“የኤርትራ ወታደሮች በጦርነቱ ተሳትፈዋል” ሲል ኢዜማ ሪፖርት አቀረበ

ኢዜማ በርዕስ ከፋፍሎ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ኤርትራ ሰራዊቷን ማዝመቷንና የህወሃት ሃይልን መውጋቷን ይፋ አደረገ። በማይክድራ ሪፖርቱ ግርግጌ በግልጽ እንዳስቀመጠው ” የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት” ሲል የገለጸው ሃይል ከሌሎች በስም ከጠቀሳቸው አደረጃጀቶች ጋር አብረው ነው ህወሃትን የወጉት። በዚህም ጦርነቱ ሊወስድ የነበረው ጊዜ እንዳጠረም አመልክቷል። ኢዜማ እጅግ እያነታረከ ያለውንና ትህነግ ዳግም ነብስ እንዲዘራ የሚደረገው ዘመቻ አንኳር የሆነውን ጉዳይ ጦርነቱ ከተካሄደ ወራት በሁዋላ ይህንን ጉዳይ አንስቶ ምስክር ለመሆን የመወሰኑ ግብ ምን እንደሆነ እንዳልገባቸው ሪፖርቱን ተከትሎ አስተያየት እየተሰጠ ነው። ጉዳዩ ኢዜማን ዋጋ እንደሚያስከፍለው ተጠቁሟል።

“የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት፣ የአካባቢው ሚሊሺያ አባላት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና እንደ ግለሰብ የታጠቁ ነዋሪዎች በጋራ ተቀናጅተው በመሰለፍ የሕወሓትን ኃይል በመፋለማቸው ጦርነቱ ሊወስድ ከሚችለው ጊዜ ባነሰ መቋጨቱን ነዋሪዎች አስረድተዋል” ያለው ኢዜማ በማይካድራ ጉብኘት ያደረጉት አባላቱ እንዳረጋገጡት የአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም ሌላ ስጋት አለባቸው።

ሪፕርቱ የኤርትራ ወታደሮች ባይደርሱ አስከፊ ቀውስ ሊደርስ ይችል እንደነበር ጠቁሞ የነዋሪዎቹን ስጋት ሲገልጽ ” … የሱዳን ጦር ሊመታን ይችላል፤ ‹‹ሳምሪ›› የሚባለው አደረጃጀት ሙሉ ለሙሉ ስለመጥፋቱ እርግጠኞች ስላልሆንን በድጋሚ ሊያጠቃን ይችላል፤ በየአካባቢው ተቆርጦ የቀረው የሕወሓት ታጣቂ ቡድን ባልታሰበ ጊዜና ሁኔታ ጥቃት ሊፈፅምብን ይችላል” በማለት ነው። አያይዞም እነዚህኑ በስም ፣ በብዛት ወይም በብሄር ያልጠቀሳቸውን ነዋሪዎች ጠቅሶ ” በአማራ ክልል አስተዳደር በኩል የአድሎዊነት ስሜት እየተስተዋለ ስለሆነ ስጋት ውስጥ ወድቀናል በማለት ነዋሪዎች ያለባቸውን ስጋት ጠቁመዋል” ሲል የኢዜማ ሪፖርት ያትታል። የአማራ ክልል ለምን? እነማን ላይ? እንዴት አይነት በደል እንደሚፈጽም በሪፖርቱ አልተብራራም።

ኢዜማ በመቀለ ጉብኝቱም ሆነ በሁመራ አካባቢ አደረኩ ባለው ማጣራት የአገር መከለከያ ላይ ስለተፈጸመው ወንጀል የትግራይ ነዋሪዎችን ጠይቆ ምን እንዳሉት በዝርዝር አልተናገረም። የራሱንም እይታ በሪፖርቱ አላካተተም።

ዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የዩኒዘርስቲ መምህር ” ኢዜማ በዚ ሪፖርቱ ዋጋ ይከፍላል” ብለዋል። አያይዘውም ከሶስት ወር በሁዋላ ሄዶ ዓለም መንግስትን ወጥሮ በያዘበት ጉዳይ ላይ መረጃ መስጠት ፖለቲካሊ ስህተት መሆኑን ጠቁመዋል። ከዛም በላይ ” ከማእከላዊ መንግስትም ሆነ ከአማራ ክልል ጋር ያለው ግንኙነት ሊበላሽ ይችላል የሚል ግምት አለኝ። ተጋራቸው ስህተት እንደሆን ከዛሬ ማታ በሁዋላ ሪፖርቱ ለፖለቲካ ግብዓት ሲውል ያዩታል። በትግራይ ያላቸውን ስም ለማደስ ከሆነ መንገዱ ይሄ አይደለም” ሲል ተናግረዋል።

See also  የአፍሪካና የአውሮፓ ህብረት ሀገራት አሸባሪው ትህነግ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ተጠየቀ -"ስልጣን ከያዘ ጀምሮ የፈጸመው ወንጀል ይጣራ"

የተለያዩ በስም የጠቀሳቸውን ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሰፈሩ ተፈናቃዮችን እንደጎበኘና የተለያዩ ወጣቶችን እንዳናገረ የጠቆመው የኢዜማ መግለጫ

  • በኤርትራ ወታደሮች ፈፀሙት ያሉትን አሰቃቂ ጥቃቶች ገልጸዋል፣
  • በትግራይ ሕዝብ ላይ ከ40 ዓመት በላይ ተጭኖ የቆየ ሥርዓት በቅርቡ ከጫንቃው ቢነሳም ሕዝቡን በፍጥነት ማሳመንና ወደ ቀድሞ ሕይወት ለመመለስ ጊዜ ስለሚፈልግ የመንግሥት ታጋሸነት እንደሚያስፈልግ፣
  • በትግራይ በየ20 ዓመቱ ጦርነት እየተቀሰቀሰ ልጆቿን የምትገብርበት ሁኔታ መቀጠሉ እንደጎዳቸው በምርጫ የሚያምን ትውልድ መፈጠር እንደሚያስፈልግ፣
  • የሕውሓት አመራሮች ተመልሰው ይመጣሉ በማለት ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች እንደአሉ፡፡ በተለይ ወጣቶቹ ከዚህ ስሜት እንዲወጡ ጊዜያቸውን በሥራ እንዲያሳልፉ ማድረግ እንደሚገባ፣
  • አብዛኛው አቅም ያላቸው ወጣቶች በመሸሻቸው ስልክም ስለማይሠራ የሸሹትን ቤተሰቦቻቸው ደኅንነታቸውን ለማረጋገጥ አለመቻላቸው ከፍተኛ ጭንቀት እንደፈጠረባቸው፣
  • አሁን ላይ ፖለቲካውን ለጊዜው በማቆየት ሰብዓዊ ድጋፍ ላይ ሁሉም ርብርብ ሊያደረግ እንደሚገባ ነዋሪዎቹ አጽንኦት ሰጥተው ለአመራሮቹ ገልጸዋል፡፡

ስለማይካድራ የቀረበው ሪፖርት ሙሉ ቃል ይህን ይመስላል

ወደ ማይካድራ የተጓዘው ልዑክ ቡድን መረጃ ያሰባሰበው የአካባቢው ነዋሪዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ ቀብር አስፈጻሚዎችን እና ወታደሮችን ቃለ-መጠይቅ በማድረግ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የጅምላ ቀብር ቦታዎችን፤ ሰፋፊ ሜካናይዝድ እርሻ ቦታዎችን፤ የተለያዩ ጥቃት ለመፈፀሚያነት የተዘጋጁ ድምዕ አልባ መሣሪያዎች የተከማቹባቸውን ሕንጻዎች፤ በከፍተኛ ደረጃ ግጭት የተካሄደባቸው ሥፍራዎችን (ለምሳሌ ከአዲስ አበባ 970 ኪሜ ላይ ከባድ እልቂትና ከሕወሓት ጋር የመጨረሻ ከባድ ግጭት የተካሄደበትን ንጓራ ድልድይን የመሳሰሉ)፤ በባህላዊ ጦር መሳሪያ እልቂት የተፈጸመባቸው አካባቢዎችን፤ ቀደም ሲል የሕወሓት ወታደራዊ ካምፕ ነበሩ የተባሉ ቦታዎችን ወዘተ… በመጎበኘት መረጃዎችን ለማሰባሰብ ተሞክሯል፡፡

