የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማንበብና መጻፍ ለማይችሉ ዲግሪ እንደሚሰጡ ተገለጸ

በአንዳንድ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አሥረኛ ክፍል ላቋረጡ ተማሪዎች፣ በተጨማሪም ማንበብና መጻፍ ለማይችሉ ሰዎች ዲግሪ እንደሚሰጡ ተገለጸ፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትምህርት ጥራት ላይ ማክሰኞ ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አንዱዓለም አድማሴ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በአንዳንድ የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠው የትምህርት ጥራት መጓደል አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

‹‹አንዳንድ የትምህርት ተቋማት አሥረኛ ክፍል ላቋረጡ ተማሪዎች ዲግሪ ይሰጣሉ፡፡ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ሰዎችም እንዲሁ ወረቀት እየወሰዱ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ ፈቃድ አውጥተው እየተንቀሳቀሱ ያሉ አንዳንድ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሕግ ውጪ በመንቀሳቀስ፣ በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደሩ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም፣ የጥራትና አግባብነት ችግር በሰፊው እንደሚስተዋል አንዱዓለም (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ለትምህርት ጥራቱ መቀነስ የተቋማት የትምህርት ሥርዓት ዝግጅት ማነስ፣ የመምህራን አቅም ውስንነት፣ ያለ በቂ ዝግጅት ትምህርት ቤቶችን ከፍቶ ለማስተማር መንቀሳቀስና መሰል ዓይነት ችግሮች ተጠቅሰዋል፡፡

በአንዳንድ ትምህርት ተቋማት መቁረጫ ነጥብ ሳያሟሉ ትምህርቶቻቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች መኖራቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው፣ ችግሮች ዕርምጃ በመውሰድ ብቻ እንደማይፈቱና ተቀራርቦ በመነጋገርና በመደጋገፍ ለማስተካከል መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማንበብና መጻፍ ለማይችሉ ሰዎች ዲግሪ እንደሚሰጡ ተገለጸ | ሪፖርተር Ethiopian Reporter Amharic

    Leave a Reply