የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 95ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፏል፡፡
ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው ከፍተኛ የዕዳ ጫና ያለባቸውን የመንግስት የልማት ድርጅቶች የዕዳ ጫና ለማቃለል የቀረበ የውሳኔ ሃሳብ እንዲሁም የእዳ እና የሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ለማቋቋም የወጣ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡
በአገሪቱ ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለውና መሠረተ ሰፊ የሆነ የልማት እንቅስቃሴ እንዲኖር ታስቦ ከዓመታት በፊት ተጀምረው ከነበሩት በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶች አብዛኛዎቹ በቂ ዝግጅት ሳይደረግባቸው የተጀመሩ፣ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግር የታየባቸው፣ ብቃት ባለው አመራር ያልተመሩ እና ሌሎችም የፕሮጀክት አስተዳደር ክህሎት ክፍተት የሚታይባቸው በመሆኑ የሜጋ ፕሮጀክቶች ባለቤት የሆኑት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር በብድር የወሰዱትን ገንዘብ መክፈል አልቻሉም፡፡
አገራችን ከገጠማት የኢኮኖሚ ስብራት አንዱ ክፍል ነበሩ፡፡
በመሆኑም የአገር በቀል ኢኮኖሚ ልማት ማዕቀፍ ታሳቢ ያደረገ የማሻሻያ ትግበራ አካል ተደርገው ተወስደዋል፡፡
በዚህም መነሻነት የልማት ድርጅቶቹን የእዳ ጫና ለማቃለል እና ውጤታማ ሆነው እንዲዘልቁ ለማስቻል በቀረበ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ምክር ቤቱ ተወያይቶ ግብዓቶችን በማከል አጽድቋል፡፡ በተጨማሪም ተለይተው የሚሰጡትን የልማት ድርጅቶች እዳዎች የሚያስተዳድር እንዲሁም በጥናት በተለዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የሚሰማራ ብሎም ውጤታማ የእዳና ሃብት አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት የሚያስችል ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ተወያይቶ በማጽደቅ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር የተደረገ ለሴቶች ኢንተርፕሪነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የብድር ስምምነት ለማጽደቅ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ በሴቶች ባለቤትነት የሚካሄዱ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በስልጠናና በፋይናንስ ለመደገፍ፣ ኢንተርፕራይዞች እንዲበራከቱ እና ወደተሻለ ደረጃ እንዲያድጉ ለማድረግ፣ እንዲሁም ሴቶች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚደርስባቸውን ተጽዕኖ ለመቀነስ እና ለስራ እድል ፈጠራ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ስምምነቱም የ100ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር ሲሆን፣ ከወለድ ነጻ፣ የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜ ያለው፣ በ38 ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅና ከአገራችን የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣም መሆኑን በማረጋገጥ የብድር ስምምነት ማጽደቂያ አዋጁ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
በተጨማሪም መቀመጫው በፊላንድ ከሆነው ዳንስኬ ባንክ ጋር የተደረገ ለሜቲዎሮሎጂ ምልከታ መሰረተ ልማት እና የትንበያ አቅም ግንባታ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የብድር ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ምክር ቤቱተወያይቷል፡፡
የስምምነቱ አላማም ለብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዘመናዊ የሆኑ የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳሮች፣ የመብረቅ መከታተያና ተንቀሳቃሽ የአየር ብክለት መከታተያ ጣቢያዎችን ማቋቋሚያ እና የሰው ኃይል አቅም ግንባታ የሚውል ነው፡፡
ብድሩም 8.8 ሚሊየን ዩሮ ሲሆን ወለዱ፣ የብድር ማስተዳደሪያ እና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎች በፊንላንድ መንግስት የሚሸፈኑ ሆነው የአምስት አመት የችሮታ ጊዜ ያለው በ15 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ እና ከአገራችን የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣምመሆኑን በማረጋገጥ ስምምነቱይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

Source – https://www.facebook.com/100378948512242/posts/167426141807522/?d=n

Leave a Reply