በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በጣና ክፍለ ከተማ በሕገ ወጥ መንገድ በግለሰብ ቤት የተከማቸ 11 በርሜል ነዳጅ እና ቤንዚን መያዙ ተሰማ። በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ እጥረት እንደነበር ሲገለጽ ነበር።

ትናንት በሕዝብ በደረሰ ጥቆማ መሰረት የባሕር ዳር ከተማ ንግድ መምሪያ፣ የጣና ክፍለ ከተማ ንግድ ጽሕፈት ቤት፣ የከተማዋ የፀጥታ ኃይል እና ፖሊስ በጋራ ባደረጉት ዘመቻ በህገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ነዳጅ እና ቤንዚን ተይዟል፡፡

በጣና ክፍለ ከተማ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ 11 በርሜል ነዳጅ እና ቤንዚን እንዲሁም ለጥቁር ገበያ የተዘጋጀ ቤንዚን በ20 ባለሁለት ሊትር የውኃ ማሸጊያ ሃይላንድ መያዙን በባሕር ዳር ከተማ ፖሊስ መምሪያ የ6ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ንብረት ተፈራ ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው ተብሏል፡፡ የተያዘው ነዳጅ እና ቤንዚን የዘርፉ ፈቃድ በሌለው ግሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ ነው ያሉት ምክትል ኢንስፔክተር ንብረቱ ለጥቁር ገበያው መበራከት ምክንያት የሆነውን እጥረት መፍታት ወደ ገበያ ይገባልም ነው ያሉት፡፡ ሕዝቡ ተመሳሳይ ጥቆማዎችን በመስጠት ከፖሊስ ጎን እንዲቆም ጥሪ ማቅረባቸውን አብመድ ዘግቧል።

በአማራ ክልል የነዳጅ እጥረት መኖሩ በተጠቆመበት ውይይት ላይ በዘርፉ የተሰማሩ በርካታ የማሻሻያ ጥቆማ ሰጥንተው ነበር። ከጥቆማቸው መካከል አንዱና የመጀመሪያው በክልሉ ህገወጥ ነጋዴዎች ነዳጅ እንደሚሸሽጉ መናገራቸው የሚጠቀስ ነው። በሌላም በኩል የነዳጅ ማደያዎችን ለመገንባት የቦታ ጥያቄ ቢቀርብም በቂ ምላሽ አለመሰጠቱ ነዳጅ ከቦታ ቦታ እያዘዋወሩ ለሚሸጡ የጥቁር ገበያ ነጋዴዎች እድሉን እንዳመቻቸላቸው ተመልክቶ ነበር።

Leave a Reply