አፍሪካን ቸል ያለው የኮቪድ19 ክትባት ሥርጭት

የናጠጡ አገሮች የኮቪድ19 ክትባት እየተሻሙ ገዝተው፤ እየተጣደፉ ዜጎቻቸውን መከተብ ቢጀምሩም አፍሪካ እጅጉን ዘግይታለች። ከአንድ ቢሊዮን በላይ ዜጎች ካሏት አኅጉር እስካሁን ክትባት መስጠት የቻለችው ጊኒ ብቻ ነች። ያውም ለ25 ሰዎች ብቻ።   

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ትናንት ማክሰኞ በዓለም የኤኮኖሚ ፎረም ባደረጉት ንግግር የናጠጡት አገሮች የኮቪድ19 መከላከያ ክትባቶች ከሚያስፈልጋቸው በላይ እያከማቹ ነው ሲሉ ወቅሰዋል። ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው “የዓለም ባለጠጋ አገሮች ክትባቶቹን ከሠሩ እና ከሚያመርቱ ተቋማት ከፍተኛ መጠን ያለው ክትባት በእጃቸው አስገብተዋል። አንዳንድ አገሮች አልፈው ሔደው ከሕዝብ ቁጥራቸው አራት እጥፍ የሚልቅ አግኝተዋል። ይኸ ሌሎች ክትባቶቹ እጅግ የሚያስፈልጋቸውን የዓለም አገሮች በማግለል ክትባቶቹን ለማከማቸት የተደረገ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። 

ይኸ ሥጋት የፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ብቻ አይደለም። የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም የኮሮና ወረርሽኝን አስመልክቶ በሚሰጧቸው መግለጫዎች ፍትሐዊ የኮቪድ19 መከላከያ ክትባት ክፍፍልን ጉዳይ ደጋግመው ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። የባለጠጎቹ አገራት ፖለቲከኞች እና የክትባቶቹ አምራቾች በዚህ የተስማሙ ይመስል ነበር። በጣት የሚቆጠሩ ክትባቶች በጥራት ተቆጣጣሪዎች ሥራ ላይ እንዲውሉ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ሥርጭቱ አሊያም ክፍፍሉ ሲጀመር ግን የሆነው እንደተባለው አይደለም።

ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም “የመጀመሪያዎቹ ክትባቶች መሠራጨት ሲጀምሩ ፍትሐዊ ክፍፍል አደገኛ ሥጋት ላይ ወድቋል። ከ39 ሚሊዮን በላይ ክትባቶች በትንሹ 49 በሚሆኑ ከፍተኛ ገቢ ላላቸው አገሮች ሰዎች ተሰጥተዋል። ለአንድ አነስተኛ ገቢ ላላት አገር የተሰጠው ግን 25 ብቻ ነው። 25 ሚሊዮን አይደለም…25 ሺሕ አይደለም…25 ብቻ…ግልጽ መሆን አለብኝ። ዓለም ከሞራል ውድቀት አፋፍ ቆሟል። የዚህ ውድቀት ዋጋ በሕይወት እና በአኗኗር የሚከፈለው ደግሞ በደሐ አገሮች ነው” ሲሉ ተናግረዋል።  Data visualization COVID-19 New Cases Per Capita – 2021-01-20 – Africa - English

የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭት በአፍሪካ

የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ-መንበር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ከሁለት ሣምንት ገደማ በፊት የኅብረቱ የክትባት ግዢ ግብረ-ኃይል 270 ሚሊዮን የኮቪድ19 መከላከያ ክትባቶች ለአፍሪካ ማግኘቱን አስታውቀዋል። ክትባቶቹ በፋይዘር፣ አስትራዜኔካ እና ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ኩባንያዎች የተሠሩ ናቸው። በአውሮፓ ሥራ ላይ እንዲውሉ ፈቃድ የተሰጣቸውን የመጀመሪያ ሁለት ክትባቶች በሕንዱ ሴረም ኢንስቲትዩት በኩል ለአፍሪካ አገራት ይቀርባሉ። የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት ገና በሰው ላይ በሚደረገው ሙከራ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ሥሪት የጥራት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናትን ይኹንታ ካገኘ ለአንድ ሰው የሚሰጠው ክትባት አንድ ብቻ ይሆናል ተብሎ ስለሚጠበቅ በተለይ ለአፍሪካ ከፍ ያለ ተስፋ የሚጣልበት ነው።  

