የሰልፊ ፓለቲካ – በላይ ባይሳ


የፓለቲካ ርዕዮት የሚመነጨው ለሃገርና ለህዝብ እድገት ይበጃል ከሚል አስተሳሰብ ነው። ይህ አስተሳሰብ በማህበረሰቡ ውስጥ ከሚስተዋል ችግር ወይንም አዳጊ ፍላጎት አልያም ከሌላ ምክንያት ሊነሳ ይችላል። በመሆኑም አንድ ግለሰብ አልያም ድርጅት ከዚህ የሃሳብ ርዕዮተ-ዓለም በመነሳት ለማህበረሰቡ አበርክቶውን ለማሳካት እና ወደፊት መንግስት ለመሆን የሚያስችለውን የጠራ የፖለቲካ ፕሮግራም መቅረፅ መቻሉ ነው።

በላይ ባይሳ

ርዕዮተ-ዓለሙን እና የፖለቲካ ኘሮግራሙን ለማሳካት ራዕዩን ሌሎችን በማሳተፍና በማካፈል ተከታዮችን በማፍራት ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር ዋንኛ ተግባሩ ነው።

በፕሮግራሙ ህዝቡ አሁን ካለበት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፓለቲካዊ እንዲሁም ቴክኖሎጂያዊ ቁመና እንዴት አንድ ደረጃ ወደፊት ማራመድ እንደሚችል የሚያቀርበው አማራጭ ምክረ-ሃሳብ ህዝቡን ማሳመን መቻሉ ነው። ፕሮግራሙ የህዝቡን ፍላጎት ከሞላ ጎደል የሚያሟላ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል።

ጠንካራ ተቋማትን ለገነቡና በተነፃፃሪ “የዘመነ” የፓለቲካ ባህል ለገነቡ እንዲሁም በአንፃራዊነት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለሚያካሂዱ ሃገራት አማራጭ የፓለቲካ ኘሮግራም በማቅረብ ለውድድር መቅረብ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው። የምትመዘነው ወደፊት ለሃገርና ለህዝብ ለመስራት በምታቀርበው አማራጭ ሃሳብህ ብቻ እና ብቻ ይሆናል ማለት ነው።

ፓለቲካ ሲዘምን ዲፎልቱ የፊት ማርሽ ላይ ሆኖ ክርክሩ ነገን የተሻለ ለማድረግ በሰዓት ስንት ኪሎሜትር እንብረር የሚል አይነት ነው። አንዱ በ80፣ ሌላው በ100፣ ልላኛው ደግሞ 120 እንፍጠን አይነት ክርክር ነው። ልዩነቱ ሲበዛ ደግሞ አንዱ ጎንደር ለመሄድ በሰላሌ ይሻላል ሲል ሌላኛው በደብረብርሃን ቢርቅም የተሻለ ነው እንደማለት ነው። የሁሉም የመጨረሻ ግብ ግን የሃገርና የህዝብን እድገት ማፋጠን እና ኑሮውን ማሻሻል ነው።

የሰልፊ ፓለቲካ ደግሞ ብዙ ነገሩ ከዚህ ተቃራኒ ነው። ዲፎልቱ የኋላ ማርሽ ነው። የኋሊት ጉዞ ደግሞ ምንም አይመችም። ሁሉን ወደኋላ እያሳየ ራሱንም፣ ሃገርንም ህዝቡንም እጅግ ያንገላታል። አለፍ ሲልም ያጋጫል። ምትክ የሌለውን የሰውን ልጅ ህይወት ይነጥቃል።

በሰልፊ ፓለቲካ ርዕዮተ-ዓለምም ሆነ የፖለቲካ ኘሮግራም መሰረት የሚያደርገው በወደፊት ላይ ሳይሆን በትላንት ላይ ተቸንክሮ ነው።

በእርግጥ የኋላው ከሌለ የፊቱ አይኖርም እንደሚባለው ትላንት ለነገ መሠረት መሆኑ እሙን ነው። ይሁን እንጂ ትላንት ታሪክ ሲሆን፣ ዛሬ እውነት ሆኖ ነገ ግን ተስፋ ነው። ተስፋ ደግሞ የመኖር እና የህይወት መሠረት ነው።

