የዶ/ር አረጋዊ ስልታዊ አቀራረብና የአብርሃ ደስታ የፊት ለፊት ግትር አቋማቸው ሲፈተሽ!

NEWS

ትናንት ሕዝብን አወያይተው ካልወሰዱት ዛሬ ሕዝብን የማወያየት ጥያቄ እንዴት ትዝ አላቸው?

የወልቃይት ጠገዴ-የራያ ማንነት ጥያቄ አሁንም ማወዛገቡን ቀጥሏል። ሰሞኑን ማህበራዊ ሚዲያውን ያጣበበው ይኸው የማንነት ጥያቄ ነው። ከጦርነቱ ማግስት ጀምሮ ቀደም ብለው ወደ ትግራይ ተወስደው የነበሩ መሬቶች በአማራ ክልል ቁጥጥር ሥር በመዋላቸው በግራ ቀኙም ጎራ የቃላት ጦርነቱ ተፋፍሟል። አማራው በእጄ ገብተዋልና ከእንግዲህ ወይ ፍንክች ብሏል። ከተከዜ ወዲያ ያሉት ባለሥልጣናት ደግሞ ሞተን እንገኛለን፣ ሥልጣን እንለቃለን እንጅ ከእኛ እጅ የመውጣቱ ጥያቄ አይታሰቤ ነው ባዮች ናቸው። ፍጥጫው ቀጥሏል። እንበለ ጥይት ጦርነቱ በቃላት ተፋፍሟል። አሸናፊው ማን ይሆን? በዚህ ፍጥጫ መሀል ዶ/ር አረጋዊ በርሄ የፍጥጫውን ግንባር ለማርገብ ስልታዊ አቀራረብ ይዘው ብቅ ብለዋል። ምን አሉ?

ዶ/ር አረጋዊና የወልቃይት- ራያ የማንነት ጥያቄ

በወልቃይት የማንነት ጥያቄ ዙሪያ ብዙ አወዛጋቢ አቋሞች ሲንጸባረቁ ይስተዋላሉ። የሰሞኑ የዶ/ር አረጋዊ ጥያቄ ላይ ላዩን ሲታይ ችግሩን በጣም አቅልለው ለማሳየት ሞክረዋል። መሬት ላይ ግን ጥያቄው እርሳቸው እንደሚሉት ሳይሆን በጣም ከባድና ውስብስብም ነው። በእርግጥ አንድ የታየው ቁምነገር የእርሳቸው አቋም ከአቶ አብርሃ ደስታ ጋር ሲነጻጸር የተለሳለሰ እና ስልታዊ መስሎ መታየቱ ነው። በይዘት ልዩነት ያለው ስለመሆኑ ግን ማንኛችንም እርግጠኞች አይደለንም።

ዶ/ር አረጋዊ እንደሚሉት በእውን የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ቀላል ነውን? የእርሳቸው የቃለ መጠይቅ መልስ በአንድ ቃል ሲጠቃለል ሕዝቡን አነጋግሮ መወሰን ማለታቸው ነው በሌላ አነጋገር ቃሉን ባይጠቀሙበትም ሕዝበ-ውሳኔ (ሪፈረንደም) ሲሉ ነው በሌላ መልክ ያስቀመጡት።

ግን ሕዝብን ማነጋገር ሲባል እንዴት? የአማራ ርስቶች ቀደም ሲል በጉልበት ተወሰዱ። ከዚያ ሁሉም እንደሚያውቀው በ 1987 በጸደቀው ሕገ መንግሥታቸው ከጉልበት ወደ ሕግ በማሸጋገር የትግራይ ክልል ይዞታቸው ተብለው (ሆነው) እስካሁን ቆይተዋል። በጦርነቱ ሳቢያ እንደገና እነኝህ ቦታቸው ወደ ቀደመ ይዞታቸው (ወደ አማራ ክልል) መመለስ ቻሉ።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዶ/ር ሙሉ ነጋም ሆኑ አቶ አብርሃ ደስታ ሁሉም ማለት ይቻላል በሕገ መንግሥቱ መሠረት የትግራይ ክልል ስለሆኑ ሞተን እንገኛለን እንጂ ወደ አማራ ክልል መመለስ አይችሉም ባዮች ናቸው።

