ዶላር አባዝተን እንሠጣለን በማለት ሲያጭበረብሩ የነበሩ ሁለት ካሜሮናዊያን በቁጥጥር ስር ዋሉ … አዲስ አበባ ፖሊስየካቲት 6/2013(ኢዜአ) በ24 ሠዓት ውስጥ አራት ሚሊዮን ዶላር አባዝተን እንሠጣለን በማለት ሲያጭበረብሩ የነበሩ ሁለት ካሜሮናዊያንን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ፡፡ሀሰተኛ የኢትዮጵያን የገንዘብ ኖት በመስራት ወደ ገበያ እንዲገባ ሲያደርጉ ከነበሩ ሶስት ኢትዮጵያዊያን ተጠርጣሪዎች መካከል ዮሴፍ ተከስተብርሃን እና ተክለብርሃን ገብረመስቀል የተባሉት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ካሜሮናዊያኑ የተለያዩ አገራት የገንዘብ ኖቶችን በ24 ሠዓት ውስጥ እያባዛን እንሰጣለን በማለት ሲያጭበረብሩ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በተደረገ ክትትል በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጿል፡፡በፓስፖርት ስማቸው ናዋ ሳምፕሰን እና ጁዲ አያምባንግ የተባሉት ካሜሮናዊያን ተጠርጣሪዎች በአዲስ አበባ ቆይታቸው ማርክ እና ሳምሶን በሚሉ ሃሰተኛ ስሞች ሲጠቀሙ ነበር።የደቡብ አፍሪካ ዜግነት ጭምር እንዳላቸው በመናገርና ከተለያዩ ኢትዮጵያዊያን ጋር ግንኙነት በመፍጠር የማታለል ተግባራቸውን ለመፈፀም ሲጥሩ በተደረገው የተቀናጀ ክትትል እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።

May be an image of 2 people
ተጠርጣሪዎቹ ካሜራዊያን

ተጠርጣሪዎቹ አንድ ኢትዮጵያዊን በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ 2 ሚሊዮን ትክክለኛ ዶላር ይዘህ ከመጣህ በ24 ሠዓት ውስጥ በሁለት እጥፍ በማተም 40 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ ላንተ ቀሪውን 60 በመቶ ለራሳችን እንወስዳለን ብለው በማግባባት የማታለል ወንጀል ሲፈጽሙ እንደነበር ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡በስምምነቱ መሠረት አብሯቸው ለመሥራት የተስማማው ኢትዮጵያዊ ከተባዛው ዶላር ውስጥ የሚገኝ የናሙና ገንዘብ ኖት ነው በማለት መቶ ዶላር በመስጠት ወደ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ሄዶ ወደ ኢትዮጵያ ብር እንዲቀይረው በማደረግ ትክክለኛና ህጋዊ ተቀባይነት ያለው እንደሆነ በማስመስል ግለሰቡን ለማጭበርበር እንደቻሉ ገልጿል።መረጃ የደረሳቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የካሜሮናዊያኑን እንቅስቃሴ በመከታተል ሃሰተኛ ገንዘብ ለማተም የሚጠቀሙባቸውን መሣሪያዎች፣ የተለያዩ አገራት ገንዘቦች፣ ሰነዶችና ፓስፖርቶች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ አድርጓል።

ተጠርጣሪዎቹ የሃሰት ገንዘብ የማሠራጨት ሥራቸው እንዳይጋለጥ ግለሰቦችን ድብቅ በሆነ ሥፍራ በማግኘት ህጋዊ ስማቸውንና ዜግነታቸውን በመቀየር የማታለል ተግባር ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።ተጠረጣሪዎቹ 40 ሚሊዮን ሃሰተኛ ዶላር ለማባዛት በዶላር መጠን የተቆራረጡና የታተሙ ወረቀቶች፣ ፓውደሮች፣ ማቅለሚያዎች፣ የዶላር መለያ ማሽኖች፣ ማድረቂያ መሳሪያዎችና ሌሎች ግብዓቶችን ተጠቅመው እንዴት ሃሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን እንደሚያዘጋጁ ጭምር በመኖሪያ ቤታቸው ፖሊስ ብርበራ ባደረገበት ወቅት አሳይተዋል።በተያያዘ ሀሰተኛ የኢትዮጵያን የገንዘብ ኖት በመስራት ወደ ገበያ እንዲገባ ሲያደርጉ ከነበሩ ሶስት ኢትዮጵያዊያን ተጠርጣሪዎች መካከል ዮሴፍ ተከስተብርሃን እና ተክለብርሃን ገብረመስቀል የተባሉት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡

ግለሰቦቹ በቡድን በመደራጀት ሃሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን አትመው ሲያሰራጩ መቆየታቸውን የጠቆመው ኮሚሽኑ፤ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት በተደረገባቸው ጥብቅ ክትትልና ድንገተኛ ፍተሻ 40 ሺህ ሃሰተኛ ባለ መቶ ብር የገንዘብ ኖቶች ከተጠርጣሪዎቹ ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉን ኮሚሽኑ ለኢዜአ የላከው መግለጫ ያሳያል።

ኢዜአ

Leave a Reply