የአዲስ አበባንና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የምርጫ ቀን ፖለቲካዊ አንድምታ አለው በሚል የሚነሱ ሀሳቦች የተሳሳቱ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ አስታወቁ።

ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ባለበት አካባቢ ምርጫ እንደማይደረግም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ“በምርጫ ብቻ” በሚል ለሶስት ተከታታይ ቀናት “ምርጫ ቦርድን ይጠይቁ” በሚል ርእስ የማህበራዊ ሚዲያ ተሳትፎ መድረክ አዘጋጅቶ ነበር።

ቦርዱ በማህበራዊ ሚዲያ የተነሱለትን ጥያቄዎች በመሰብሰብ በቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

የአዲስ አበባንና ድሬደዋን የምርጫ ቀን በተመለከተ የፖለቲካ ምልከታ ሊኖረው ይችላል በሚል የሚነሳ ሃሰብ መኖሩን የጠቆሙት ዋና ሰብሳቢዋ የሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች የምርጫ ቀናት ከሌሎች አካባቢዎች የተለየበት ምክንያት የምርጫውን ተአማኒነት ለማረጋገጥና ፖለቲካዊ ችግሮች እንዳይከሰቱ ታስቦ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ከ1997 ዓ.ም በኋላ አስተዳደራዊ ለውጦች መደረጋቸውን ተከትሎ የቀበሌ አስተዳደር በመቅረቱ ድሮ በምርጫ አከላለል የነበረው የቀበሌ ሁኔታ አሁን አለመኖሩን አንስተው፤ አዳዲስ ክፍለ ከተሞች መኖራቸው አንዲሁም የወረዳ ወንበሮች በክፍለከተማ ደረጃ በሚገኝ ምክር ቤት እንዲሆን በከተማ ደረጃ መወሰኑን ገልጸዋል።

የከተማዋ ምርጫ ከክልሎች ምርጫ ጋር እኩል ቢካሄድ አከላለቻቸው አስቸጋሪ በሆኑ በነዚህ ቦታዎች ላይ የሚካሄደውን ምርጫ ለመቆጣጠርና በተአማኒነት ለመቀበል ምቹ አለመሆኑን ነው ተናገሩት።

ይህም ለፓርቲዎችም ታዛቢና ወኪሎቻቸውን ለመላክ አስቸጋሪና አጠራጣሪ እንደሚያደርግባቸው ተናግረዋል።

የሁለቱ ከተማ መስተዳደሮች ምርጫ ግልጽና ቁጥጥር የተደረገበት እንዲሆን ከሌሎች አካባቢዎች ምርጫ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ አንዲካሄድ መወሰኑን አመልክተዋል።

በዚህም የከተሞቹ ምርጫ ቀን መራዘም ፖለቲካዊ አንድምታ አለው የሚለው መታሰብ የሌለበትና ከተሳሳተ አተያይ የመነጨ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ በኩል የሚሱ ጉዳዮች ተቀባይነት እንደሌላቸው አስታውቀዋል።

ከመታወቂያ ጋር ተያይዞ የሚነሱትን ጉዳዮች ለመፍታት ተቋሙ የራሱን አሰራር እንደዘረጋና ቁጥጥር እንደሚደረግ ነው የገለጹት።

ህብረተሰቡም ከእነሱ ቀበሌ ውጪ ነዋሪ የሆነ አካል ወደ ምርጫው በሚመጣበት ጊዜ መቆጣጠርና ማጋለጥ እንዳለበት አስገንዝበው በዚህ ጉዳይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሲቪክ ማህበራትም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ምርጫና የጸጥታና ደህንነትን በተመከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም ቦርዱ ከፌደራል መንግስትና ከክልሎች ጋር ስልጠናዎችን በመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ስራው ግን ከዚህ በተሻለ ፍጥነት መሰራት አለበት ሲሉም ገልጸዋል።

ችግሮች ሲከሰቱ የሚፈቱበትን መንገድ በመፈለግና በማሳሰብ ከመንግስት ጋረ አብሮ መስራት ያስፈልጋል ያሉት ዋና ሰብሳቢዋ፤ መረጃ ላይ የተመሰረተ ትንታኔ በመስጠት ስራዎች መሰራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ባለበት አካባቢ ምርጫ እንደማይደረግም ገልጸው፤ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ባለበት ቦታ ዜጎች በታማኝነት ምርጫ ያደርጋሉ ተብሎ እንደማይታሰብም ነው ያስታወቁት።

በትግራይ ክልልም በጸጥታው ዘርፍና በአስተዳደሩ ክፍል ከፍተኛ መሻሻል ሲመጣ ምርጫው እንደሚደረግ ገልጸው፤በክልሉ ለሚካሄደው ምርጫ ቅድመ ዝግጅት ከወዲሁ መጠናቀቁንም ጠቁመዋል።

የክልልነት ጥያቄዎች ሳይመለሱ ምርጫው ሊካሄድ ይችላል? ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄም የክልል ጥያቄዎች እሰከሚመለሱ ተብሎ ምርጫው እንደማይዘገይና ከምርጫው በፊትም ሆነ በኋላ ጥያቄው መቅረብ እንደሚችል ምላሽ ሰጥተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸውን አቤቱታዎችን በተመለከተ ምርጫ ቦርድ መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየሰራ እንደሚገኝና የስልጣን ወሰንነት እስሚገድበው ድረስ ቦርዱ ሃላፊነቱን በገለልተኝነት በመወጣት ላይ ይገኛል ብለዋል።

በፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆነው ግጭት በመቀስቀስ በአመጽ በመሳተፍና በግድያ ወንጀል የተጠረጠሩ አካለትን ጉዳይ በተመለከተ ምርጫ ቦርድ በቀጥታ ገብቶ መፍትሔ መስጠት እንደማይችልና የስራ ሃላፊነቱም እንደማይፈቅድለት ተናግረዋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀው “በምርጫ ብቻ” የማህበራዊ ሚዲያ የጥያቄ ተሳትፎ 1200 ገደማ ጥያቄዎች የተነሱበት ሲሆን ጥያቀዎቹን በመጭመቅ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ምላሽ ሰጥተውበታል።

ENA

Leave a Reply