የኢትዮጵያ አዲሱ የኢኮኖሚ ከተማ ግንባታ


በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር በአዳማ እና ሞጆ ከተሞች መካከል ለመገንባት የታቀደው ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ተገንብቶ ለመጠናቀቅ 40 አመታት ይፈጃል ተብሏል። ተገንብቶ ሲጠናቀቅ የአዲስ አበባ ከተማን ግማሽ ያህል ይሆናል የተባለለት አዲሱ ከተማ በ23,656 ሄክታር መሬት ላይ ያርፋል ተብሏል። ጤና ይስጥልኝ አድማጮች በዛሬው የኢኮኖሚው ዓለም ዝግጅታችን በአዲሱ የኢኮኖሚ ከተማ የመንግስት ዕቅድ ከሀገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር እንዳስሳለን መልካም ቆይታ።

የኢትዮጵያ መንግስት የታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ ግዙፍ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የልማት አውታሮች በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛል። ሀገሪቱ የምታከናውናቸው የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጿቸው ከፍተኛ መሆኑ የመጠበቁ ያህል ፕሮጀክቶቹ ለመገንባት የታቀዱበት መንገድ እና ወደ ትግበ,ራ ሲገባ የነበሩ ሀገራዊ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች በፕሮጀክቶቹ ላይ ጥያቄ ሲያስነሱ ቆይተዋል። ከእነዚህ ውስጥ የልማት ፕሮጀክቶቹ ጊዜ ተወስዶባቸው እና አዋጭነታቸው በጥልቀት ሳይጠና እና በይድረስ ይድረስ ወደ ግንባታ የተገቡ ፕሮጀክቶችን ማንሳት ይቻላል ።ለዚህ ደግሞ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፣ ኩራዝ የስኳር ፕሮጀክቶችን የባቡር ፕሮጀክቶችን በማሳያነት ማንሳት ይቻላል ። ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸው ብቻ ሳይሆን ከታቀዳለቸው በላይ መዋዕለ ንዋይ መጠየቃቸው የሀገር ሀብት ለብክነት እንዲዳረግ ስለማድ,ጉ ይጠቀሳል። 
አዲሱ የኢኮኖሚ ዞን የከተማ ግንባታ ከ2009 ዓ/ም ጀምሮ ሲጠናበ የቆየ ፕሮጀክት መሆኑን የገዳ ኢኮኖሚ ዞን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ደመላሽ ሙሉ ይናገራሉ። በሀገሪቱ መጣ ያሉትን ለውጥ ተከትሎ የታቀደ ነው የሚሉት ኢንጂነር ደመላሽ ፕሮጀክቱ ትኩረት ያደረገው «የሀገሪቱን ስራ አጦች ቁጥር ለመቀነስ የስራ ዕድል መፍጠር ነው»


 ለለውጡ ምክንያት ናቸው ተብለው ከሚታሰቡ ጉዳዮች አንደኛው በጣም መጠነ ሰፊ የሆነ የስራ አጦችነት መስፋፋት በሀገራችን ላይ  ወጣቱ ከዩኒቨርሲቲ እየተመረቁ በተለያዩ ሴክተሮች ምንም ስራ ሳያገን የመቀመጥ እና ወደ ሌላ ነገር የሚያስገባው ከዚህ የስራ አጥነት ጋር የሚያያዝ ስለሆነ ዋና ዋና ናቸው የሚባሉትን ምክኒያት ትኩረት አድርጎ በእነርሱ ላይ መስራት  ስለታመነበት ነው።የዚህ የገዳ ኢኮኖሚ ዞን መሰረተ ሃሳቡ ለሀገሪቱ ከሚያስገኘው ጥቅም ባሻገር በቅድሚያ ለወጣቱ የስራ ዕድል በስፋት ያመጣል።»
በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ አለመረጋጋቱ ፣የኢኮኖሚው እየተዳከመ መሄድን ተከትሎ  የዋጋ ግሽበቱ እየጨመረ መሆኑ ይነገራል። ይህ ደግሞ የኑሮ ውድነትን አስከትሏል። በተለይ ደግሞ የውጭ ምንዛሬ እጥረት መግጠሙ  የግንባታ ቁሳቁሶችን ዋጋ አንሯል። ይህንን ተከትሎም  መሰል ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴው ሲጀመር በእርግጥ ቅድሚያ ማግኘት ይገባው ነበር ወይ ብለው የሚጠይቁ ወገኖች እንዳሉ ይሰማል። የባለስልጣኑ ዳይሬክተር ኢንጂነር ደመላሽ ለዚህ ሲመልሱ የመንግስት ሚና የከተመዋን የመሰረተ ልማት ስራዎች ከሟሟላት ሃላፊነት የዘለለ ሚና አይኖረውም ።

