. የቀበሌ፣ የወረዳ እና የዞን አመራሮች ሆን ብለው ወይም ተገደው የችግሩ አስተሳሰብ ተሸካሚ ሆነዋል፤
. ከፍተኛ አመራሮችም በአብዛኛው ሆን ብለው የችግሩ አራማጅ ነበሩ፤

አቶ ታደለ ተረፈ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ


(ኢ ፕ ድ)

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን የተከሰተው የጸጥታ ችግር ውስብስብ የሆነው ከቀበሌ ጀምሮ በየደረጃው ባሉ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ አመራሮች የተሳተፉበት በመሆኑ እንደሆነ የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ ገለፁ።

አፈጉባኤው አቶ ታደለ ተረፈ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ በክልሉ ከመጋቢት 2011 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ የፀጥታ ችግሮች ተከስተዋል። ባለፉት ስድስት ወራት ደግሞ ችግሩ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር።

የክልሉ ምክር ቤት ይህንን ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት በህግና ዴሞክራታይዜሽን ቋሚ ኮሚቴ አማካኝነት ልዩ ልዩ ጥረቶችን ቢያደርግም በአካባቢው በነበሩ የፀጥታ ችግሮች የተነሳ ኮሚቴው ታች ድረስ ወርዶ ችግሩን ለማየትና ለመገምገም እንዳልቻለ አመልክተዋል።

በምክር ቤት ደረጃ በጉዳዩ ላይ ምክክርና ውይይት ከተደረገ በኋላ በተደጋጋሚ አቅጣጫዎች ተቀምጠው እንደነበርም አስታውቀዋል።

ችግሩ ከምክር ቤቱም ሆነ ከክልሉ አቅም በላይ በመሆኑ የፌዴራል መንግስት ከአንድም ሶስት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት ችግሩን ለመቆጣጠር ሙከራ አድርጓል ያሉት አቶ ታደለ፤ ይህም ቢሆን ስኬታማ ሊሆን እንዳልቻለ ጠቁመዋል ። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ የውስጥና የውጭ ኃይሎች በአካባቢው ላይ ያላቸው የተለየ ፍላጎት እንደሆነም ገልጸዋል።

ክልሉ ሰፊ የእርሻ መሬት፣ በርካታ ማዕድናትና ጥሬ ሃብት አለው ያሉት አቶ ታደለ፤ ይህም የራሳቸውን ሃብት ለማካበት የሚፈልጉ ኃይሎች ልዩ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ምክንያት መሆኑን አመልክተው፣ ከዚህም ባሻገር ክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚገነባበት ስፍራ በመሆኑ የውጭ ኃይሎች በአካባቢው ላይ ልዩ ትኩረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል ።

በነዚህና ሌሎች ችግሮች የተነሳ ክልሉ የግጭት መናኸሪያ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ታደለ ገለፃ፤ በየደረጃው ያሉት የመንግሥት መዋቅሮች ለችግሩ መባባስ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በተለይ የቀበሌ፣የወረዳ እና የዞን አመራሮች ሆን ብለው ወይም ተገደው የችግሩ አስተሳሰብ ተሸካሚ ሆነዋል ፤ ከዚያ በላይ ያሉ ከፍተኛ አመራሮችም በአብዛኛው ሆን ብለው የችግሩ አራማጅ እንደነበሩ አስታውቀዋል።

በተለይ የቀበሌና የወረዳ አመራሮች በህብረተሰቡ ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው እነዚህን ኃይሎች ከህብረተሰቡ በመነጠል እርምጃ ለመውሰድ አዳጋች እንደነበር የጠቆሙት አቶ ታደለ፤ ይህ ደግሞ ችግሩን ውስብስብ አድርጎት እንደቆየ አመልክተዋል።

በዚህ ውስጥ የሚሳተፉ የታችኛው መዋቅር ውስጥ ያሉ አመራሮችን ሁኔታ ስንመለከት አንዳንዱ ሆን ብሎ የሃሳቡ ደጋፊና ተጋሪ ሆኖ ሲሆን ከፊሉ ደግሞ ተገዶ በጫና የነዚያ የፀረ ሰላም ኃይሎችን እቅድ የሚያስፈጽም ነው።

ወደ ከፍተኛ አመራሩ ሲመጣ ደግሞ በአብዛኛው የአስተሳሰቡ ተሸካሚ ሆኖ ነው። ይህ ደግሞ ከግል ጉዳይ ወይም ከስልጣን ጥማት ጋር ተያይዞ ሊሆን ይችላል። በዚህ የተነሳ የሃሳቡ ተጋሪ የሚሆንበት ሁኔታ አለ። በአጠቃላይ ግን በታችኛው መዋቅር ውስጥ ችግሩ በጣም ሰፊ እንደሆነ አስታውቀዋል።

Via Ena

Leave a Reply