አብን፣ መኢአድ እና ባልደራስ በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ተቀናጅተው የመቅረብ እድል የላቸውም

አብን፣ መኢአድ እና ባልደራስ በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ተቀናጅተው የመቅረብ ዕድል አላቸው? የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት( መኢአድ) እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በቀጣዩ 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ጥምረት ሊፈጥሩ ስለመሆናቸው ኢትዮ ኤፍኤም የአብን ምክትል ሊቀመንበር እና የምርጫ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ የሱፍ ኢብራሒምን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

ጥምረቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤቶች የጋራ እጩዎችን ማቅረብ እና ሌሎች የፖለቲካ ስራዎችን እንደ አንድ ፓርቲ ለማከናወን እንደሚያስችልም በዘገባው ተጠቅሷል። ይህን ዘገባ ተከትሎ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሶስቱ ፓርቲዎች በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ተቀናጅተው ሊቀርቡ እንደሆነ የሚገልጹ ጽሁፎች ቀርበዋል፣ ትንታኔዎች ተደምጠዋል። የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 በአንቀጽ 1 እና ሁለት ላይ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለተወሰነ ጊዜ እና በተወሰኑ ጉዳዮች ዙሪያ ተቀናጅተው እንደ ሁኔታው በአገር አቀፍ ወይም በክልል ደረጃ ሊንቀሳቀሱ እንደሚችሉ የደነገገ ሲሆን “ለመቀናጀት የፈለጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄያቸውን የጠቅላላ ምርጫ ወይም የአካባቢ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ከመውጣቱ ከሁለት ወራት በፊት በጽሑፍ ለቦርዱ ማቅረብ አለባቸው” ይላል።

በአዋጁ መሰረት ሶስቱ ፓርቲዎች በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ተቀናጅተው የመቅረብ እድል የላቸውም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሳምንታት በፊት የ6ኛውን አገር ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። ከዚህ ጋር በተገናኘ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ባለፈው ሐሙስ በቦርዱ የትዊተር ገጽ ከተከታዮች ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት የመቀናጀት ጊዜ ማለፉን አዋጅ ቁጥር 1162/2011ን በመጥቀስ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ቼክ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የጠየቃቸው የመኢአድ ፕሬዝደንት አቶ ማሙሸት አማረ ፓርቲዎቹ ጥምረቱን በተመለከተ የሚያደርጉትን ውይይት ከመቋጨታቸው በፊት ምንም ማለት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።#FactCheck Exclusive

    See also  TPLF destroys schools that accommodate 1 mln Students

    Leave a Reply