አማራው ደግሞ ቀድሞም በጉልበት ስለነበር ርስቶቻችን የሄዱት አሁን ደግሞ በጉልበት ስለተመለሱ ከእንግዲህ ወይፍንክች አንመልስም ብሎ የራሱን አስተዳደር መሥርቶ ራሱን እያስተዳደረ ይገኛል። በቋንቋቸው መማርም ጀምረዋል። በአንደበታቸው ላይ የተጣለው በልሳናቸው የመናገር እገዳ ተነስቶላቸዋል።

እና እንዴት ነው ዶ/ሩ በጣም ቀላል ነው እያሉ በጥያቄው ላይ የሚያፌዙት? በነገራችን ላይ ችግሩን ከፈጠሩት ጥቂት የወያኔ አመራሮች ዶ/ር አረጋዊ ግንባር ቀደሙ እንደሆኑ ሁላችንም የምናውቅ ይመስለኛል። ያንጊዜ በውሳኔው አብረው ተዋናይ ነበሩ። በትጥቅ ትግሉ ዘመን ከጉምቱ የወያኔ መሪዎች የመጀመሪያው ፋና ወጊም ናቸው።

በ 1992 ዓ.ም ፍራንክፈርት ላይ በተካሄደ ኮንፈረንስ በአንድ ወልቃይቴ (ወርቅነህ ረታ) አማካይነት ስለ ወልቃይት ተጠይቀው “ሜዳ እያለን ከሰራናቸው ስህተቶች አንዱ ወልቃይት ጠገዴን አለ አግባብ ወደ ትግራይ መጠቅለላችን ነው” ሲሉ ነበር የተደመጡት። (ይህን ሲሉ የተናገሩበት የቪዲዮ ማስረጃ በእጃችን አለ)

ዛሬ ደግሞ በጣም ቀላል ነው፣ ሕዝቡን አወያይቶ መወሰን ነው ሲሉ ሰማናቸው። የትኛው ሕዝብ? የተገደለው? የተሰደደው? ሕዝቡ ይወስን ሲባል፣ መጀመሪያ ወደ ትግራይ ሲከለል ሕዝቡ ተጠይቆ በሕዝብ ድምፅና ስምምነት ነበር ወይ የተወስነው? ሕዝቡ ይወስን ሲባልስ ነባሩ (indigenous) የወልቃይት ኗሪስ አሁን የት ነው ያለው? ጥያቄው ዶ/ሩ እንደሚሉት ቀላል ሳይሆን የፌዴራል መንግሥቱንም፣ የአማራና የትግራይ ክልላዊ መንግሥታትንም የሚፈታተን ገና ያልተፈታ አሳሳቢ ችግር መሆኑ እንቆቅልሽ ሊሆንብንም አይገባም።

የአቀራረባቸው ስልታዊነት ካልሆነ በወልቃይት ጠገዴ፣ ራያ የማንነት ጥያቄ ከአቶ ገብረመድህን አርአያ በቀር አብዛኛዎቹ የአቋም ልዩነት አይታይባቸውም ማለት ይቻላል። ትናንት ሕዝብን አወያይተው ካልወሰዱት ዛሬ ሕዝብን የማወያየት ጥያቄ እንዴት ትዝ አላቸው?

አንዳንዶች ጥያቄውን ለማቅለል አንድ አገር እስከሆን ድረስ ወደ ትግራይም፣ ወደ አማራ ክልልም ቢሆን ምን ችግር አለው ይላሉ። ችግሩ መሬቱን ሲወስዱ አንድ አገር ላለመሆን የራስን አገር በመመሥረት ምኞት ካርታም ዘርግተው ነው። ራሳቸው ዶ/ር አረጋዊ ደጋግመው ሲናገሩ እንደተደመጡትም እነ ሁመራ-መተማ ለሱዳን ኮሪዶር የውጭ በር መውጫ መግቢያ ስለሚያስፈልጋቸው ታስቦበት የተደረገ ውሳኔ ነበር። ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ኢኮኖሚ ነው። አካባቢው ድንግል መሬት እንደ መሆኑ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትም ሆነ ለየዕለት የፍጆታ አቅርቦት የታደለ አካባቢ ሆኖ መገኘቱ የኢኪኖሚ ሕልውና ቀልባቸውን ስለሳበውም ነው። እነ አብርሃ ደስታ ሞተን እንገኛለን የሚሉትም ያለ ምክንያት አይደለም።

