የኮሮና ተሐዋሲ ክትባቶች ሂደትና መሻሻል

የኮሮና ተዋህሲ ከተከሰተ ካላፈው አንድ አመት ወዲህ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መድሃኒትና ክትባት ለማግኘት ተመራማሪዎች በርካታ ሳይንሳዊ ምርምሮችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።ጥቂቶቹም ውጤታማ መሆናቸው እየተገለፀ ነው።

የኮቪድ-19 በሽታ በወረርሽኝ ደረጃ መከሰቱንና የዓለም የጤና ስጋት መሆኑ፤  በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ይፋ ከተደረገ  በጎርጎሮሪያኑ ያለፈው ጥር 30 እነሆ ድፍን አንድ ዓመት ሆኖታል።ይህንን ወረርሽኝ ለመከላከል የሚያስችል ክትባት ለማበልፀግ በዓለም ዙሪያ በርካታ የምርምር ቡድኖች ሳይንሳዊ ጥናቶችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡ ያም ሆኖ እስካሁን ድረስ የሙከራ ክትባቶቻቸውን ወደ ሦስተኛው ዙር ክሊኒካዊ ሙከራ ከፍ ማድረግ የቻሉት ጥቂት የምርምር ቡድኖች ብቻ  ናቸው። ከነዚህም መካከል የጀርመኑ ባዮንቴክና የአሜሪካው የፊዘር ኩባንያ ያመረቱት እንዲሁም  የሞደርና  ክትባቶች ይጠቀሳሉ።ባለፈው ሳምንት ደግሞ «አስትራዜኒካ» የተባለ ሌላ የኮሮናተዋህሲ ክትባት በአውሮፓ ህብረት ተቀባይነትን አግኝቷል።

የአውሮፓ መድኃኒቶች ኤጄንሲ በቅርቡ እንዳስታወቀው  «አስትራዜኔካ» ለተባለ  ኮቪድ-19 ክትባት ፈቃድ ሰጥቷል ።ይህ  በብሪታንያ የተመረተ ክትባት ከፒፊዘርና ባዮንቴክ እንዲሁም የሞደርና ክትባቶች ቀጥሎ በአውሮፓ መድኃኒቶች ኤጀንሲ ስራ ላይ እንዲዉል  የተፈቀደለት ሦስተኛው የኮቪድ -19 ክትባት ነው።ክሊኒካዊ ሙከራዎች እንዳመለከቱት ክትባቱ ከ18 ዓመት ዕድሜ በላይ ለሆኑ ሰዎች ኮቪድ-19ን ለመከላከል ደህንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ  መሆኑን  ኤጀንሲው ገልጿል ፡፡ ክትባቱ የተሰራበት ቴክኖሎጅም ከቀደሙት የተለዬ መሆኑን የኤጀንሲው ዳይሬክተር ኤመር ኩክ ገልፀዋል።

Coronavirus - Astrazeneca Impfstoff

«የአስትሮ ዜኒካ ክትባትን ለማፅደቅ ሀሳብ ያቀረብነው፤ ኮቪድ-19ን በመከላከል ረገድ በክትባቱ ላይ  ደህንነትን ከሚያረጋግጥ መገለጫ ጋር የቀረቡ አስተማማኝ መረጃዎችን መሰረት አድርገን ነው። የመጀመሪያዎቹ ሁለት  ማረጋገጫ የተሰጣቸው ክትባቶች «ሜሴንጀር አር ኤን ኤ» በተባለው ዘዴ የተሰሩ ሲሆን፤የአስትሮዜኒካ ግን «ዲኖ ቫይረስ»በተባለ ሌላ ቴክኖሎጅ የተሰራ ነው። ይህ ማለት ክትባቱ የተሰራው የ«ዲኖ» ተዋህሲ ቤተሰብ የሆነ ሌላ ተራ ተዋህሲን በመጠቀም፤የኮቪድ-19ን የኮሮና ተዋህሲ የተወሰነ የፕሮቲን ክፍል እንዲይዝ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።»

ያም ሆኖ የአውሮፓ ህብረት ክትባቱ በዕድሜ ለገፉ  ሰዎች  ውጤታማ ስለመሆኑ ጥርጣሬዎች አሉት።የአውሮፓ ህብረትን ስጋት የጀርመን የክትባት ኮሚሽንም ይጋራል።ኮሚሽኑ፤ ይህንን በሚመለከት በቂ መረጃ ባለማግኜቱ  ከ 65 ዓመት እና ከዛ በላይ ለሆኑት ሰዎች ክትባቱን እንዲጠቀሙ መምከር እንደማይችል ተናግሯል። የአውሮፓ የመዳህኒት ኤጀንሲ ባለሙያዎች ግን ክትባቱ  ከ55 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎችም ውጤታማ መከላከያ ሆኖ ያገለግላል ይላሉ።ይህንን  የባለሙያዎች ምክር ተከትሎም  የአውሮፓ ኮሚሽን  ክትባቱን 27ቱ የህብረቱ አባል ሀገራት እንዲጠቀሙ የመጨረሻውን ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡ ክትባቱ በመደበኛ ማቀዝቀዣ ውስጥ ማስቀመጥ የሚቻል በመሆኑ፤ኢመር ኩክ እንደሚሉት ለማጓጓዝ ምቹ ነው።  

