በትግራይ ክልል የጤና አገልግሎቶችን የማስቀጠልና ድንገተኛ ምላሽና ድጋፍ የመስጠት ስራ ተጠናክሮ መቀጠዑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የጤና ሚኒስቴር ከተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር አካላት እንዲሁም ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች እየተሰጠ ያለውን የድንገተኛ ምላሽና የጤና አገልግሎት ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በቅርብ ጊዜ ከተላከው ከ71 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድሃኒቶችና የህክምና ግብዓቶች ጨምሮ በመድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ የመቀሌ እና ሽሬ ቅርንጫፍ በአጠቃላይ ግምታቸው ከ 500 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ መድሀኒቶች እና የህክምና ግብዓቶች በክምችት ይገኛል።

በመሆኑም በየቀኑ ወደ ተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች ለሚገኙ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች እየተሰራጩ ይገኛሉ፡፡

እስካሁንም ከ70 በላይ ለሚሆኑ ጤና ተቋማት መሰራጨቱን ሚኒስቴሩ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ገልጿል።

በተጨማሪም ግምታቸው 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ የተለያዩ ክትባቶች የተሰራጩ ሲሆን በጤና ሚኒስቴር 12 አምቡላንሶች፣ 11 ለቢሮና ለመድሀኒት ማጓጓዣ አገልግሎት የሚውሉ ፒካፕ መኪኖች፣ 1 የቅዝቃዜ ሰንሰለት ያለው ተሸከርካሪ ለክልሉ የተላኩ ሲሆን 100 ኮምፕዩተሮች ለክልሉ ተሰጥተዋል፡፡

ለእነዚህ የመልሶ ማቋቋምና አገልግሎቶችን የማስቀጠል ስራዎች 37 ሚልዮን ብር እስከአሁን ለክልሉ ጤና ቢሮ የተላለፈ ሲሆን በያዝነው ሳምንት ተጨማሪ በጀት ለማስተላለፍ በሂደት ላይ ነው፡፡

የተለያየ የሞያ ስብጥር ያለው ከጤና ሚኒስትር፤ ከህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት እና ኤጀንሲዎች የተውጣጣ ቡድን ወደ ክልሉ በመሄድ ከክልሉ ጤና ቢሮ እና ከአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ቡድኑ ጋር እየሰራ ይገኛል፡፡

የኮቪድ ምርመራ እና ህክምና ለማስቀጠል የባለሙያዎች ቡድን ወደ ክልሉ ተልኮ ዳሰሳ ያደረገ ሲሆን የላቦራቶሪ ምርመራ እና የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ በጥቂት ቀናት ውስጥ በመቀሌ ከተማ አገልግሎት መስጠት ይጀመራል፡፡

የደም አቅርቦትን ለማጠናከርም 952 ዩኒት ደም ከክልሉ ደም ባንኮች የተሰራጨ ሲሆን 2803 ዩኒት ደም ደግሞ ከመቀሌ የበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች ተሰብስቧል፡፡

ከተለያዩ አጋር ድርጅቶችም የተለያዩ አልሚ ምግቦችና ለሴቶች ንጽህና የሚውሉ ግብዓቶችም ተሰራጭተዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ ጤና ተቋማት በከፊል ስራ ጀምረው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን ካሉት ሆስፒታሎች ውስጥ 46 በመቶ የሚሆኑት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

በቅርብ ጊዜያትም ሁሉም ጤና ተቋማት ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

ተፈናቅለው በተለያዩ ከተሞች ለሚገኙ ወገኖችም በብሄራዊ አደጋና ስጋት ኮሚሽን ከሚደረገው የምግብ ድጋፍ ጎን ለጎን ተንቀሳቃሽ የህክምና ቡድኖች የህክምናና የስርዐተ ምግብ ድጋፍ በተለይም ተጋላጭ ለሆኑ እናቶችና ህጻናት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

በሚንስትሮች የሚመራው ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አስተባባሪ ኮሚቴ በመቀሌ ከተማ ካደረገው ሁለት ዙር ምልከታና ውይይት በተጨማሪ፤ በጤና ሚኒስቴር ከተቋቋመው ግብረ ሃይል ውስጥ በሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ዓለምጸሀይ የተመራ ቡድን ያለውን የመልሶ ማቋቋም ስራዎች በተለያዩ ተቋማት በመዘዋወር የተመለከተ ሲሆን ከተለያዩ ስራ ኃላፊዎች ጋርም ውጤታማ ውይይት እና ድጋፍ አድርጓል፡፡

Via Ena

Leave a Reply