በመስከር በሚፈጸም ወንጀል ስለሚኖር የወንጀል ሀላፊነትና የህጉ አንድምታ


አንድ ሰው ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ ክስ ሊቀርብበት እና ሊቀጣ የሚችለው የተላለፈውን የወንጀል ድርጊት ሊያቋቁሙ የሚችሉት ህጋዊ፤ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች ባንድ ላይ ተሟልተው ሲገኙ ብቻ እንደሆነ የኢፌድሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 23/2/ ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሰረት የወንጀል ፈጻሚው የሀሳብ ክፍል (moral element) መረጋገጥ ያለበት አንዱ ዋናው የወንጀል ማቋቋሚያ መስፈርት መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል አንድ ሰው በወንጀል ህግ መደበኛ ድንጋጌዎች መሰረት የሚቀጣው ላደረገው ድርጊት ሃላፊ የሆነው ወንጀል አድራጊ ብቻ ነው፡፡ በእድሜ፣ በህመም፣ ባልተለመደ የእድገት መዘግየት፤ ጥልቅ በሆነ የአእምሮ የመገንዘብ ወይም የማመዛዘን ችሎታ መቃወስ ወይም በማናቸውም ስነ ህይዎታዊ ዘዴ ድርጊቱ ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት ለመገንዘብ የማይችል እንደሆነ ፍርድ ቤት ቀርቦ ችግሩ ስለመኖሩ በበቂ ማስረጃ ሲረጋገጥ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ከወንጀል ተጠያቂነት ሊድን እንደሚችል የወንጀል ህጋችን አንቀጽ 48 እና 49 ድንጋጌዎች ያመለክታሉ፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በአልኮል ወይም በሌላ አዕምሮን በሚያደነዝዝ ነገር መስከር የአእምሮ የመገንዘብ ወይም የማመዛዘን ችሎታ መቃወስ ሊያስከትል ቢችልም ከጉዳዩ ልዩ ባህሪ አንጻርም በመስከር በሚፈጸም ወንጀል ስለሚኖር የወንጀል ሃላፊነት፤ ፍፁም ወይም ከፊል ኢ-ሃላፊነት ሊያስይቅ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ በእነዚህ ድንጋጌዎችም መሰረት በስካር ውስጥ ሆነው የወንጀል ድርጊት የፈጸሙ ሰዎች እንደየሁኔታው ከሙሉ ሃላፊነት እሰከ ከፊል ሃላፊነት ወይም ሙሉ በሙሉ ኢ-ሃላፊ ናቸው በሚል በፍርድ ቤቶች ውሳኔ ይሰጣል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ብዙ ተከሳሾች ወንጀሉን የፈጸምሁት ሰክሬ ነው፤ ሃላፊነት የለብኝም በሚል የሚከራከሩ እና በዚሁ መሰረት ውሳኔ ሲሰጥ ይሰተዋላል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መከራከሪያ ከመቅረቡ በፊትም ሆነ በዚህ መከራከሪያ መሰረት ውሳኔ ለመስጠት የሚከተሉት ነጥቦች በሚገባ መታየት አለባቸው፡፡ ይኸውም ግለሰቡ የሰከረው እና ድርጊቱን የፈጸመው፡-

• ወንጀሉን ለመፈፀም በራሱ ፍላጐት ወንጀሉን ለመፈፀም በማቀድ ወይም ሊፈፅም እንደሚችል እያወቀ (50/1/) መሆኑ፣ ወይም
• ድርጊቱ ወንጀሉን ለመፈፀም እራሱን እንደሚያጋልጥ እያወቀ፣ ማወቅ እየቻለ ወይም ማወቅ እያለበት በራሱ ጥፋት ስለመሆኑ(50/2/ሀ/) ፣
• በቸልተኝነት ራሱን ወደ ከፊል ወይም ፍፁም ኢ-ሃላፊነት ራሱን ካስገባ በኋላ ሊያደርግ ያልፈቀደውን ወይም ያላሠበውን ወንጀል ስለማድረግ አለማድረጉ 50/3/፤59 እና 491፣ ወይም
• ምንም ጥፋት ሣይኖረው (ተገዶ) በፍፁም ኢ-ሃላፊነት ውስጥ ባለበት ጊዜ የፈፀመው ድርጊት (50/4/) ስለመሆን አለመሆኑ፣
• ከሁሉም በላይ ግን የተከሣሽን ፍፁም ወይም ከፊል ኢ-ሃላፊነት ማስረዳት ያለበት ማን እና በምን ሁኔታ ነው የሚሉትን ነጥቦች ከወንጀል ህጉ አንቀጽ 51 መሠረታዊ ሃሳቦች ማየት ተገቢ ይሆናል፡፡

