ጆሮ ያለህ ስማ። ልብ ያለህ ልብ በል። ህሊና ያለህ አስተውል። ማሰብና ረጋ ብሎ መመርመር የወቅቱ ጥያቄ ነው። ጠላቶቻችን ከመቼውም ይልቅ ዛሬ ጥፍራቸውን ስለው፣ ምላሳቸውን አሹለው፣ የዘረፉትንና በጓሮ የሚቀበሉትን ሃብታቸውን በትነውና ነስንሰው፣ ተነስተዋል። አገር አልባ፣ ታሪክ አልባ፣ መቀበሪያ አልባ ሊያደርጉህ በጥፋት ባቡር እየከነፉ ነው። አባቶችህ፣ እናቶችህ፣ አያቶችህን ቅድመ አያቶችህ ” ቃል ወይም ሞት፣ ሃቅ የአምነት እዳ ነው” ብለው ደማቸውን ገብረው፣ አጥንታቸውን ሰብረው ያቆዩዋትን አገር ሊያሳጡን ከአብራኳ የተወለዱትን ፊት አድረገው እየታተሩ ነው።

ዶሮ ከምትበላው በላይ ጭራ እንደምትበትን ሁሉ፣ እነሱ የማይበሉዋት አገር እንድትወላልቅ ሌት ተቀን እየደከሙ ነበሩ። ዛሬ የባንዳነት ዘመን የሚመከትበት ሳይሆን የሚከስምበት ዘመን በመቃረቡ መርዛቸውን በጥብጠው ከጎረቤት እስከ መሐል አገር ዘመቻው ተጧጡፏል። አንተ ራስህ በምትቆርጠው ቀለብ እያሳስቱህ በሃሰት ፕሮፓጋንዳ አገርህን ሊያሰምጡ ከጸጉረ ልውጡና ከውስጥ ቀበሮዎች ጋር እየተናበቡ እየሰሩልህ ነው። እንደ ፍልፈል ውስጥህን እየቦረቦሩት ነው። እስከዛሬ ስንሞት፣ ስንደማ፣ ስንገረፍ፣ ስንዘረፍ፣ ስንወቀጥና ስንኮላሽ ” የት ነበራችሁ” ያላሉን ዛሬ ካጥናፍ አጥናፍ በበሉትና በሴራቸው መጠን እየጮሁ ነው።

የአገርህ አሌኝታ መከላከያ “እንኳን ታረደ” የሚሉ ዜጎች አገር ቤት ቁጭ ብለው የወገን ደም ላይ ሲማማሉ እየታየ ነው። ሰራዊታችን ግፍ ተፈጽሞበት እንደ ባዕድ መዛበቻ መሆኑን የሚያደንቁ እንግዴ ልጆች ሂሳቡ በማይታወቅ ደረጃ ከአገርህ ጠላት ጋር አብረው እሜዳህ ላይ እየተዛበቱ ነው። ችግር ካለ በርጋታ በር ዘግቶ መነጋገር ሲቻል አገር ዙሪያዋን በሉሲፈር ቀንደኞች ተወጥራ፣ ዜጎች ተፈናቅለውና በየቦታው ተሰደው ባለበት ወቅት ቤንዚን የሚያርከፍክፉ፣ የነጭ ደጅ የሚልከሰከሱ እያየህ ስለምን ዝም ትላለህ? ስለምን ዝም ትያለሽ?

እኒህ ክፉዎች አገርህን ሊያጠፏት ሲማማሉ የአንተ ዝምታ ምክንያት የሚቀርብበት አይሆንም። ሊሆንም አይችልም። ነገ ብትቆጭ ወይም ብታለቅሺ ከንቱ ውዳሴ ነው። ዋጋ የለውም።

ወደድክም ጠላህም/ ጠላሺም ዝምታን በመረጥክ/ ሺ ቁጥር እነሱ በሃሰት ገዝፈው ትውልዱን ይበሉታል። ብታምንም ባታምንም አገር አልባ እንሆናለን። ፈለክም አልፈለክም ትፈርሳለህ። ነገር ግን ዝምታህን ሰብረህ ከተነሳህ ድምጽህ ከሃጂዎቹን በሙሉ ያከስማቸዋል። ምናምንቴዎች ይሆናሉ። እንደ ኢያሪኮ ይናዳሉ። እንደ ሎጥ ሚስት የጨው አምድ ይሆናሉ። ከሃጂዎቹን ብቻ ሳይሆን ከከሃጂዎቹ ጀርባ ያሉትን ተኩላዎችና ዋናዎቹን ሊበሉን ያሰፈሰፉ የፈርዖን ጅቦችን ያጠፋቸዋል። ስለዚህ ባንተ ዝምታ ላይ አገርህን ለማፍረስ ለሚጥሩ አትመች። ተነሳ!! አገር በመከላከያ ብቻ አትደንምና!!

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚከተለውን ጥሪ አቅርበዋል። ጆሮ ያለህ ስማ!! አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ ደረጃ ከነገረህ ቀሪውን ረጋ በልና አስላው

የጠቅላይ ሚንስትር አብይ ጥሪ

በመላው ዓለም ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የእናት ሆድ ዥንጉርጉርነት የልጆችዋን መልክና ጠባይ አንድ አይነት እንደማያደርገው ሁሉ፤ ከኢትዮጵያ ማህጸን በቅለው፣ የክብር ቦታ አግኝተውና ከሩብ ክፍለ ዘመን ለተሻገረ ጊዜ ሀገር የአስተዳደሩ ሰዎች መልሰው ሀገራችንን ከጀርባ ቢወጓት፥ የእናትን ውርደት በማይፈልጉ ኢትዮጵያውያን ርብርብ እርምጃ ተወስዶባቸዋል።

ዳሩ ግን፥ ዛሬም የጁንታው ሞት ያልተዋጠላቸው ከዥንጉርጉር ማህጸኗ የፈለቁ ሰዎች ከሀገራችን ጠላቶች ጋር እያበሩ፣ የተዛቡ መረጃዎች መርጨቱን የዕለት እንጀራቸው አድርገውታል። እንዳሻቸው መሆን ካልቻሉ ኢትዮጵያ እንድትኖር አይፈልጉም።

በሕግ ማስከበር ዘመቻው ያጡትን ድል በወሬ ግንባር ለመመለስ ተንኮልን መሣሪያ፣ ሐሰትን ጥይት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።በመሆኑም በመላው ዓለም የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች፥ ስለ ሀገራችሁና ስለ ወቅታዊው ጉዳይ ትክክለኛውን መረጃ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በመናገር፤ የሀገራችንን መልካም ክብርና ስም ለማጥፋት የተነሱ ሰዎችን ድል በመንሳት፤ ሐሰትን በእውነት እንድታሸንፉ ጥሪ አቀርባለሁ።

Leave a Reply