ሌላው የሞተን እንገኛለን ምሥጢሩ ደግሞ ፓለቲካ ነው። ለትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት የራስ ምታት የሆነበት ይህን መሬት ካስረከብን ሕዝባችን እንዴት ይቀበለናል ነው? ለአማራው ክልላዊ መንግሥት ደግሞ ቀድሞ በጉልበት ሂዶ በጉልበት በእጃችን ከገባ እንደገና ብንመልስ ሕዝባችን ምን ይለናል? መንግሥትነታችንስ ቅቡልነት ይኖረዋል ወይ ነው የሚያስጨንቃቸው ጉዳይ።

በዚህ አስጨናቂ ጥያቄ ነው ዶ/ር አረጋዊ በጣም ቀላል ነው፣ ሕዝቡን አነጋግሮ መወሰን ነው ብለው ብቅ ያሉት። በማንኛውም አገራዊ የፓለቲካ ችግር ሕዝብን አነጋግሮ መወሰን እጅግ ጠቃሚም ነው። ግን ከ 1987 ጀምሮ በሕገ መንግሥቱ በትግራይ ክልል ተካለው የቆዩ የእኛ ይዞታዎች ስለሆኑ አሁን በእነኝህ ቦታዋች አንደራደርም ሞተን እንገኛለን ለሚሉት ለነ አብርሃ ደስታ ምን ምክር ይለግሷቸዋል ዶ/ር አረጋዊ?
በወታደራዊ ቋንቋ “ስልታዊ ማፈግፈግ” ሲባል እሰማለሁ። ዶ/ር አረጋዊ በትጥቅ ትግሉ ዘመን እነኛን ቦታዎች በጉልበት ወደዚያ ማካለላችን ስህተት ነበር ባሉበት አንደበታቸው ዛሬ ደግሞ ታጥፈው ሕዝቡን አነጋግሮ መወሰን ነው፣ በጣም ቀላል ነው ሲሉ ስንሰማቸው ስልታዊ አቀራረብ እንጂ ከነ አቶ አብርሃ ደስታ ተለይተዋል የሚያሰኛቸው ነጥብ በእጃችን ላይ የለም። በነገራችን ላይ ከዶ/ር አረጋዊ ቃለ መጠይቅ ትንሽ የተመቸኝ አገላለጽ ቢኖር የቀድሞው የጠቅላይ ግዛት ወይም ክፍለ ሀገር አስተዳደር ይሻል ነበር ያሉት ነው። ይህ አባባላቸው ቢያንስ የቋንቋ ፌዴራሊዝምን መቃወማቸውን ያመለክታል። ወልቃይት ጠገዴም ትግሬኛ ቋንቋ ትናገራላችሁ ተብለው መከለላቸውን በገደምዳሜም ቢሆን ተቃውመውታል።

ለማንኛውም ቦታዎቹ በአማራ ይዞታ ሥር ስለመሆናቸው አዋሳኟ ኤርትራ በመሪዋ በፕሬዚዴንት ኢሳይያስ በኩል የሚከተለውን ገልጻለች።
” ከአማራ ጋርም ጎረቤት ሆነናል። ከዚህ በኋላ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ ወሎ እና ሸዋ የኤርትራ ማረፊያ ይሆናሉ። አስመራም፣ ቀይባህርም የአማራ ቤት ይሆናሉ። በኢኮኖሚ ይተሳሰራሉ። ጥሩ ጉርብትና፣ ዝምድና ይኖራሉ።” ብለው አጠቃለውታል።

