የፊደራል አቃቤ ህግ በኦፊሳል ገጹ ይፋ እንዳደረገው ከባድ የውንብድና መፈጸማቸው በማስረጃና በሰው ምስክር የተረጋገጠባቸው የፖሊስ አባላት እያንዳንዳቸው በ13 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ወስኗል። ጥፋተኞቹ ጥፋታቸውን ማመናቸውን ተጠቁሟል።

ህግን ለማስከበር እንዲገለገሉበት የተሰጣቸውን የፖሊስ መኪና እና የደንብ ልብስ በመጠቀም ከባድ የውንብድና ወንጀል የፈፀሙት የፖሊስ ዓባላት በፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ የዐቃቤ ህግ ክስ እንደሚያስረዳው

1ኛ ተከሳሽ ረ/ ሣጅን መሀመድ ሰይድ እና 2ኛ ተከሳሽ ረ/ሣጅን ገመቹ አለማየሁ የተባሉት የፖሊስ አባላት ወይም ተከሳሾች የወንጀል ህግ አንቀፅ 32 /1/ሀ/ እና 671 /1/ለ/ ስር የተመለከተውን ድንጋጌዎች በመተላለፍ ሰኔ 27/2010 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ሲሆን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው” ሀይሌ ጋርመንት“ አካባቢ ዶላር አለን የሚገዛን ሰው አገናኙን በማለት የግል ተበዳይ ቢኒያም ሲሣይን ከላይ በተገለፀው ቦታ እንዲመጣ ያደርጋሉ።

ከዛ በኋላ የ4ኛ የዐቃቤ ህግ ምስክር ንብረት የሆነውን ቶዮታ ኮሮላ መኪና ፊት ለፊት የሰሌዳ ቁጥሩ ሊታወቅ ያልቻለና ለስራ እንዲገለገሉበት የተሰጣቸውን የፌደራል ፖሊስ ፒካፕ መኪና በማቆም እና መንገዱን በመዝጋት ተበዳይ ላይ ሽጉጥ በመደገን “እንዳትንቀሳቀስ ግንባርህን ነው የምንልህ” በማለት ተበዳይ በጥቁር ቦርሳ ይዞት የነበረውን ብር 1,500,000 (አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ ብር) ይዘው ሊሰወሩ ሲሉ በሌሎች የህግ አስከባሪ አካላት እጅ ከፍንጅ የተያዙ በመሆኑ በፈፀሙት ከባድ የውንብድና ወንጀል በዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎትም ተከሳሾቹ ጥፋታቸውን በማመናቸውና በመፀፀታቸው የዐቃቤ ህግን ዝርዝር የሰው፣ የሰነድ እና የኢግዚቪት ማስረጃዎች ማየት እና ማዳመጥ ሳያስፈልገው ችሎቱ ጥር 20/2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሾች ጥፋተኛ ናቸው ሲል ፍርድ በመስጠት ከዚህ በፊት የጥፋት ሪከርዶች የሌለባቸው እና በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ይሳተፉ እንደነበር በማረጋገጡ የቅጣት ማቅለያዎችን በመያዝ ተከሳሾችን ያርማል መሰል አጥፊዎችንም ያስተምራል ሲል እያንዳንዳቸው በ13 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል ።

Leave a Reply