See also  የኢትዮ-አውሮፓ ሕብርት የጋራ ምክክር ተካሄደ

ለግንባታው ተሳትፎ የውጭ እና ሀገር በቀል ባለሃብቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ነው የሚገልጹት። «በመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ብቻ ነው የመንግስት ጣልቃ ገብነት እንጂ ሌሎቹ ነገሮች በአጠቃላይ የሚገነቡት በአለምአቀፍ አልሚ ባለሀብቶች አማካኝነት ነው።እኛ መድረኩን ነው የምንፈጥረው፤የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እናካሂዳለን፤ ዉሃ ይፈልጋሉ ውሃ እናስገባለን ፤ መብራት ይፈልጋሉ መብራት እናስገባለን። ቴሌኮሙኒኬሽን ይፈልጋሉ ዋናው መስመር ድረስ እናስገባለን። ከዚያ በኋላ ግን ያለው እኛ በምናወጣው ዕቅድ መሰረት አለማቀፍ አልሚዎች ወስደው የሚሰራውን ነገር ይሰራሉ።»


በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር በአራት ክፍል ተከፋፍሎ ለመገንባት የታቀደው አዲሱ የኢንዱስትሪ ከተማ የዲዛይን ስራው ተጠናቆ ወደ ተከታዩ ምዕራፍ ለመሸጋገር በዝግጅት ላይ እንዳለ ተገልጿል። ነገር ግን መንግስት ቀደም ሲል በተመሳሳይ መንገድ ያስገነባቸው አነስተኛ የኢንደስትሪ መንደሮች የስራ ዕድልን በመፍጠርም ሆነ የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት ሂደት ምን ያህል ውጤታማ ሆነዋል ሲሉ አንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ይጠይቃሉ። ዶ/ር አየለ ገላን  በኩዌት ኢንስቲትዩት ፎር ሳይንቲፊክ ሪሰርች የፐብሊክ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተመራማሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በኦሮሚያ ክልል ሊገነባ የታሰበው አዲሱ የኢኮኖሚ ከተማ ከመገንባት በፊት ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ከመዳሰስም  በፊት በሀገር ውስጥ የተገነቡ ተመሳሳይ አንስተኛ ፕሮጀክቶች ምን ያህል ውጤታማ ሆነዋል የሚል ጥናት መከናወን ነበረበት ይላሉ።
« እንግዲህ ይኼ በሞጆ እና በአዳማ ከተሞች መካከል ያለው የኢኮኖሚ ዞን  የመጀመርያው አይደለም ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚያ በላይ እስከ 16 የሚደርሱ የኢኮኖሚ  ዞኖች እንዳሉ ነው የምናውቀው። እንዚያም ሲፈጠሩ የስራ ዕድል ፈጠራ ፣ የውጭ ምንዛሪ ማምጣት መሰረታዊ የኢንደስትር ሽግግርን ለማፋጠን ተብለው ነው ስራ ላይ የዋሉት። እነዚህ ከዚህ በፊት የተተገበሩት ምን ያህል ስራ ፈጠሩ ? ምን ያህል የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ቀረፉ? ምን ያህል ወደ ኢንደስትሪ የሚደረገውን ሽግግር አፋጠኑ?  እስካሁን ያሉትን የኢንደስትሪ መንደሮች አፈጻጸም ለምን አናይም?»
ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛው የኢንደስትሪ ልማት ስራዎች የአዲስ አበባ ዙርያን ተመራጭ ሲያደርጉ መኖራቸው ይነገራል። በምክንያትነት የሚጠቀሰው በተለይ እንደ ኤሌክትሪክ ውሃና መንገድን የመሳሰሉ የመሰረተ ልማቶች ከተቀረው የሀገሪቱ ክፍል የተሻለ ሆነው መገኘት እና አዲስ አበባን በቅርበት ማግኘታቸው ነው። አዲሱ የገዳ የኢኮኖሚ ዞን ከተማ  ከአዲስ አበባ አዳማ መስመር ያለውን  ያለውን የበለጸገ የመሰረተ ልማት ታሳቢ አድርጎ ታቅዷል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ደመላሽ ሙሉ።
«የመጀመርያው የድሬዳዋ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እዚያ ግንባር ላይ ወደ ስራ የገባው የዚህ ጥናት መነሻ ነው ።ከእርሱ በመቀጠል  ይኼ አሁን እኛ የመረጥነው ቦታ ነው። ከብዙ የመረተ ልማት አውታሮች ጋር የተገናኘቦታ ስለሆነ ፤ በባቡር የተገናኘ ነው፤ በየብስ ትራንስፖርት ሀገር አቋራጭ ሀገራችንን ከሌሎች የሚያገናኙ በሁለቱም ወደ ኬንያ እና ወደ ጂቡቲ የሚሄደው በዚሁ መስመር መሆኑ እንዲሁም ወደ አሰብም የሚሄደው በዚሁ ኮሪደር ያልፋል። ባቡርም እንደሚታወቀው ከጂቡቲ  ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው በውስጡ ነው የሚያልፈው ፤ በፈጣና መንገድም ከአዲስ አባባ አዳማ እና ከሞጆ ሐዋሳ የሚሄደው መንገድ በዚሁ መስመር ነው የሚያልፈው ። በዚህ ላይ ሌሎች የቴሌኮሚኒኬሽን መሰረተ ልማቶች በዚሁ አካባቢ የሚያልፉ በመሆናቸው እና ለአዲስ አበባ ከተማ እጅጉን ቅርበት ስላለው ቦታው ተመራጭ ሆኗል።»
የስራ አጥነትን ችግር ከመሰረቱ መቅረፍን አንዱ አላማው አድርጎ የተጀመረው አዲሱ ከተማ የሚገነባበት ከተቀረው የሀገሪቱ ክፍል አንጻር የተሻለ የመሰረተ ልማት በሚገኝበት አካባቢ መመስረቱ እንዲሁም ለመዲናዋ አዲስ አበባ በቅርበት ላይ መገኘቱ በመንግስት በኩል  እንደ መልካም አጋጣሚ ተወስዷል። ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የሀገሪቱን ሀብት ወደ አንድ አካባቢ የሚያከማች እና ተበታትኖ ያለውን የስራ አጥ ያላገናዘበ ነው ሲሉ የኢኮኖሚ ባለሞያው ያስረዳሉ። 


