የሙለር ሪል ስቴት ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ በሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው

 የሙለር ሪል ስቴት ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ በሙስና ወንጀል ዐቃቤ ህግ ክስ መሰረተባቸው፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በዛሬው እለት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በተሰጠው ክስ መመስረቻ አምስት ቀናት ውስጥ ክስ መመስረቱን ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

ክሱ በመደበኛ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አምስተኛ የሙስና ወንጀል ችሎት በመዝገብ ቁጥር 266478 ክስ መመስረቱን ለችሎቱ ገልጿል፡፡ የአቶ ሙሉጌታ ጠበቆችም ክሱን ለመመልከት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት በዛው ችሎት ክሱን የተመለከቱ ሲሆን፥ ክሱ ያልደረሳቸው በመሆኑ ክሱ በዛሬው እለት በተከፈተው መዝገብ እንዲታይላቸው ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡

ችሎቱም በጠየቁት መሰረት በተከፈተው መደበኛ ክስ እንዲታይላቸው አዟል፡፡ ይሁንና ከዐቃቤ ህግ ጋር ተማክረው በመደበኛው ችሎት ዳኞች ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ተከትሎ በሰኞው መደበኛ ችሎት ጉዳያቸውን ለማየት ቀጠሮ ይዘዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ በቦሌ ክፍለከተማ ያለአግባብ 50 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት በመውሰድ እንዲሁም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማ ደግሞ 11 ሺህ ካሬ ሜትር የመሬት ወረራ በማድረግ በሚል ሁለት የሙስና ክስ ነው የተመሰረተባቸው፡፡

ይህ ክስ በቀጣይ ሰኞ በመደበኛው ችሎት የሚታይ ይሆናል፡፡

በታሪክ አዱኛ FBC

    Leave a Reply