See also  "ርዝራዥ ጁንታ"የተባለው ሃይል ወደ ሱዳን ሲሸሽ ተደመሰሰ፤ ለይለፍ የኦሮሞ ማንነት መታወቂያ አዘጋጅተው ነበር

በፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የተቋቋመው የአፍሪካ የክትባት ግዢ ግብረ-ኃይል (African Vaccine Acquisition Task Team) 55ቱ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት ክትባቶቹን ለመሸመት አስቀድመው የሚያዙበትን ሥርዓት ዘርግቷል። የአፍሪካ የወጪ እና ገቢ ንግድ ባንክ ያዘጋጀው የሰነድ ረቂቅ እንደሚያሳየው የአፍሪካ አገሮች በኅብረቱ በኩል ለሚያገኟቸው ክትባቶች ለእያንዳንዱ ከ3 እስከ 10 ዶላር እንዲከፍሉ መታቀዱን ሬውተርስ ዘግቧል። ይኸ ቀድሞም የኮሮና ወረርሽኝ በምጣኔ ሐብታቸው ላይ ያስከተለባቸውን ሸክም መቋቋም ለተሳናቸው የአፍሪካ አገሮች የተሻለ እፎይታ የሚፈጥር ይመስላል። ምክንያቱም የበለጸጉት አገሮች ለአንድ ክትባት ከ19.50 እስከ 37 ዶላር ድረስ ይከፍላሉ። የአፍሪካ የወጪ እና ገቢ ንግድ ባንክ ለ55ቱ የአፍሪካ አገሮች የክትባት ግዢ እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር የክፍያ ዋስትና ለአምራቾች እንደሚያቀርብ አስታውቋል። 

በዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ ዳይሬክተር ዶክተር ማትሲዲሶ ሞኤቲ “በአፍሪካ ኮቫክስ 600 ሚሊዮን የመጀመሪያ ዙር ክትባቶች በ2021 መጨረሻ ለማሰራጨት አቅዷል። ይኸ ለአንድ ሰው ሁለት ክትባቶች ቢሰጡ በሚል ስሌት የታቀደ ሲሆን ከአፍሪካ አገሮች ሕዝብ 20 በመቶውን ለመከተብ ያስችላል። የመጀመሪያዎቹ 30 ሚሊዮን ክትባቶች በየካቲት ለአገሮቹ መድረስ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል። እነዚህ ለጤና ሰራተኞች እና ሌሎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎት የታቀደ ሲሆን በሒደት በተጨማሪ ተጋላጭ ወደሆኑት ይዳረሳል” ብለዋል።

 https://twitter.com/i/status/1353266306615808000

አፍሪካ በኮቫክስ በኩል የምታገኛቸው ክትባቶች ግን ወረርሽኙን ለመቋቋም በቂ ለመሆናቸው በርካቶች ጥያቄ አላቸው። በዚያ ላይ ክትባቶቹ ከአፍሪካ አገራት ዘንድ የሚደርሱት እስከ የካቲት ዘግይተው ነው። የኬንያ የጤና ምኒስትር ሙታይ ካግዌ “በጤና ረገድ ለደሕንነታችን በምዕራባውያን ላይ ጥገኛ መሆን የዋሕነት ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። 
ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖምም የናጠጡት አገሮች ለዜጎቻቸው ቅድሚያ ለመስጠት የክትባት አምራቾች ትርፍ ለማጋበስ ትኩረት አድርገዋል ሲሉ ከሁለት ሳምንት በፊት የዓለም ጤና ድርጅት ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ስብሰባ ሲጀመር ወቅሰዋል። 

“ስለ ፍትሐዊ ክፍፍል እያወሩ አንዳንድ አገሮች እና ኩባንያዎች ኮቫክስን ገሸሽ በማድረግ ለተናጠል ሥምምነቶች ቅድሚያ በመስጠት ክትባቶቹን ቅድሚያ ለማግኘት ዋጋውን እያስወደዱ ነው። ይኸ ስህተት ነው። አብዛኞቹ አምራቾች ሰነዶችን ለዓለም ጤና ድርጅት ከማቅረብ ይልቅ ከፍተኛ ትርፍ በሚያገኙባቸው የበለጸጉ አገሮች ፈቃድ ማግኘትን በማስቀደማቸው ኹኔታው ተወሳስቧል” ያሉት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር “ይኸ የእኔ ልቅደም አካሔድ የዓለም ደሐ እና ተጋላጭ ሕዝቦችን ቸል ማለት ብቻ ሳይሆን ራስንም ለሽንፈት መዳረግ ነው። በስተመጨረሻ እንዲህ አይነት እርምጃዎች ከወረርሽኙ በተጨማሪ ሕመማችንን፣ ለመቆጣጠር የሚደረጉ ክልከላዎችን እና ሰብዓዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳቱን ጭምር ያራዝሙታል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።  

