የኦብነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ በአስቸኳይ ስብሰባ ውሣኔዎች በሙሉ ተቀባይነት እንደሌላቸው ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

NEWS

የኦብነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ በአስቸኳይ ስብሰባ ተላልፈዋል የተባሉ ውሣኔዎች በሙሉ ተቀባይነት እንደሌላቸው ምርጫ ቦርድ አስታወቀ


የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ በአስቸኳይ ስብሰባ ተላልፈዋል የተባሉት ውሣኔዎች በሙሉ ተቀባይነት እንደሌላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ በማህበራዊ ገፁ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ)ን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

እነ አቶ ራያል ሃሙድ ጥር 24 ቀን በተፃፈ ደብዳቤ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር/ኦብነግ ከጥር 12-15 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በፓርቲው ውስጠ ደንብ እና ሌሎች የውስጥ መመሪያዎች፣ ከቀረቡት ሪፖርቶች እና ግኝቶች አንፃር በጥልቅ አጥንቶ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አብዲራህማን ማህዲ የሊቀመንበርነት ቃለ መሃላቸውን እና የድርጅቱን ውስጠ ደንቦች ጥሰዋል የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱንና ከሊቀመንበርነታቸው መነሳታቸውን፤ በአራት ወራት ውስጥ ብሔራዊ ጉባኤ እንዲካሄድ፤ አቶ ራያል ሃሙድ ተጠባባቂ ሊቀመንበር እንዲሆኑ መወሰኑን እንዲሁም ተጠባባቂ ሊቀመንበሩ 15 የሽግግር ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እና 3 የውስጥ ኦዲተሮች መምረጣቸውን ገልፀው ዝርዝሩን አያይዘው አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም ጥር 26 ቀን 2013 ዓ.ም. በፃፉት ደብዳቤ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ከጥር 12-15 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄው አስቸኳይ ስብሰባ የፓርቲው ሊቀመንበር እንዲታገዱ የወሰነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በፓርቲው ሊቀመንበር በተፈረመና በ29/01/2021 በቁጥር Chair/ONLF/G/D/001/21 ለኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር የዲሲፕሊን ኮሚቴ በተፃፈ እና ለቦርዱ በግልባጭ በተላከ ደብዳቤ በፓርቲው ስነምግባር ደንብ አንቀፅ 11(b)፣ አንቀፅ 17(b)፣ አንቀፅ 22(b) በአንቀፅ 23(b) እና በአንቀፅ 29 መሠረት ክስ ቀርቦ በዲሲፕሊን ኮሚቴው ከተገመገመና ከተጣራ በኋላ የክስ ዝርዝሮች ከአቃቤ ሕግ ከተሰሙ በኋላ የዲሲፕሊን ኮሚቴው ተከሳሾቹ የተከሰሱትበትን ጥፋቶች መፈፀማቸውን አረጋግጠው 22 ሰዎች እንዲባረሩ፣ 7 ሰዎች ለ6 ወራት እንዲታገዱ፣ ጥፋተኛ የተባሉ ሰዎች በፓርቲው ሕጎች በተደነገገው መሠረት ቅጣቱ ከተጣለበት ቀን ጀምሮ በ1 ወር ጊዜ ውስጥ ይግባኝ ማለት እንደሚችሉ በግልባጭ ለቦርዱ አሳውቋል፡፡

ቦርዱ በፓርቲው አመራሮች መካከል ያለውን አለመግባባት አስመልክቶ የቀረቡትን ሰነዶች በመመርመር ከዚህ የሚከተለውን ውሣኔ ወስኗል፡፡ በእነ አቶ ራያል ሃሙድ በኩል ከጥር 12-15 ቀን 2013 ዓ.ም. ተካሂዷል የተባለው አስቸኳይ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ስለመጠራቱ የሚያሳይ ሰነድ ያልቀረበ በመሆኑ፣

በአስቸኳይ ስብሰባው ላይ ተገኙ ከተባሉት 47 ሰዎች መሃል 10 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ብቻ በመሆናቸው በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀፅ 11.2 እና በአንቀፅ 13.1 መሠረት ምልአተ ጉባኤ ሳይሟላ የተካሄደ ስብሰባ በመሆኑ፤

