« ቀጣዩ አምባሳደር የኢትዮጵያና አሜሪካን ግንኙነት ለማጠናከር ይበልጥ መሥራት ይኖርበታል» አምባሳደር ራይነር

አሜሪካየኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብታዊ እድገት እድሎች እንዲስፋፉ በተለይም አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነትን እንዲያጎለብቱ ድጋፍ ማድረጓን ተሰናባቹ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር ተናገሩ።

ማይክል ራይነር ሀገራቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት ለኢትዮጵያ ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጓን ገልፀዋል።

አምባሳደሩ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው የሰሩባቸውን ያለፉት ሦስት ዓመታት ቆይታቸውን አስመልክተው ዛሬ ከጋዜጠኞች ጋር ተወያይተዋል።

አሜሪካ ለተለያዩ ዘርፎች ፈሰስ ባደረገችው በዚህ ገንዘብ በኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብታዊ እድገት ዕድሎች መስፋፋታቸውንና አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነትን እንዲያጎለብቱ መደረጉን ተናግረዋል።

ወጣቶች ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑና በርካታ የአሜሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ተዋናዮች ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ ድጋፉ እገዛ ማድረጉንም ነው ተሰናባቹ አምባሳደር መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ ራሷን በምግብ ለመቻል ለምታደርገው ጥረት አሜሪካ ድጋፍ ያደረገች ሲሆን በተፈጥሯዊ ችግር ሠብዓዊ ቀውስ ለገጠማቸው ዜጎችም ድጎማ ተደርጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያን የትምህርት ዘርፍ ለማዘመንና የጤና ዘርፉን ዕድገት በተለይም የኮቪድ-19 ጫናን ለመቋቋምም ድጋፉ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

አሜሪካ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላም ያካሄዷቸውን ዘርፉ ብዙ የለውጥ ሥራዎች መደገፏን ነው አምባሳደሩ የተናገሩት።

በዚህ ዘርፍ ድጋፍ የተደረገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሷቸው ሃሳቦች ከአሜሪካ የዴሞክራሲ መርህና እሳቤ ጋር የሚጣጣም በመሆኑ እንደሆነም አስረድተዋል።

“ይህን ተከትሎም አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት አጋርነት እንዲሰፋ ተደርጓል” ነው ያሉት አምባሳደር ማይክል ራይነር።

የኢትዮጵያ መንግሥት ያከናወናቸው የለውጥ ሥራዎች ተቋማዊ እንዲሆኑና የሚፈለገውን ግብ እንዲመቱ ይበልጥ መሥራት እንደሚገባም ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
“ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የነበሩ ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባቶች፣ አሜሪካ ድጋፍ መሠረዟና
የኢትዮጵያ መንግሥት በውስጣዊ ሁኔታ መጠመድ ግንኙነቱ ላይ አሉታዊ ጫና አሳድሯል” ብለዋል።

ያም ሆኖ ተሹሞ የሚመጣው የአሜሪካ አምባሳደር የሀገራቱ ግንኙነት ላይ ይበልጥ መሥራት እንደሚኖርበት ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሠላም ማስከበርና በቀጣናው ፖለቲካዊ ተሳትፎ
ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የገለጹት።

አምባሳደሩ “በኢትዮጵያ በቆየሁባቸው ዓመታት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር በተከናወኑ ሥራዎች አዎንታዊ ውጤት መገኘቱን አምናለሁ” ብለዋል።

See also  በኬኒያ ናይሮቢ የተፈረመው የስምምነት ሰነድ (ኦሪጂናል ቅጂ) 

የኢትዮጵያና የአሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት ከ100 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።

(ኤፍ ቢ ሲ)

Leave a Reply