See also  "ሚዲያዎች ፊቴን ይሸፍናሉ... እኔ አላፍርም ዓለም ግፋቸውን ይመልከት፣ እነሱ ይፈሩ" የ14 ዓመቷ ታዳጊ

እነዚህ ነጥቦች ባብዛኛው የሰውን ልጅ ውስጣዊ የእምሮ ማገናዘብ እና የማመዛዝን ደረጃን እና ሁኔታን የሚመዝኑ በመሆኑ የሚረጋገጡትም ጠንከር ባለ እና በበቂ ማሰረጃ አንዳንዴም በሞያ ማስረጃ (expertise witness) ሊሆን ይችላል፡፡ በመሠረቱ የወንጀል ህጉ አንቀጽ 51/1/ ድንጋጌ በግልፅ እንደሚያመለክተው አንድ ሠው በስካርም ይሁን በሌላ ምክንያት አንድን ድርጊት ሲፈፅም በከፊል ወይም በፍፁም ሀላፊ ስለመሆኑ አጠራጣሪ ነገር ሲኖር ልዩ የአዋቂ ምርመራ በፍ/ቤት ትዕዛዝ መሠረት ሊጣራ የሚገባው ስለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም አንድ ሰው አልኮል አልኮል በመሽተቱ፣ በመኮላተፉ እና በመንገዳገዱ ምክንያት በፍፁም ሃላፊነት ውስጥ እራሱን አስገብቶ ነበር ብሎ መደምደም ተገቢነት ያለው አይደለም፡፡ ይህም ተከሳሽ በመስከሩ እና ማገናዘብ ባለመቻሉ ምክንያት ድርጊቱን ስለመፈጸሙ ፍ/ቤት አዝዞ በልዩ የአዋቂ ምርመራ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በግምት ተከሣሽ ፍፁም ኢ-ሃላፊነት ነበረው ወደሚለው መደምደሚያ ይወስደናል፡፡ በሌላ በኩል የተከሣሽን መስከር በምስክሮች ቃል አረጋግጫለሁ ቢባል እንኳን (ምስክሮች በጉዳዩ ላይ ልዩ አዋቂ አለመሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ) ተከሣሽ ወደ ፍፁም ኢ-ሃላፊነት የገባው ከላይ በተገለፀው አግባብ ድርጊቱን ለመፈፀም በማቀድ፣ ወይም ሊፈፀም እንደሚችል እያወቀ አስቦ እራሱን ወደ ፍፁም ኢ-ሃላፊነት አስገብቶ ከሆነ እነዚህ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ የማይሆኑለት እና በመደበኛ ድንጋጌዎች መሠረት ሊከሰስ እና ሊቀጣ የሚገባው ስለመሆኑ የወንጀል ህጉ አንቀጽ 50/1/ ድንጋጌ ያስረዳል፡፡ በአንፃሩ ተከሣሽ የወንጀል ድርጊቱን ለመፈፀም ራሱን እንደሚያጋልጥ እያወቀ ወይም ለማወቅ እየቻለ ወይም ማወቅ እያለበት በራሱ ጥፋት ወደ ፍፁም ኢ-ሃላፊነት ወይም ከፊል-ሀላፊነት ራሱን ካስገባ በኋላ ድርጊቱን የፈፀመ እንደሆነ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 50/2/ እና 59 መሠረት በቸልተኝነት በፈፀመው ድርጊት ተጠያቂ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡

በሌላ በኩል አድራጊው በገዛ ጥፋቱ ወደ ፍፁም ኢ-ሃላፊነት ራሱን ካስገባ በኋላ ያልፈቀደውን ወይም ያላሰበውን የወንጀል ድርጊት ከፈፀመም በወንጀል ህጉ አንቀጽ 491 መሠረት ተጠያቂ እንደሚሆን የወንጀል ህጉ አንቀጽ 50/3/ ድንጋጌ ያዝዛል፣ በተጨማሪም ተከሣሹ ምንም ጥፋት ሳይኖረው ወይም በሌላ ሰው ተገዶ በፍፁም ኢ-ሃላፊነት ውስጥ የነበረ ከሆነም የወንጀል ተጠያቂነት የሌለው ስለመሆኑ የወንጀል ህጉ አንቀጽ 50/4/ ድንጋጌ ያስቀምጣል፡፡

See also  የሞት ቅጣት የሚያሰጋቸው ጀማል እና ሀሰን

ስለሆነም አንድ ሰው በወንጀል ተከሶ ድርጊቱን የፈጸመው በስካር ውስጥ መሆኑ ቢረጋግጥ እንኳን ወደ ስካር የገባው ወንጀሉን ለመፈጸም አቅዶ ስለመሆኑ ወይም በሶስተኛ ወገን ተገፋፍቶ ስለመሆኑና አለመሆኑ ወይም ስለሀላፊነት መጠኑ በአግባቡ በማስረጃ መረጋገጥ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
በአጠቃላይ በስካር የሚፈጸሙ የወንጀል ድረጊቶች በአብዛኛው ከወንጀል ተጠያቂነት የማያድኑ በመሆኑ ዜጎች ይህንን ተገንዝበው ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ስካር እና የወንጀል ሃላፊነት በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው እና የማስረጃ ደረጃዉም ከተለመደው የማስረጃ አቀራረብ ላቅ ያለ የአዋቂ ማስረጃን የሚጠይቅ በመሆኑ ተከሳሾች፣ ዐቃቢያነ ህጎችም ሆነ ዳኞች በሚሰጧቸው ውሳኔዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው ማየት ተገቢ ነው እንላለን፡፡

Attorney general

Leave a Reply