አንድ ጀምበሩ አረጋ የተባሉ የጎንደር ዩንቨርስቲ መምሕር እንደተናገሩትም፣ ሕዝቡን አነጋግሮ መወሰኑም፣ የሞተን እንገኛለን አካኪ ዘራፍ ፉከራውም እንዳለ ሆኖ አሁን በአማራው ክልል መደረግ ያለበት ቁምነገር ቢኖር፣

“….ወደ ራስህ የቤት ስራ በማተኮር፣

የአማራ ሕዝብን መሰረታዊ የሕልውና ጥያቄዎች በተመለከተ ከትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደርም ሆነ ከትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ድጋፍንና አጋርነትን የሚጠብቅ ካለ እሱ ሴራው አልገባውም ማለት ነው፡፡ ይልቁንስ በእጅህ የገባውን ወርቃማ እድል አሟጠህ በመጠቀም በምንም ታዓምር ሳትዘናጋ የራስክን የቤት ስራ በአግባቡ ስራ፡፡ ሙሉ ኃይልህንና ትኩረትህንም በሰሜን ምዕራብ ጎንደርና በሰሜን ምስራቅ ወሎ ላይ አሳርፍ ወዳጄ !! በዚህ ጉዳይ ላይ አብርሃ ደስታም ሆነ ዶ/ር ሙሉ ነጋ ያው አባይና ስዩም ማለት ናቸው፡፡ ሲሉ አሳምረው ገልጸውታል።…”

ሁሌ እየታመሙ አንገት ደፍቶ መቅረት፣
አበቃ እኮ ትናንት ዛሬ ላይ ላይደግሙት፣
ፅዋ ሞልቶ ፈስሶ ራሱ ጠፋበት፣
እሾህና አጣሪው ሥራና ሰሪውም ተፈራረዱበት።

ዘቦ እዝን ሰሚአ ለይስማ! (ጆሮ ያለው ይስማ!)
ሆኅተብርሐን ጌጡ

Via Amhara broadcasting corporation

Related posts:

"መከላከያ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል በሚችልበት አስተማማኝ የዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛል" አብይ አህመድ
መንግስት "በመላው አገሪቱ ቁርጠኛ እርምጃ እየወሰድኩ ነው"- የትህነግ ሰርጎ ገቦች ላይም እርምጃ መወሰዱን አስታወቀ
አቶ ወርቁ አይተነው የገንዘብ ቀውስ እየገጠማቸው መሆኑ ተሰማ
ብ/ጄ ተፈራ ህገ መንግስቱን በኃይል በመናድ ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀረቡ
አውሮፓ ህብረት ያዘገየውን ድጋፍ አስመልክቶ ዳግም ሊመክር ቀጠሮ ያዘ
«ሕወሓት ጦርነትን እንደ አምልኮ የሚቆጥር ቡድን ነው» – ፕሮፌሰር ሀረገወይን አሰፋ
«በሕገወጦች ላይ ያለ ምኅረት እርምጃ መውሰድ አለብን፤ ይህ የመንግሥት ተግባር ነው» የአማራ ክልል
125 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ
«በአገሩ መከላከያ ላይ አፉን የሚከፍት ሕዝብ የለም፤ መንግስትም አይታገስም» ክብር ለመከላከያ ሰራዊት!!
በኢትዮጵያና ቱርክ መካከል የተደረገውን የወታደራዊ ማዕቀፍ ስምምነት ምክር ቤቱ አጸደቀ
የሞት ፍርደኛው የ25 ዓመታት ሰቆቃ! ከመሬት በታች የታፈኑት አባት
«ኢትዮዽያን ማስቀጠል ከሚፈልጉት ጎን በመሆናችን የሚከፋ ከአለ እርሱ መፍረሷን የሚናፍቅ ብቻ ነው!»
ደብዳቤ ለኢትዮጵያ - ከቢልለኔ ስዩም
የዓለም ባንክ የ300 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ፈረመ
"እናቴ ፍጹም እስር ቤት እንድትገባ አልፈግም" ብሎ እግሩን ያጣው ወጣት ምስክርነት ለሮይተርስ

Leave a Reply