የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ለመምህራን ይከፈል የነበረውን የቤት አበል ከብር 850 ወደ ብር 3 ሺህ እንዲሻሻል መወሰኑ ተገለጸ፡፡

የከተማ መስተዳድሩ ካሁን በፊት በከተማው ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሩ መምህራን 5 ሺህ የመኖርያ ቤት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ሆኖም ለሁሉም መምህራን በፍጥነት ቤት ማዘጋጀት ባለመቻሉ፤ ለሁሉም መምህራን 3 ሺህ ብር የቤት አበል ክፍያ እንዲከፈላቸው የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ዛሬ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ካቢኔው በተጨማሪም የከተማ የቦታ ደረጃና የመሬት ሊዝ ዋጋን አስመልክቶ በጥናት የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ አፀደቀ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያጠናው ይህ የመነሻ ሃሳብ ከአሁን በፊት የከተማ ቦታ ደረጃ 14 የነበረውን ወደ 18 ከፍ እንዲል፤ እንዲሁም የሊዝ መነሻ ዋጋ በ18ቱም የቦታ ደረጃዎች ተጠንቶ መቅረቡ ነው የተገለጸው፡፡

የጥናቱ ዋና አላማ በዝቅተኛ ሁኔታ ኑሯቸውን የሚመሩ ዜጎችን እንዳይጎዱ፤ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት፤ ባለሃብቶች ወደ ኢንቨስትመንቱ እንዲገቡ ለማድረግ፤ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን እና ልማትን ለማፋጠን የሚረዳ መሆኑን ተገልጿል፡፡

ጥናቱ አጠቃላይ የከተማ አስተዳደሩ በተለያየ አግባብ የሚያወጣቸውን ወጪ መነሻ በማድረግ በሳይንሳዊ መንገድ እንዲጠና በመደረጉ ባለፉት ሁለት አመታት መሬት በምደባ ብቻ ይሠጥ የነበረውን አሁን ግን በምደባም በጨረታም ለመስጠት ያስችላልም ተብሎአል፡፡

ነባር ይዞታዎችና ሰነድ አልባ ቦታዎች ቀድሞ ባለው መመሪያ 11/2004 የሚስተናገዱ ይሆናሉ በማለት ካቢኔው መወሰኑን ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬተርያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

Via ENA

Leave a Reply