የህወሃት መወገድ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም ወሳኝ ነው!!ጠ/ሚ አቢይ አህመድ

ለኢትዮጵያም ሆነ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም መስፈን የህወሃት መወገድ አስፈላጊ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክት ሲንዲኬት ለተባለው ድረገጽ በላኩት ጽሁፍ መንግስት በትግራይ ክልል ያካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ የትግራይን ህዝብ ከታሰረበት የህወሃት አምባገነናዊ አገዛዝ ያላቀቀና ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢም ተስፋን ያሳየ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

“የህወሃት መወገድ በኢትዮጵያ ሰፍኖ የቆየው የሙስና ድርጊት እና አምባገነናዊነት ከማጥፋቱም ባሻገር አንድነት፣ እኩልነት፣ ነጻነትና የዴሞክራሲ ተስፋን አሳይቷል” ብለዋል። በምስራቅ አፍሪካ አገሮች ሲስተዋል የነበረው ጎሳን መሰረት ያደረገ ሽኩቻ ከህወሃት ጋር አብሮ የተወገደ መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር አቢይ፤ በህግ ማስከበሩ ሂደት የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

“ለሰዎች ሃሳብ ቦታ መስጠት ያስፈልጋል” የሚለውን የቶማስ ጃፈርሰን አባባልን በመጠቀም መንግስት በክልሉና በክፍለ አህጉሩ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ሰዎች እንዳይጎዱ ጥረቶችን ሲያደርግ እንደቆየ አስታውሰው፤ ለዚህ ጥረት አጋዥ እንዲሆንና ህብረተሰቡ እንዲጠቀም ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ ማቅረባቸውን ጠቁመዋል።“የየትኛውም አገር መንግስት የመከላከያ ሰራዊት ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ጥቃት ተፈጽሞበት እጁን አጣጥፎ ሊቀመጥ አይችልም” ሲሉ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ስራ የኢትዮጵያን ዜጎች ከማንኛውም ውስጣዊና ውጫዊ ጠላቶች መጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።በህወሃት ጥቃት ምክንያት በትግራይ የተደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻ በጣም በአጭር ጊዜ በስኬት መጠናቀቁን አስረድተዋል።

በከፍተኛ ጥንቃቄ በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ውጤታማ መሆን ቢቻልም በዜጎች ላይ የደረሰው ሞትና መፈናቀል እሳቸውንም ሆነ ሰላም ፈላጊውን ህብረተሰሰብ በእጅጉ ያሳዘነ መሆኑት ተናግረዋል።የአለም አቀፉን ማህበረሰብ በማስተባበር በትግራይ ያለው ሰቆቃ እንዲያበቃና አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግ መንግስት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራበት እንደሆነም ገልጸዋል። የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የህወሃትን ምንነት ተረድቶ ድርጊቶቹን ቢያወግዝም በህወሃት መሪነት የተደረጉ ብሄር ተኮር ግጭቶችን፣ ሰብአዊ መብት ረገጣዎችን፣ ግድያዎችንና ሰዎችን የማጥፋት ወንጀሎችን ላለማየት አይናቸውን የጨፈኑ ጥቂቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የተለያዩ አካላት ህወሃት ከሌለ ኢትዮጵያ እንደዩጎዝላቪያ ተበታትና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የቀውስ ማእከል ትሆናለች የሚል ሊሆን የማይችል ትንቢት ሲናገሩ እንደነበርም አስታውሰዋል።በብሔረሰብ ክፍፍል ላይ የተመሠረተ አገዛዝ ብዙም ሊዘልቅ እንደማይችልና ሰዎች የዘር፣ የጎሳ እና የሃይማኖት አመጽን ለረጅም ጊዜ ታግሰው አብረው መኖር እንደሚችሉ ብዙ ማሳያዎች እንዳሉም ገልጸዋል። ከአመት በፊት እርሳቸው አባልና መሪ ሆነው የቆዩበት ኢህአዴግ በህዝብ ግፊት ለውጥ እንዲያመጣ ሲገደድ ህወሃት በእንቢተኝነቱ ጸንቶ መቆየቱን ያስታወሱት ዶክተር አቢይ፤ “ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ብሄርን፣ ሃይማኖትንና ዘርን መሰረት ያላደረገ አስተዳደር እንዲፈጠር አስችሏል” ብለዋል።

ህወሃት በክልሉ ሲያስተገብረው የቆየውን ከፋፍሎ የመግዛት የአስተዳደር ዘይቤን በኤርትራና በሌሎች አጎራባች አገሮች ላይ ለመተግበርና አገራቱን ለማፈራረስ በመሻት የውክልና ጦርነቶችን ሲያካሂድ እንደነበረ ገልጸው፤ “ህወሃት በመወገዱ የአፍሪካ ቀንድና ኢትዮጵያ ሰላምና አካታች የልማት ድላቸውን እንዲያጣጥሙ አስችሏል” ብለዋል።

አዲሲቷ ኢትዮጵያ በውስጥ በሁሉም ዜጎችና ቡድኖች ዘንድ እኩልነት የሰፈነባት በውጭ ደግሞ ጎረቤቶቿን የያዘችና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር እየሰራች መሆኗን አመልክተው፤ ከኤርትራ ጋር የየተደረሰው የሰላም ስምምነት ለዚህ አስረጂ መሆኑን አንስተዋል።ስምምነቱ ለ20 አመታት በሰላምና በጦርነት መካከል የነበረውን የሁለቱን አገሮች ሁኔታ ከስሩ የቀየረና ኤርትራን ለምስራቅ አፍሪካና ከአለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያስማማ ከመሆኑም በላይ በድንበር አካባቢ ያሉ ህዝቦችን ከጦርነት ዳመና ሰጋት ያላቀቀ እንደሆነ አብራርተዋል።ለውጡ በውስጣዊ ችግሮቿ የምትናጠውን ሱዳንን ጨምሮ ለበርካታ የኢትዮጵያ አጎራባች አገሮች እፎይታ የሰጠ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ትርጉም – (ኢዜአ)

    Leave a Reply