ፓለቲካንም ሰው ሰው እንዲሸት የሚያሰኘው ታሪክን እንደ መማርያ፤ መጪውን ጊዜ ደግሞ በይቻላል መንፈስ አሻግሮ ካሳየ ብቻ ነው። ከዛ ውጪ ፓለቲካ ደረቅና እንጨት እንጨት የሚል ይሆናል። ጨው እንደሌለው ወጥ ጭምር አይመችም።

የፓለቲካ ርዕዮት ከትላንቱ ተምሮ ትኩረቱ የወደፊቱ ላይ ሲሆን ነው ማህበራዊ ለውጥ የሚያመጣው። ተራማጅ አተያይና አርቆ ተመልካች አስተሳሰብ እና ስብዕናም ስትጎናፀፍ ነው ለሃገር መዳኛ ለህዝቡም መድሃኒት የምትሆነው።

ሁል-አቀፍ እና አሳታፊ ገዢ የፖለቲካ የሃሳብ ልዕልና ማማ ላይ ለመድረስ ትላንት ላይ ተቸክሎ በማላዘን ዛሬ በእጁ ያለውን ወርቃማ ጊዜ ሳያበላሽ ለነገ መትጋት ሲቻል ነው።

የሰልፊ ፓለቲካ አዙሪቱ ልክ እንደ ሁለት ግራ እግር ጫማ ግራ የገባው የፓለቲካ አስተሳሰብ ነው። በትክክል የማይገባ እና የማይመች አካሄድ።

የሰልፊ ፓለቲካ ብቃት ሳይሆን የጅምላ ጩኸት፣ የጠራ የፓለቲካ ርዕዮትና ኘሮግራም ሳይሆን ጨበጣ (shooting in the dark)፣ ለውጥን ሳይሆን ነውጥን የሚያቀነቅን፣ በሃሳብ ሳይሆን በመንደር፣ በራዕይ ሳይሆን በድንግዝግዝ ቅዠት፣ በስሌት ሳይሆን በስሜት፣ በሃሳብ የበላይነት ሳይሆን በነሲብ ወዘተ… በሽታ የተለከፈ ነው።

የሰልፊ ፓለቲካ ዋንኛ መገለጫው ትላንት እንዲህ ሆንክ እንጂን ነገን እንዲህ ትሆናለህ አለያም ይሄን አደርግልሃለሁ የሚል ወደፊት ተስፋ አያሰንቅም። መርዶ እንጂ ብስራት የለውም። የኋሊት ጨለምተኛ ጉዞ ብቻ ነው። የፊትለፊት እይታህን የሚጋርድ የተዛባ አተያይ ጭምር።

የሃገራችን ፓለቲካ ደግሞ ተደጋግሞ በሰልፊ ደዌ የተመታ ነው። የሃገረ-መንግስትና እና የህብረ-ብሄራዊ ግንባታ ብሎም የማንነት ጥያቄዎች በተገቢው መልኩ ስላልተሰራባቸው ነው ሁሌ የሚያወዛግቡት።

በዚህ ምክንያት የ”ፓለቲካ ፖርቲዎች”ም በአብዛኛው በሚባል ደረጃ የሰልፊ ተጠቂ ናቸው። አባላቶቹም በተመሳሳይ። ለዚህም ይመስላል ከአዙሪቱ መውጣት ያልቻለው። ይህን ስል ግን ቁጥራቸው ቢያንስም ሀገራዊ ሃላፊነት የሚሰማቸው ፓርቲዎች እንዳሉም ልብ ይለዋል::

ታድያ ጥያቄው መፍትሄው ምንይሁን ነው?
መፍትሄው አንድ እና አንድ ነው። እሱም ከሰልፊ ፓለቲካ መፋታት ብቻ ነው።

ትላንት ታሪክ ሲሆን፣ ዛሬ እውነት ሆኖ ነገ ግን ተስፋ ነው! ሰልፊ ደግሞ ትላንትን ብቻ ወደሗላ የሚያሳይ::
በላይ ባይሳ
ጥር 24/2013 ዓ.ም

Leave a Reply