See also  “ዳጉ” ስውሩ ጦር - የፕሮፓጋንዳ ምች

« ክትባቱ ከ«ኤም አር ኤን ኤ» ክትባቶች ጋር ሲነፃጸር ለማስቀመጥም ይሁን ለማጓጓዝ ምቹ ነው።ይህም ክትባቱን በብሪታንያም ይሁን በአውሮፓ አባል ሀገራት ለማሰራጨት የሚደረገውን ስራ ቀላል ያደርገዋል።»

በሌላ በኩል በአሜሪካ ኩባንያ የተመረተ ኖቫቫክስ የተባለ ተስፋ ሰጪ ክትባት ሰሞኑን እውቅና ለማግኜት እየተጠባበቀ መሆኑ ተገልጿል።ይህ ክትባት በክሊኒካዊ ሙከራ 89 ነጥብ 3 ውጤታማ ሲሆን፤በብሪታንያና በደቡብ አፍሪቃ የታየውን የተለወጠ የኮሮና ተዋህሲ ጭምር የሚከላከል መሆኑን ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል።ከዚህ በተጨማሪ በቻይና፣ በሩሲያ፣ በእስራኤል፣ በህንድ፣በአውስትራሊያና ሌሎች ሀገሮች የኮቪድ-19  ክትባት ማግኘታቸውን ሲገልፁ ቆይተዋል። 

በአጠቃላይ የኮሮና ተዋህሲ ከተከሰተ ካላፈው አንድ አመት ወዲህ እነዚህን አዳዲስ ክትባቶች ጨምሮ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መድሃኒትና ክትባት ለማግኘት ተመራማሪዎች በርካታ ሳይንሳዊ ምርምሮችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው የኮሮና ወረርሽኝ በተከሰተ ሰሞን ቢያንስ 246  ጥናቶች  ነበሩ።በጎርጎሪያኑ 2021 ዓ/ም እስከ ጥር አጋማሽ  ባለው ጊዜ ደግሞ በድርጅቶችና በተቋማት 235  ምርምሮች እየተደረጉ ነው። ከነዚህ ውስጥ ከ100 በላይ የምርምር ቡድኖች ደህንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ  የኮቪድ-19 ክትባት ለማዘጋጀት እየሞከሩ ነው። ከ50 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ክሊኒካዊ ሙከራዎችን ጀምረዋል። 

ይሁን እንጅ ከነዚህ በርካታ ምርምሮች ውስጥ ማረጋገጫ ያገኙት ጥቂቶች ናቸው።ምክንያቱም ተዋህሲውን የሚከላከል ክትባት ለማግኘት በአማካኝ ከ10 እስከ15 ዓመታትን የሚወስድ ሳይንሳዊ ምርምርን የሚጠይቅ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ለተዋህሲው ክትባት ማግኘት ቀላል አልሆነም።ባለሙያዎች እንደሚሉት የክትባቱ ውጤታማነትና ስኬታማነትም ወሳኝ ነው።ለመሆኑ የክትባቱ ስኬታማነትና ውጤታማነትስ በምን ይለካል?

Deutschland | Coronavirus | Berlin öffnet drittes Impfzentrum

«ሁለቱም ቃላት ክትባት  ምንያህል በጥሩ ሁኔታ ሰዎችን ከበሽታ መከላከል  ይችላል የሚለውን ያሳያሉ። ስኬታማነት ክትባቱ በክሊኒካል ሙከራ ጊዜ  የተለዬ ቁጥጥር ባለበት አካባቢ ያለውን ውጤት የሚያሳይ ነው። ነገርግን ውጤታማነት የሚገልፀው ክትባቱ በእውነተኛው ዓለም ሰዎችን እንዴት ይከላከላል የሚለውን ነው።»

ያም ሆኖ የወረርሽኙ እያደረሰ ያለው ጉዳት ቀላል ባለመሆኑ  ክትባቱን በአጭር ጊዜ ለማድረስ ብዙ የምርምር ቡድኖች  ሩጫ ላይ ናቸው። አብዛኛዎቹ  ጥናቶች ግን አሁንም ድረስ ቅድመ ሁኔታ ውስጥ፤ ማለትም በእንስሳት አማካኝነት ክሊኒካዊ ሙከራ እየተካሄደባቸው ነው። እነዚህ ምርምሮች ስኬታማ ከሆኑ በሰዎች ለመሞከር ወደ ሚያስችል ክሊኒካዊ ሙከራ ሊሸጋገሩ ይችላሉ።

