የማዳበር ስራ መሰራት ይኖርበታል። እንዲህ ከሆነ በለፋው ልክ ጥቅም እንዲያገኝ ያችለዋልና በዚህ ደረጃ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል ብለዋል።

ዶክተር አዱኛ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ባለስልጣኑ ቡና ከማብቀል ጀምሮ ውጭ አገር እስከ መላክ ድረስ ያለውን ሂደት በማገዝ እንዲሁም ገበያ በማፈላለግ ረገድ በመስራት ላይ ይገኛል። አርሶ አደሮቻችን እስከ ውጭ አገር በራሳቸው እንዲልኩ ይሰራል። 500 ያህል አርሶ አደሮች ወደውጭ አገር መላክ የሚያስችላቸውን ሰነድ አውጥተዋል። በዚህም እየሄዱበት ነው።

ቀርጫንሼ የሰራው ስራ በአርአያነት መጠቀስ የሚያስችል ስራ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በቦታው ተገኝተን ያስተዋልነው ነገር ቢኖር ይህን ነው ብለዋል። ይህም ወደሌሎቹም መስፋፋት ያለበት ቴክኖሎጂ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ስራው ደግሞ እንደ መንግስት ድጋፍ እናደርግለታለን ብለዋል።

አዲስ ዘመን ጥር 10/2013 ዓ.ም

Leave a Reply