የዓለም ምግብ ድርጅት ሠብዓዊ ድጋፍ፣ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አቀርባለሁ አለ፤ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች ሠብዓዊ ድጋፍ አግኝተዋል

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለትግራይ ክልል ሠብዓዊ ድጋፍ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት እንደሚያቀርብ አስታወቀ። በመቀሌ የምግብ ማከማቻ መጋዘን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን ለሁለት ወራት መመገብ የሚያስችል እህል መከማቸቱን መንግስት አስታውቋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር ዴቪድ ቤስሊን፣ በተባበሩት መንግስታት የሠብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚና የሠላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ዛሬ በመቀሌ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎችና የድጋፍ አሰጣጡን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። ዳይሬክተሩ ሚስተር ዴቪድ በትግራይ ክልል ከተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በኋላ የሠብዓዊ ድጋፍ ለማዳረስ የተለያዩ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በቦታው ተገኝተው የሠብዓዊ ድጋፍ አሰጣጡን መመልከታቸውንና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ማነጋገራቸውን ተናግረዋል። ሠብዓዊ ድጋፉን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለማዳረስ የመገናኛ አውታሮች ሁሌም ክፍት ሊሆኑና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ሊቀላጠፍ ይገባልም ብለዋል።

ተቋማቸው በክልሉ እየተደረገ ያለውን የሠብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እየደገፈ መሆኑንና በተለይም ከውጭ ተገዝተው የሚመጡ የምግብ እህሎች ከጅቡቲ ወደ መቀሌ በቀላሉ እንዲጓጓዙ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በትግራይ ክልል በርካታ ዜጎች የዕለት ደራሽ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ መንግስት ሁሉንም ማዳረስ አዳጋች ስለሚሆንበት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

በርካታ ህጻናትና እናቶችም የአልሚ ምግብ ድጋፍ የሚሹ በመሆኑ ይህም በስፋት ሊዳረስ እንደሚገባ ተናግረዋል። ለዚህ ደግሞ መንግስት የክሊራንስና ሎሎች ህጋዊ ጉዳዮችን ሊያመቻች ይገባል ነው ያሉት።

የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው መንግስት በትግራይ ክልል ሠብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች  ከተባበሩት መንግስታትና ከሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር እያደረሰ ነው ብለዋል። መቀሌ በሚገኘው መጠባበቂያ ምግብ ክምችት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ለሁለት ወራት የሚበቃ የምግብ ክምችት መኖሩን አስታውቀዋል።

የሠብዓዊ ድጋፍ ስርጭቱን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንና በ24 ወረዳዎች፤ ማህበረ ረድኤት ትግራይ ደግሞ በቀሪዎቹ 12 ወረዳዎች እያሰራጩ መሆኑ ተገልጿል። የዓለም ምግብ ፕሮግራም 400 ሚሊዮን ዶላር መድቦ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን የዕለት እርዳታ የሚሹ ዜጎች ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።

በተመሳሳይ ዜና –

በትግራይ ክልል 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች ሠብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉን የሠላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ። በክልሉ 800 ሺህ ዜጎች የአልሚ ምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ​ብለዋል።

በሠላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚልና በዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሊን የተመራ የልዑካን ቡድን በትግራይ ክልል በመንግስት እየተካሄደ ያለውን የሠብዓዊ ድጋፍ አሰጣጥ ዛሬ ተመልክቷል።

የልዑካን ቡድኑ በመቀሌ የሚገኘውን በፌዴራል መንግስት ማዕከላዊ መጋዘን ለሰብዓዊ ድጋፍ የተዘጋጀ እህልና በመቀሌ አቅራቢያ ኩዊሃ አካባቢ የሚገኘውን የሰብዓዊ ድጋፍ ማዕከል ጎብኝቷል።

የሠላም ሚኒስትሯ መንግስት ባደረገው የመጀመሪያ ዙር የዳሰሳ ጥናት በትግራይ ክልል ሠብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች መለየታቸውን ገልጸዋል።

የሠብዓዊ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ዜጎች እስካሁን 1 ነጥብ 7 ሚሊዮኑ ድጋፍ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። በተለይም በፍጥነት ድጋፍ ለሚሹ ሴቶችና ህጻናት አልሚ ምግብ እየተሰጠ ሲሆን ድጋፉ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር እየቀረበ ይገኛል ብለዋል።

በኢትዮጵያ መንግስት ወጪ ከውጭ አገር የተገዛ ስንዴ ትናንት ወደ መቀሌ ማዕከላዊ መጋዘን መግባቱንም ጠቁመዋል። በመቀሌ ማዕከላዊ መጋዘን በትግራይ ክልል ሠብዓዊ ድጋፍ ለሚያሻቸው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ለሁለት ወር የሚበቃ የምግብ ክምችት መኖሩንም ነው ወይዘሮ ሙፈሪያት የገለጹት።

አልሚ ምግብ ለሚሹ 800 ሺህ ወገኖችም ግዢ እየተከናወነ መሆኑንና የዛሬው ጉብኝት በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል ግዢው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በተጨማሪም የሠብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። መንግስት በትግራይ ክልል ሠብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች በተመለከተ የሁለተኛ ዙር የዳሰሳ ጥናት እንደሚያካሂድም አክለዋል።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሣ በበኩላቸው በትግራይ ክልል ሠብዓዊ ድጋፉን በተፋጠነ ሁኔታ ለማድረስ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ተቋቁሞ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ማዕከሉ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተወጣጡ ባለሙያዎችን ያካተተ እንደሆነ ገልጸዋል። በማስተባበሪያ ማዕከሉ አማካኝነት የሚመጣውን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች ለዜጎች እየደረሱ መሆኑንም ገልፀዋል።

ጉብኝቱ አጋር አካላት በትግራይ ክልል የሚያደርጉትን ድጋፍ የሚያጠናክሩበትን ሁኔታ እንደሚፈጥርም ነው ኮሚሽነር ምትኩ የጠቆሙት። በተያዘው ሳምንት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ ጋር በነበራቸው ውይይት በትግራይ ክልል ሠብዓዊ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች 80 በመቶውን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን መግለጻቸው ይታወሳል።

ENA

Leave a Reply