See also  ኢትዮጵያን ሊበላ የተነሳው "አውሬ" ሴራ ተጋለጠ፤ "30ሺህ ሳምሪ ሱዳን ታጥቆ ቀዳዳ እየፈለገ ነው

አንድ ክትባት ውጤታማነቱና ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ  ሦስት ክሊኒካዊ የሙከራ ደረጃዎችን ማለፍ ይጠበቅበታል።እነዚህ ሙከራዎች ስኬታማ ከሆኑ አንድ ኩባንያ ፈቃድ ለማግኘትና  ህብረተሰቡ እንዲጠቀምበት ለማድረግ ለሚመለከተው የጤና ባለስልጣን መስሪያ ቤት ማመልከት ይችላል።በዚህ መሰረት የሰሞኑን አስትራዚኒካ ጨምሮ የባዮንቴክና የፌዘር እንዲሁም የሞደርና  ክትባቶች ሙከራውን በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቅ ከአውሮፓና ከአሜሪካ  የመድሃኒት ድርጅቶች እስካሁን ማረጋገጫ ያገኙ ክትባቶች ናቸው።

ተመራማሪዎችም በዚህ ሁኔታ ማረጋገጫ ያገኙ ክትባቶችን   የወሰዱ ሰዎችን ለውጥ መከታተል ይጀምረዋል።በዚህ የክትትል ሂደትም ባለሙያዎች እንደሚሉት ከጥቂት የጎንዮሽ ጉዳት ውጭ  ያጋጠመ ችግር  የለም።

«ከሁለት እስከሶስት ቀናት የሚቆዩ የተለመዱ የጎንዮሽ ጉዳቶች ማለትም ክትባቱ ያረፈበት ቦታ ማበጥና ትንሽ ህመም ፣ ድካም፣ትኩሳት፣ ራስ ምታት እንዲሁም የመገጣጠሚያና የጡንቻ  ህመሞች ሊኖሩ ይችላሉ። በአጠቃላይ እነዚህ አይነቶቹ የጎንዮሽ ጉዳቶች ብዙ አይቆዩም።ሌላ ጉዳትም አያመጡም።ህይወት የሚያሳጣ በሽታን የሚከላከል ክትባት ከማግኘት አኳያም ልንቀበላቸው የሚገቡ ናቸው።»

Belarus Minsk Impfung Covid-19

 የኮቪድ-19  ክትባትን ለማግኘት ተመራማሪዎች 12 የተለያዩ ዘዴዎችን እየተከተሉ ሲሆን፤ መረጃዎች እንደሚያሳዩት አብዛኛዎቹ  ጥናቶች የበሽታ አምጪ ተዋህሲን ከመጠቀም ይልቅ በውስጣቸው ያለውን ፕሮቲን ንዑስ ክፍል የመጠቀም ዘዴን ይከተላሉ።ያ ፕሮቲን በከፍተኛ መጠን በክትባት መልክ  የሚሰጥ ሲሆን ዓላማውም የሰዎች  የበሽታ መከላከል ስርዓት ፈጣንና ጠንካራ ምላሽ እንዲሰጥ ለማድረግ ነው።የምርምር ቡድኖች  የክትባት መከታተያ  ጥናት መረጃ እንደሚያሳየው በዚህ ሁኔታ የተመረቱ የኮቪድ-19 ክትባቶች በአዲሱ የጎርጎሪያኑ 2021 ዓ/ም ጥር ወር መጨረሻ ድረስ በዓለም ላይ ከሶስት መቶ ሺህ በላይ በሆኑ ፈቃደኛ ሰዎች ላይ አምስት የምርምር ቡድኖች ሙከራ አድርገዋል።

በሌላ በኩል  በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህመምና ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለሞት የዳረገውን ወረርሽኝ ለመከላከል በአሁኑ ወቅት ሀብታም ሀገራት ክትባቶቹን በገፍ መግዛት ይዘዋል።በአውሮፓና በአሜሪካ የሚገኙ  በርካታ ሰዎችም በቅርቡ  አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ፈቃድ የተሰጣቸውን ክትባቶች በመውሰድ ላይ ናቸው። ያም ሆኖ በክትባቱ ደህንነት ፣ ውጤታማነት እንዲሁም ለአፍሪቃውያን ተደራሽ ባለመሆኑ  ዙሪያ የሚነሱ ብዙ ጥያቄዎች መልስ አላገኙም።የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዚዳንት ሲርል ራማፎዛም ይህንኑ ያሳስባሉ።

«ክትባትን ሀገራዊ  ከማድረግ አዝማሚያ ይልቅ፤ህዝባችንን ከወረርሽኙ ለመጠበቅ በአንድ ላይ በመስራት የተሻለ ነው።ይህ የብሪታንያን ህዝብ ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም ከተዋህሲው መከላከል ያስችላል።የዓለም ደህንነት እስካልተጠበቀ ድረስ ማንም ደህንነቱ የተጠበቀ ሊሆን አይችልም።»ብለዋል።

See also  ፖሊስ አዲስ አበባ "በጁንታው ደጋፊ ንግድ ቤቶች" ድንገተኛ አሰሳ አካሂዶ መሳሪያ፣ ወታድራዊ ትጥቅ፣ሀሺሽ፣ገንዘብ፣የትህነግ የስብሰባ ቃለ ጉቤ ... አገኘ መረጃው ተያይዟል

ፀሐይ ጫኔ ማንተጋፍቶት ስለሺ dw amharic

    Leave a Reply