የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ሚና ተፈትሾ የመፍትሄ አቅጣጫ ይቀመጣል፤ የተለያዩ ውሳኔዎችም ይኖራሉ”

“ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሳው ቡድን የብልጽግና አስተሳሰብን ለማምከን ሲሰራ ቆይቷል…የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ሚና ተፈትሾ የመፍትሄ አቅጣጫ ይቀመጣል፤ የተለያዩ ውሳኔዎችም ይኖራሉ”አቶ ተስፋዬ በልጅጌ

ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያለመው ሀይል ከመተከል በመነሳት የህዝቦችን አብሮነት በመናድ የብልጽግና አስተሳሰብ መሬት ላይ እንዳይወርድ ሲሰራ መቆየቱን በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ አስታወቁ።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ኮንፍረስ ዛሬ በአሶሳ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

አቶ ተስፋዬ በኮንፍረስ መክፈቻ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት መድረኩ መተከልን ጨምሮ በክልሉ የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን ገምግሞ በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ ነው።

“በኮንፍረንሱ የክልሉ የጸጥታ ችግር በጥልቀት ተገምግሞ መዋቅሩን በማጥራት እንደገና የመገንባት ስራ ይከናወናል” ብለዋል።

ኢትዮጵያን የማፈራረስ ተልዕኮ ያነገበው አፍራሽ ሀይል መተከልን ዋነኛ የጥፋት መነሻ አድርጎ እየሠራ መሆኑን ገልጸው በዚህም የህዝቦችን አብሮነት የሚንድ ሀሳብ በመርጨት የብልጽግና አስተሳሰብ መሬት ላይ እንዳይወርድ ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

“መተከልን ጨምሮ በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ሚና ተፈትሾ የመፍትሄ አቅጣጫ ይቀመጣል፤ የተለያዩ ውሳኔዎችም ይኖራሉ” ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው የመተከል ጉዳይ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው አጀንዳ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፌዴራልና የክልሉ መንግስታትም የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመመለስ የመፍትሄ እርምጃ እየወሰዱ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

ለጠፋው ህይወትና ለወደመው ንብረት አንዳንድ የክልል የስራ ሃላፊዎች ተሳትፎ እንዳለበት ገልጸው፤ “በኮንፍረንሱ ላይ ዘላቂ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ሁሉም የሚሳተፉበት ውይይት ይደረጋል” ብለዋል።

ENA

See also  ከ65 ሚሊየን ብር በላይ ሰርቀዋል የተባሉ ሃላፊዎች ላይ ፍርድ ተሰጠ

Leave a Reply