See also  " ከአዲሱ የኢትዮጵያ ካርታ ጋር ተያይዞ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጨዉ መረጃ ተቀባይነት የሌለዉና መወገዝ ያለበት ነዉ"

ዶክተር ቴድሮስ የፍትሐዊ ክፍፍል እጦት “ዓለምን ከሞራል ውድቀት አፋፍ ጥሎታል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ከትናንት በስቲያ ሰኞ ሁለት ዓለም አቀፍ ተቋማት ይፋ ያደረጓቸውን ጥናቶች ጠቅሰው እንደተናገሩት ግን ጉዳዩ የሞራል ውድቀት ብቻ ሳይሆን ምጣኔ ሐብታዊ ቀውስም ያስከትላል። 

በበርካታ የአፍሪካ አገራት ሆስፒታሎች በኮሮና ሕሙማን ብዛት ጫና ውስጥ መግባት ጀምረዋል

“የዓለም የሥራ ድርጅት ይፋ ያደረገው አዲስ ሪፖርት ወረርሽኙ በዓለም የሥራ ገበያ ላይ ያሳደረውን ጫና ተንትኗል። ጥናቱ ባለፈው አመት 8.8 በመቶ ዓለም አቀፍ የሥራ ሰዓታት በወረርሽኙ ሳቢያ መባከናቸውን ደርሶበታል። ይኸ የዓለም የሰራተኞችን ወደ 3.7 ትሪሊዮን ዶላር ገቢ አሳጥቷል። ሪፖርቱ አብዛኞቹ አገሮች በ2021 ሁለተኛ መንፈቅ እንደሚያገግሙ ትንበያ አስቀምጧል። ይኸ ግን በክትባት ሥርጭት ላይ የሚመሰረት ነው። ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት ክትባት ለዜጎቻቸው እንዲያዳርሱ፤ ምጣኔ ሐብታቸው እንዲያገግም እና የቅጥር ዕድል እንዲሻሻል ድጋፍ እንዲደረግላቸው ምክረ ሐሳብ ሰጥቷል” ሲሉ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ተናግረዋል።

ዶክተር ቴድሮስ  “ዓለም አቀፉ የንግድ ምክር ቤት ያሰራው ሁለተኛ ጥናት ፍትሐዊ የክትባት ክፍፍል ሊኖር እንደሚገባ ጠንካራ ሙግት አቅርቧል። ጥናቱ የፍትሐዊ የክትባት ሥርጭት እጦት ዓለምን እስከ 9.2 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚያሳጣ ይኸው ጥናት ይገልፃል። ከዚህ ግማሽ ያክሉ ማለትም ወደ 4.5 ትሪሊዮን ዶላር የሚሆነው በበለጸጉት ኤኮኖሚዎች ላይ የሚወድቅ ነው” ሲሉ አብራርተዋል። 

ዶክተር ቴድሮስ እንዳሉት የኮቪድ19 ክትባቶች ሥርጭትን ለማፋጠን የጎደለው ወደ 26 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው። ይኸው የኮቪድ19 ክትባቶችን በአፋጣኝ ለማሰራጨት የተዘረጋ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ቢያገኝ በእያንዳንዱ ዶላር እስከ 126 ዶላር ገደማ ትርፍ ይገኝበታል። “ባለጠጎቹ ለዜጎቻቸው ክትባት ሲሰጡ ደሐዎቹ እጃቸውን አጣምረው እየተጠባበቁ ነው” ያሉት ዶክተር ቴድሮስ “እያንዳንዷ ሰዓት ባለፈች ቁጥር ባላቸው እና በሌላቸው መካከል ያለው ልዩነት ይበልጥ እየሰፋ ይሔዳል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። 

እሸቴ በቀለ – አዜብ ታደሰ    listen the audio here

Leave a Reply