በግጭቱ ወቅት የታዩ ክስተቶች

ሕወሓት ያስተዳድራቸው በነበሩ አካባቢዎች በተለይም ማይካድራ እና ሑመራ ግጭቱን ተከትሎ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ፣ ሞት እና የሀብት ውድመት ተከስቷል፡፡ የማይካድራው እልቂት የተጀመረው ጥቅምት 29 ቀን 2013 ዓ.ም ለጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም አጥቢያ ሲሆን፤ እስከ ኅዳር 3 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በነዋሪዎቹ ላይ እልቂት እንደተፈፀመ ልዑክ ቡድኑ ከነዋሪዎች ለመረዳት ችሏል፡፡ የሟቾቹ ቁጥር በሚመለከት ልዑክ ቡድኑ የተለያዩ መረጃዎችን የአካባቢው ነዋሪዎችን፣ ቀብር አስፈጻሚዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ መረጃ ለማሰባሰብ ሙከራ አድርጎ የነበረ ሲሆን የሟቾቹ ብዛት ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንና ትክክለኛ ቁጥር ለማስቀመጥ እንደሚያዳግት ለመረዳት ተችሏል፡፡ ቡድኑ ከላይ የተጠቀሱትን አካላት ቃለመጠይቅ ከማድረግ በተጨማሪ የጅምላ ቀብር ሥፍራዎችን ተመልክቷል፡፡

See also  ‹‹ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ማካተት አንዱ የሰላም ምንጭ ነው›› -የሃይማኖት መሪዎች

ሟቾቹን አንድ በአንድ ለመቅበር ሙከራ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም የሟቾቹ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ የተነሳ ጉድጓድ መቆፈር እና አስክሬኖቹን መሸከም ስላቃተ በጅምላ ከመቅበር ውጪ ሌላ አማራጭ ስላልተገኘ አስክሬኖቹን በዶዘር መቅበር ብቸኛ አማራጭ እንደነበር ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡ ሟቾች ማንነታቸው እየተለየ የተጠቁ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

ወደ ማይካድራ የተጓዘው የኢዜማ ልዑክ ቡድን ፖለቲካዊ ቀውስ ወደተባባሰባቸው ማይካድራ፣ ሑመራ እና አካባቢው በደረሰበት ወቅት የቀውሱ መጠን ካለፈው አንጻር እንደቀነሰ ተረድቷል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለውም እልቂቱ እንዲያበቃ፤ ቂመኝነት እንዲቀር፤ ሀዘኑ እንዲለዝብ የሃይማኖት አባቶች መገዘታቸው እና በሕዝቡ ውስጥ ሆነው ችግሩ እንዲፈጠርና የተፈጠረውም እንዲባባስ ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች ከአካባቢው በመሰወራቸው መሆኑን ልዑክ ቡድኑ መረዳት ችሏል።

 የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት፣ የአካባቢው ሚሊሺያ አባላት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና እንደ ግለሰብ የታጠቁ ነዋሪዎች በጋራ ተቀናጅተው በመሰለፍ የሕወሓትን ኃይል በመፋለማቸው ጦርነቱ ሊወስድ ከሚችለው ጊዜ ባነሰ መቋጨቱን ነዋሪዎች አስረድተዋል።

2 Comments

  1. ” ኢዜማን ዋጋ ይስከፍለዋል” … ኣይመስለኝም ። የኤርትራ ጦር ኣገልግሎቱን ጨርሶል ከአሁን ብኃላ ተፈላጊም ኣይደለም ። ቀጣይ መግለጫ የብልጽግና ነው ። ኢዜማ መቅደሙ ነው ። የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ኣሰላለፉን ያስተካክላል ። ትሕነግ ላልከው የሞተ ዘምድ የለህም

Leave a Reply