ጎንደር ለሰርግ ማድመቂያ የተተኮሰ ጥይት የሙሽራውን ቤተሰቦች ገደለ

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ለሠርግ ማድመቂያ በሚል በተተኮሰ ጥይት የወንድ ሙሽራው ሁለት አጃቢዎች ህይወታቸው ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር መሳፍንት ዓባይ ለኢዜአ እንደተናገሩት አጃቢዎቹ ህይወታቸው ያለፈው በወረዳው ጭህራ ማንጠርኖ በተባለ የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡

ጥር 16/2013 አመሻሽ የተከሰተው አደጋ ሙሽራው ከወንድ አጃቢዎቹ ጋር በመሆን ሴት ሙሽራዋን ከቤተሰቦቹዋ ቤትና ከመንደሩዋ ይዟት በመውጣት ላይ እያለ መሆኑን ን ገልጸዋል፡፡ለሠርጉ ማድመቂያ ተብሎ በአንድ ግለሰብ በተተኮሰው ጥይት ሁለቱ የሙሽራው አጃቢዎች ክፉኛ ቆስለው ወደ ህክምና በመወሰድ ላይ እያሉ ህይወታቻው ማለፉን ዋና ኢንስፔክተር መሳፍንት አስታወቀዋል፡፡

ፖሊስ የሙሽራውን አጃቢዎች አሟሟት በህክምና በማረጋገጥ አስከሬናቸውን ለቤተሰቦቻቸው ማስረከቡንና የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸውም ትናንት መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡በሠርጉ እለት ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብ ለጊዜው ከአካባቢው ሸሽቶ ማምለጡን ያመለከቱት ዋና ኢንስፔክተሩ ፖሊስ ለመያዝ የተጠናከረ ፍለጋ እያካሄደ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

በሠርግና ቀብር ሥነ-ሥርዓት ላይ ጥይት በመተኮስ በንጹሃን ሰዎች ላይ በየጊዜው የሚደርሰውን አደጋ ለመከላከል ማህበረሰቡ ከፖሊስ ጋር ተባብሮ ሊሰራ እንደሚገባም ዋና ኢንስፔክተር መሳፍንት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

See also  ኤርዶጋን - ከሱቅ በደረቴ እስከ ፕሬዚደንትነት

Leave a Reply