በእለቱ የተካሄደውን ስብሰባ የመሩትና የፓርቲው “ምክትል ሊቀመንበር” እንደሆኑ የተገለፁት አቶ ራያል ሃሙድ በቦርዱ ጽሕፈት ቤት በሚገኘው የፓርቲው ሰነድ ላይ የሚታወቁት በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ሲሆን የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ አህመድ ያሲን ሼክ ኢብራሂም በመሆናቸው፤

የፓርቲው ሊቀመንበር የፈፀሟቸው ጉዳዮች በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀፅ 33 መሠረት በዲስፕሊን ኮሚቴ ስለመታየታቸው የቀረበ ሰነድ ባለመኖሩ፣

በዕለቱ በተካሄደው ስብሰባ አስራ አምስት “የሽግግር ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ” እና ሶስት የውስጥ ኦዲት መመረጡን መግለፁ ስብሰባው ምልአተ ጉባኤ ሳይሟላ የተካሄደ ከመሆኑ በተጨማሪ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ስለ “ሽግግር ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ” የተደነገገ ባለመኖሩ፣

በአራት ወራት ውስጥ ብሔራዊ ጉባኤ እንዲካሄድ የተላለፈው ውሣኔ ምልአተ ጉባኤ ሳይሟላ የተካሄደ ከመሆኑ በተጨማሪ ከመተዳደሪያ ደንቡ አንቀፅ 10.3 እና አንቀፅ 12.7 ጋር የሚቃረን በመሆኑ፣

ቦርዱ ከላይ የተገለፁት በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ ተላልፈዋል የተባሉት ውሣኔዎች በሙሉ ተቀባይነት የላቸውም ሲል ወስኗል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በፓርቲው ሊቀመንበር በኩል በፓርቲው ስነምግባር ደንብ መሠረት ክስ ቀርቦ በዲሲፕሊን ኮሚቴው ከተገመገመና ከተጣራ በኋላ 22 ሰዎች እንዲባረሩ 7 ሰዎች ለ6 ወራት እንዲታገዱ ስለመወሰኑ የተገለፀው ተጠቃሾቹ የተከሰሱበትን ጉዳይም ሆነ አጠቃላይ ሂደቱን የሚያሳይ ቃለጉባኤና ተያያዥ ሰነዶች ያልቀረቡ በመሆኑ ቦርዱ ውሣኔው ተቀባይነት የለውም ሲል የወሰነ መሆኑን ቦርዱ ያሳውቃል።

EBC

Related posts:

"መከላከያ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል በሚችልበት አስተማማኝ የዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛል" አብይ አህመድ
መንግስት "በመላው አገሪቱ ቁርጠኛ እርምጃ እየወሰድኩ ነው"- የትህነግ ሰርጎ ገቦች ላይም እርምጃ መወሰዱን አስታወቀ
አቶ ወርቁ አይተነው የገንዘብ ቀውስ እየገጠማቸው መሆኑ ተሰማ
ብ/ጄ ተፈራ ህገ መንግስቱን በኃይል በመናድ ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀረቡ
አውሮፓ ህብረት ያዘገየውን ድጋፍ አስመልክቶ ዳግም ሊመክር ቀጠሮ ያዘ
«ሕወሓት ጦርነትን እንደ አምልኮ የሚቆጥር ቡድን ነው» – ፕሮፌሰር ሀረገወይን አሰፋ
«በሕገወጦች ላይ ያለ ምኅረት እርምጃ መውሰድ አለብን፤ ይህ የመንግሥት ተግባር ነው» የአማራ ክልል
125 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ
«በአገሩ መከላከያ ላይ አፉን የሚከፍት ሕዝብ የለም፤ መንግስትም አይታገስም» ክብር ለመከላከያ ሰራዊት!!
በኢትዮጵያና ቱርክ መካከል የተደረገውን የወታደራዊ ማዕቀፍ ስምምነት ምክር ቤቱ አጸደቀ
የሞት ፍርደኛው የ25 ዓመታት ሰቆቃ! ከመሬት በታች የታፈኑት አባት
«ኢትዮዽያን ማስቀጠል ከሚፈልጉት ጎን በመሆናችን የሚከፋ ከአለ እርሱ መፍረሷን የሚናፍቅ ብቻ ነው!»
ደብዳቤ ለኢትዮጵያ - ከቢልለኔ ስዩም
የዓለም ባንክ የ300 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ፈረመ
"እናቴ ፍጹም እስር ቤት እንድትገባ አልፈግም" ብሎ እግሩን ያጣው ወጣት ምስክርነት ለሮይተርስ

Leave a Reply