ኢትዮጵያ – ኮቪድ ምንም በሽታ የሌለባቸውን ወጣቶች ህይወት እየቀጠፈ ነው

«ተጓዳኝ ህመም የሌለባቸውና በዕድሜ ወጣት የሆኑ ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸው እያለፈ ነው» ዶክተር ውለታው ጫኔ በሚሊኒየም የኮቪድ 19 ሕክምና ማዕከል ዋና ዳይሬክተር

ተጓዳኝ ሕመም የሌለባቸውና በዕድሜ ወጣት የሆኑ ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑን በሚሊኒየም የኮቪድ 19 ሕክምና ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ውለታው ጫኔ አስታወቁ። ቫይረሱ በራሱ ተጨማሪ ተጓዳኝ የጤና ችግሮችን እንደሚያስከትል አሳሰቡ።

ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ውለታው ጫኔ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የኮቪድ 19 ቫይረስ ተጓዳኝ ህመም ያለባቸውንና በዕድሜ የገፉትን ብቻ ነው የሚያጠቃው የሚለው የተሳሳተ ግንዛቤ አሁንም በስፋት ይስተዋላል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የታየው ግን የተጠቁት ተጓዳኝ ህመም የሌለባቸው በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ጭምር ናቸው።

ምንም ዓይነት ተጓዳኝ ህመም የሌለባቸውና በዕድሜ ወጣት የሆኑ ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተሩ፣ ምናልባት በዕድሜ የገፉና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ላይ የበለጠ ቢከፋም እየሞቱ ያሉት ግን በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ዜጎች ናቸው ብለዋል።

አሁን ላይ ባለው ሁኔታ የጽኑ ህሙማን ታካሚዎች እና በኮቪድ 19 ሕይወታቸው የሚያልፍ ወገኖችም ቁጥር ጨምሯል። የማሽን ድጋፍ እና ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ መምጣቱን አስታውቀዋል።

እንደ ዶክተር ውለታው ገለፃ፤ ከወራት በፊት 60 በመቶ የሚሆኑ ታካሚዎች ቶሎ አገግመው የሚወጡ ታካሚዎች ነበሩ፤ አሁን ላይ ግን ከ50 በመቶ በላይ ያለው ታካሚ በፀና ታሞ የሚመጣ ነው። ይህም የሚያሳየው መዘናጋት መኖሩንና ከውጭ ተጎድተው መቆየታቸውን ነው።

ጥንቃቄ በጎደለ ቁጥር የቫይረሱ ዝውውር እየሰፋ እንደሚሄድ ያመለከቱት ዶክተሩ ከሰዎች ጋር ሳይገናኙ በቤት ውስጥ የቆዩ እናቶችና አባቶች መዘናጋት በመኖሩ ምክንያት በቫይረሱ የመጠቃት ዕድላቸው እየጨመረ መጥቷል። ይህም የሞት ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን አመልክተዋል።

See also  መንግስት የኑሮ ወድነትን ለማሻሻልና የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ተከታታይ እርምጃ አንደሚወስድ ተገለጸ

Leave a Reply