«አሁን ችግር የሆነው የሀገሪቱ አንጡራ ሀብት በሙሉ አዲስ አበባ እና አዲስ አበባ ዙርያ ፣ አዲስ አበባ እና አዳማ መካከል እንዲፈስ ተደርጎ ሌሎች አካባቢዎች እየተራቆቱ ነው ።  ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ግንዛቤ ያልሰጠው እና መንግስትም ግንዛቤ ያልሰጠው ነገር የአካባቢ ድህነት ነው። የስራ ዕድልን ወደ እነዚያ አካባቢዎች በመውሰድ  እነዚያ አካባቢዎች እንዲለሙ እንዲያድጉ በመጠነኛ ኢንጸስትመንት ማለት ነው ግዙፍ በሆነ ቢሊዮን አንድ ከተማ እዚህ አዲስ አበባ ማዕከል ላይ ከማቋቋም ትናንሽ መሰረተ ልማቶችን በየቦታው ማደራጀት ያስፈልግ ነበር። »
መሰል የኢኮኖሚ ከተሞች መፈጠራቸው ሀብትን አሰባስቦ እና አቀናጅቶ ለመጠቀም እና የተሻለ አማራጭ እንደሆነ የሚገልጹት ደግሞ አቶ ወንድሙ ገምታ ናቸው። የተበታተነ የኢኮኖሚ አማራጮች እንዲኖሩ የሚፈለጉን ያህል የተበታተነውን የሚያስተሳስር መሰ ል የተደራጀ ከተማ ሊኖር ይገባል ይላሉ። አቶ ወንድሙ በዩናይትድስቴትስ ላስቬጋስ ኔቫዳ ዩኒቨርሲቲ ረዳት የኢኮኖሚ ተመራማሪ ናቸው ።  
«  እዚህ ቦታ ላይ የሚሰራው የኢንደስትሪ ልምድ አብዮት የመፍጠር አቅም አለው።በገጠሩ አካባቢ ያለውን አቅም ትንንሽ አቅም ከዚህኛው ጋር ለማስተሳሰር ፤ ገበሬውን ከዚህ ኢንደስትሪ ጋር የማስተሳሰር ፣ ዋናው ትስስር የመጠሩ ጉዳይ ላይ ነው እንጂ ሀይል በመሰባሰቡ ወይም ደግሞ ከተሞች አንድ ቦታ መሰባሰባቸው ችግር የለውም ። ምክንያቱም የማምረቻ ወችን ስለሚቀንስ ነው። የማምረቻ ወጭ ቀነሰ ማለት ደግሞ የምንፈልገውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት በር ከፈተልን ማለት ነው።»
የሆነ ሆኖ ከሌሎች ክልሎች ቀድሞ በ40 ዓመት የሚጠናቀቅ የኢኮኖሚ ከተማ ለመገንባት አቅዶ ስራ የጀመረው የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር ትልቅ ስራ ከፊቱ ይጠብቀዋል። ምናልባትም ዕቅዱ ተግባራዊ ከሆነ ኢትዮጳያ በአፍሪካ እንደ ግብጽ ፣ ጋና እና ኬንያን የመሳሰሉ ሀገራት ከጀመሯቸው መሰል ፕሮጀክቶች ጋር ስሟ እንዲነሳ ሊያደርግ ይችል ይሆናል። ለዛሬ ያልነው ይኸው ነው ሳምንት በሌላ ዝግጅት እንጠብቃችኋለን።
 
ታምራት ዲንሳ  ኂሩት መለሰ DW amharic

See also  "ኢትዮጵያ ግድቧን ውሃ ብትሞላም የሚፈጠር ጫና የለም" የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

Leave a Reply