መንግስት አምባሳደሮች በተመደቡበት አገራት ብሄራዊ ጥቅምን አስመልክቶ እንደ ሰራቸው መጠን ሊገመግም ነው

የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ አገራት የሚገኙ ዲፕሎማቶች የአገራቸውን ጥቅም አስመልክቶ እንደ ስራቸው መጠን ሊገመግማቸው መሆኑ ተሰማ። መንግስት ዲፕሎማቶቹ የአገር ብሄራዊ ጥቅምና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ ደካማ ሆነው ሳለ እርምጃ አለመውሰዱ በድክመት ሲገለጽበት መቆየቱ ያታወሳል።

ለረዠም ዓመታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሃላፊነት ቦታ የተቀመጡት የህወሃት አመራሮች በመሆናቸውና የዚሁ ዘርፍ አካል የሆነው የዲፕሎማቶች ምደባ በትህነግ አማካይነት ይከናወን ስለነበር መንግስት ይህንን መቀየር እንዳለበት የሚያምኑ ” በተለይ ቁልፍ በሆኑ አገራት መንግስት ዲፕሎማቶቹን ሊመረመርና ብቁ ዜጎችን ሊመድብ ይገባል” የሚል አስተያየት በተለያዩ ሚዲያዎች ሲያቀርቡ ነበር። በርካታ ጽሁፎችም ቀርበዋል።

ከለውጡ በፊትም ሆነ በሁዋላ ከሁሉም በላይ መከራከሪያ ሆኖ የቆየው የብቃት ጉዳይ ነበር። እንደ አለቃ ጸጋዬ አይነት ሰዎች አምብሳደር ሆነው ሲሾሙ ይህ ተቃውሞ የገነነ ነበር። ከዛም በላይ አምባሳደርነት የማሸሺያና የማግለያ እንዲሆም የመጦሪያ ቦታ ተደርጎ መወሰዱ አገሪቱን የጎዳት እንደሆነ ሰፊ መግባባት የተፈጠረበት አሰራር ሆኖ ቆይቷል። መጠነኛ መሻሻል ቢያሳይም ቀደም ሲል የተሾሙትም ሆነ አሁን አዲስ ሹመት የተሰጣቸው አምብሳደሮች ላይ ማስተካከያ እንዲደረገ በስፋት የሚቀርበውን ትችት ያዳመጠ የመሰለው መንግስት ሁሉንም ዲፕሎማቶቹን ሊገመግም እንደሆነ ተሰምቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 እንዳለው ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ እየገጠማት ያለዉን የተዛባ አመለካከት ለማስረዳት ሁሉም ድፕሎማቶች ስለ አገራቸዉ ብሄራዊ ጥቅም በትኩረት እንዲሰሩም ቢሰጥም የተወሰኑቱ ስራቸውን በአግባቡ አልተወጡም።

የተወሰኑ ድፕሎማቶች በዓለም አቀፍ መገናኛዎች ጭምር በመቅርብ በኢትዮጵያ ስላለዉ ሁኔታ እንዲሁም ስለ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እያስረዱ ቢሆንም አብዛኞቹ ግን ብዙ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋልም ተብሏል፡፡

የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለ አገራቸዉ ብሄራዊ ጥቅም የተሸለ አፈፃፀም የሰሩና ያልሰሩ ዲፕሎማቶችን በቁጥር ጭምር በመያዝ እንደሚገመግምም ከሚኒስቴሩ ያገኘዉ መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያን ወክለዉ በተለያዩ አገራት የሚገኙ የዲፕሎማት ማህበረሰቦች ባገኙት አጋጣሚ በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እና በማህበራዊ ሚዲያዎችም ጭምር የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግንዛቤ እንዲኖረዉ በትኩረት እንዲሰሩም ጥሪ ተደርጓል፡፡

See also  የከዱት ዲፕሎማት በአማራ ክልል "1 ለ200" የህቡዕ አደረጃጀት አመራር መሆናቸው ተደርሶበት ነበር

ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ አገራት የሚኖሩ የዲያስፖራ ማህበረሰብ እና ምሁራን የአገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ ብዙ ስራዎችን ሊሰሩ ይገባል ተብሏል፡፡

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በነበረዉ የህግ ማስከበር ሂደት ጋር ተያይዞ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የተዛቡ መረጃዎችን እንደያዘ ያስታወቀዉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እዉነታዉን ለማስረዳት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

ከህዳሴ ግድብ እና ከኢትዮ ሱዳን የድንበር ዉዝግብ ጋር ተያይዞም ዲፕሎማቶች፤ ምሁራን፤ ዲስፖራዎች፤ እና የአገር ዉስጥ ሚዲያዎች ጭምር ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለ አገራቸዉ ተጨባጭ ሁኔታ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት አለባቸዉ ተብሏል፡፡

    Leave a Reply