የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክን ከጥፋት የማዳን ሀላፊነት የሁሉም ዜጋ ሊሆን እንደሚገባ ተመለከተ

የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበቅትን የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ የማዳን ሀላፊነት የሁሉም ዜጋ ሊሆን እንደሚገባ ተመለከተ።

ፓርኩን ከጥፋት ለመከላከል 49 ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ዛሬ በአርባምነጭ ከተማ ተካሄዷል፤ ሀብቱን በቅንጅት ለመጠበቅ የሚያስችል የጋራ ሥምምነት ሰነድም ተፈርሟል።

በዚህ ወቅት እንደተገለጸው የነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ በህገወጥ ሰፈራ፣ ልቅ ግጦሽ፣ በደን ምንጣሮና ህገወጥ አደን እንዲሁም የፓርኩ አካል በሆኑት የአባያና ጫሞ ሀይቆች በደለል የመሞላትና በእምቦጭ አረም የመወረር አደጋ ተጋርጦባቸዋል።

በመድረኩ የተገኙት የሀይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን መስራች የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበቅትን የነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ የማዳን ሀላፊነት የመላው ኢትዮጵያውያን ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

ፋውንዴሽንናቸው ፓርኩን ከመጥፋት ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ ገልጸው በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ አሁን ካለበት የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚደረገውውን ጥረት እንደሚያግዙም አስታውቀዋል።

ባለፉት ዓመታት ፓርኩን ከጉዳት ለመታደግ የተናጠል ስራዎች የነበሩ ቢሆንም በጋራና መተባበር ባለመሆኑ የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ አውስተዋል።

ሀብቱን በመጠበቅ ከጥፋት ለመከላከል ፓርኩ ከሚገኝባቸው በደቡብና ኦሮሚያ ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ አዋሳኝ አካባቢዎች በስምምነቱ መሰረት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀይለማርያም ተስፋዬ በበኩላቸው ፓርኩ የሀገር ሀብት ጭምር በመሆኑ የክልሉ መንግስት ከአደጋ ለመጠበቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት በፓርኩ ዙሪያ በተናጠል የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ እንደቆዩ አስታውሰው በፓርኩ ክልል ውስጥ ሰፍረው የነበሩ ማህበረሰቦችን በማወያየት እንዲወጡ መደረጉን ጠቅሰዋል።

እስካሁን በተናጠል ሲሰራ የነበረው ስራ የተፈለገውን ያህል ለውጥ ባለማምጣቱ በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ለመስራት መስማማታቸው ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ የነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ በህገወጥ ሰፋሪዎች፣ ደን ምንጣሮና ከብቶችን በፓርኩ ውስጥ በሚለቁ አካላት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት በፓርኩ ላይ ከፍተኛ የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠበት ጠቁመው ሀብቱን ከጥፋት ለመታደግ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እስካሁን በርካታ ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል።

ይህን ተግባር አጠናክሮ በማስቀጠል ፓርኩን ከጉዳት ነጻ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባባር እንደሚሰራና የተፈረመው የስምምነት ሰነድ ስኬታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋ- (ኢዜአ)

Leave a Reply