“የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ከሕዝቡ ጋር በመወያየት በቀላሉ ሊፈታ የሚችል ነው ”(ዶ/ር) አረጋዊ በርሄ

“ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ከሕዝቡ ጋር በመወያየት በቀላሉ ሊፈታ የሚችል ነው የጠቅላይ ግዛትና የክፍለ ሀገር አከላለል ቋንቋን መሰረት ካደረገው የአሁኑ አከላለል የተሻለ ነበር ”

“ቋንቋን መሰረት ያደረገ አከላለልን መከተል ከቀጠለ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 በላይ ክልሎች ሊፈጠሩ ነው ማለት ነው” ዶ/ር አረጋዊ

ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ፣ የመሰረቱትን ሕወሓትን ትተው ውጭ ከቆዩ በኋላ በኢትዮጵያ የተካሄደውን የአመራር ለውጥ ተከትሎ በተሰደዱ በ40 ዓመታቸው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በፖለቲካ ተሳትፏቸው የቀጠሉት አንጋፋው ፖለቲከኛ ፣ የመጀመሪያው የሕወሓት ሊቀመንበር ሲሆኑ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ይባል የነበረውና አሁን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የተባለው ፓርቲ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ዶ/ር አረጋዊ አሁን ላይ ከተቃዋሚ ፖለቲካ መሪነት ባለፈም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ም/ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

አል ዐይን አማርኛ ከአንጋፋው ፖለቲከኛ አረጋዊ በርሄ ጋር ባደረገው ቆይታ ስለአወዛጋቢዎቹ የራያና ወልቃይት የማንነት ጥያቄዎች ፣ ስለትግራይ ሕግ ማስከበር ዘመቻና ስለምርጫ ጠይቋቸዋል፡፡ ዶ/ር አረጋዊ የወልቃይትና ራያን ጉዳይ በተመለከተ የሰጡትን ምላሽ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

የራያና ወልቃይት ጉዳይ እንዴት ይፈታ?

ረዘም ላሉ ዓመታት የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ሲያጨቃጭቅና ሲያወዛግብ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሁለቱም አካባቢዎች “የማንነት አስመላሽ ኮሚቴዎች” የነበሯቸው ሲሆን የፌዴሬሽን ም/ቤትና የትግራይ ክልል ም/ቤት ለጉዳዩ ምላሽ እንዲሰጡ ውትወታዎች ነበሩ፡፡ የትግራይና የአማራ ክልሎች ፖለቲከኞችም በሁለቱ አካባቢዎች ላይ እሰጥ አገባ ውስጥ ሲገቡ ተስተውሏል፡፡

አሁን ላይ አካባቢዎቹ በአማራ ክልል ስር እየተዳደሩ ቢሆንም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ግን ቦታዎቹ ከሕወሓት መነሳት በፊት እንደነበረው በትግራይ ክልል ስር መቀጠል እንዳለባቸው በትግራይ ቲቪ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

የትዴፓ ሊቀመንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ግን የራያና ወልቃይት ጉዳይ በውይይት ሊፈታ የሚችል እንደሆነ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡

የውዝግቡ መነሻ ከመሰረቱ የአስተዳደር አከላለሉ ቋንቋን መሰረት ያደረገ መሆኑ እንደሆነ ያነሱት አንጋፋው ፖለቲከኛ ፣ ከሕዝቡ ጋር በሚደረግ ውይይት ለሕዝቡ በሚመቸው መንገድ የአስተዳደር መዋቅር መፍጠር እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡

See also  "የምናስበውና የምናደርገው የሚገባቸው ጠላቶቻችን ናቸው" አብይ አሕመድ፤ ትህነግ ያፈረሰው ባህር ሃይል ዳግም ተወለደ

በአጼ ኃ/ስላሴ ጊዜ ጠቅላይ ግዛት ፣ በደርግ ዘመነ መንግስት ደግሞ ክፍለ ሀገር እየተባለ መካለሉ ቋንቋን መሰረት አድርጎ ከተካለለው የተሻለና ግጭት የማያስነሳ እንደነበረም አንስተዋል፡፡ “መሬቱ የትም አይሄድም፤ ባለበት ነው ያለው፤ የነዋሪውን ማንነቱን ጠብቆ በሰላም መኖር ይቻላል፡፡ ክልል ማካለል ካስፈለገ ደግሞ የትኛውም አስተዳዳሪ፣ የትኛውም ባለስልጣን ከሕዝቡ ጋር ተወያይቶ በዚህ መተዳደር ይጠቅማል በሚል በቀላሉ ሊፈታው ይችላል“ ብለዋ ዶ/ር አረጋዊ፡፡ “በተረፈ ግን ይሄ የኔ ነው፤ ያ የኔ ነው የሚባል ነገር የሚመጣው የመገንጠል ጥያቄ ስታነሳ ብቻ ነው“ ሲሉ አክለዋል፡፡

በራያና በወልቃይት የሚነሱትን ጨምሮ ሀገሪቱ ችግሮች ውስጥ እንድትገባ ያደረጓት ሌሎች መሰል ጉዳዮች “የሕወሓት ቋንቋን መሰረት ያደረገ አከላለል” ውጤት መሆናቸውን ያነሱት ዶ/ር አረጋዊ ፣ ቋንቋን መሰረት አድርጎ ክልል ማካለል “ሀገርን ወደ መበታተን አቅጣጫ ነው የሚወስደው” ነው ያሉት፡፡

“ቋንቋን መሰረት ያደረገ አከላለልን መከተል ከቀጠለ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 በላይ ክልሎች ሊፈጠሩ ነው ማለት ነው፤ አሁንም እየተፈጠሩ ናቸው“ብለዋል፡፡ ቋንቋን መሰረት ከማድረግ ይልቅ ሌሎችንም ሁኔታዎች፡ ማለትም ታሪክን፣ ባህልን፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ፤ መልክዓ ምድርና ሌሎች ጉዳዮችንም ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

የአጼ ኃ/ስላሴ እና የደርግ ዘመነ መንግስት እንዲሁም ከዛ በፊት የነበሩ መንግስታት “ቋንቋን መሰረት ያደረገ ክልል ስላልፈጠሩ እንደዚህ አይነት ግጭቶች እንዳልተከሰቱ” ያነሱት ዶ/ር አረጋዊ “ቋንቋን ብቻ መሰረት ያደረገ አከላለል ለማንም አይጠቅምም “ብለዋል፡፡

ራያና ወልቃይትን የተመለከተ ችግርን ለመፍታት ቁጭ ብሎ ከሕዝቡ ጋር መወያየትና ምን ይበጃል ብሎ ሕዝቡን መጠየቅ እንደሚገባ ያነሱት ዶ/ር አረጋዊ ፣ የቋንቋ ዕድገትን ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የሳይንስ ዕድገት እና ሌሎችንም መሰል ጉዳዮች ግምት ውስጥ በማስገባት በሀገር ደረጃ ተጠንቶ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚበጅ ስራ መስራት እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር አረጋዊ ከኢትዮጵያ የበለጠ የቋንቋ ብዛት ያላቸው ሀገሮች አከላለላቸው ቋንቋን መሰረት ያደረገ ስላልሆነ ከሕዝቡ ጋር እየተወያዩ አስተዳደራዊ መካለል እንደሚፈጥሩ በማሳያነት በማንሳት በኢትዮጵያም ተመሳሳይ መንገድ መከተል እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

See also  በትግራይ ክልል ተቋርጦ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ተጀመረ

Leave a Reply