ችጋራም መባል ያለበት ኢሳያስ አፈወርቂ ሳይሆን ሃያ ሰባት አመት ኢትዮጵያን ሲዘርፍ ኖሮ የያዝከውን ይዘህ ሰላም ስጠን ሲባል ጥጋብና ዕብሪት ዳግመኛ የስልጣን ረሀብ ውስጥ የከተቱት ህወሃት ነው። ቅር የሚለው ይበለው በግሌ የኤርትራ ህዝብና መንግስት በዚህ ክፉ ወቅት ባለውለታዎቻችን ናቸው። ለዚህም ከምስጋና ውጪ አንዳች ክፉ ቃል መናገር ለሰራዊታን ውሃና እንጀራ ያቀበሉትን የኤርትራ የዳር ሀገር ገበሬዎች በጎ ተግባር መካድም ፣ ነውረኝነትም ነው !

ነጻ አስተያየት – Samson Michailovich

” ኢሳያስ አፈወርቂ /የኤርትራ ህዝብ / ሹካና ማንኪያ የሚዘርፍ ችጋራም ነው ” እያለ ደጋግሞ ሲናገር አደመጥነው። ይልቃል አድማጭና ተከታይ የሌለው ፣ የራሱም ጥላ የምርጫ ካርድ የማይሰጠው ባዶ ተስፋ ውስጥ የገባ ሰው ስለሆነ ስለእርሱ ማውራት ጊዜ ማባከን ነው።

ይልቃል ሹካና ማንኪያ ይዘርፋል ስላሉት የኤርትራ ህዝብና መንግስት ግን ትንሽ እንበል። እኛ ሳንሆን የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት እውነቱን ይናገሩ። የ7ኛው መካናይዝድ ክፍለጦር አዛዥ ብ/ጄነራል ግርማ ክበበው እንደሚነግሩን ጥቅምት 24 ምሽት እርሳቸው ያሉበት ጦር በሃያ አምስት አውቶቡሶች ተሳፍረው በመጡ የትግራይ ልዩ ሀይል አባላት ተኩስ ይከፈትባቸዋል ።

ከዚህ በተጨማሪ ህወሃት ያደራጀው ሚሊሺያም በገፍ ከልዩ ሀይሉ ጋር ቆሟል። እነ ጄነራል ግርማ የቻሉትን የጦሩን ክፍል ይዘው እየተታኮሱ በሽላሎ አድርገው ኤርትራ ይገባሉ። ህወሃት ለሶስት ቀንና ሌሊት የውሃ መጠጫ መስመሮችን ዘግቶ ስለነበር ብዙው የሰራዊት አባል እዚህ ግባ የሚባል እህል ከቀመሰ ቀናት ተቆጥረዋል።

ጄነራሉ እንደሚሉት ኤርትራ ጦሩ ሲገባ ገበሬው በጉንም ፍየሉንም እያረደ ” እንኳን መጣችሁ ” ብሎ ተቀብሎ እህል አቅምሷቸዋል የክፉ ጊዜ መጠጊያም ሆኗቸዋል። አመዛዛኝ ህሊና ያለው ሰው ኤርትራ የጠላት ቀጠና ብትሆን የጦሩ ዕጣ ምን ይሆን ነበር ብሎ ይጠይቅ ! ህወሃት የኢትዮጵያ ጦር አላሸነፈንም ለማለት ከኤርትራ ጨምሮ ፣ ኤምሬትስ ፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን በህብረት ወጉኝ የሚል ፕሮፖጋንዳ እየነዛ ነው።

እሳቤው ‘ ህወሃትን ብዙ ሆናችሁ ካልሆነ አታሸንፉም ‘ የሚል ዕብሪት የወለደው ነው። በሰራዊታችን ድባቅ ከተመታ በኃላ የኤርትራ ሰራዊት ትግራይን ወረረ ይል ጀምሯል ፣ አላማው የትግራይ ጦርነት አለምአቀፋዊ ነው ለማለት እንደ ኮሶቮ የተባበሩት መንግስታት ጦሩን ይላክ የሚል አጀንዳ ያዘለ ነው። እነ ይልቃል ‘ የኤርትራ ጦር ማንኪያና ሹካ ‘ ዘረፈ ሲሉ ከፍየሏ በላይ የሚያለቅሱት የቀጠናው ፖለቲካ ሳይገባቸው ቀርቶ ፣ የኢትዮጵያና ኤርትራ ወዳጅነት ጠቀሜታንም ሳይረዱት አይደለም። ግፍ በተፈጸመበት ሰራዊታችን ላይ የፖለቲካ ቁማር ለመቆመር እንጂ።

ብዙዎቻችን እንደ ይልቃል ጌትነት ከእኔ በላይ ላሳር የትዕቢት ፖለቲካ ውስጥ የለንበትም። ችጋራም መባል ያለበት ኢሳያስ አፈወርቂ ሳይሆን ሃያ ሰባት አመት ኢትዮጵያን ሲዘርፍ ኖሮ የያዝከውን ይዘህ ሰላም ስጠን ሲባል ጥጋብና ዕብሪት ዳግመኛ የስልጣን ረሀብ ውስጥ የከተቱት ህወሃት ነው። ቅር የሚለው ይበለው በግሌ የኤርትራ ህዝብና መንግስት በዚህ ክፉ ወቅት ባለውለታዎቻችን ናቸው። ለዚህም ከምስጋና ውጪ አንዳች ክፉ ቃል መናገር ለሰራዊታን ውሃና እንጀራ ያቀበሉትን የኤርትራ የዳር ሀገር ገበሬዎች በጎ ተግባር መካድም ፣ ነውረኝነትም ነው !

Leave a Reply