ህወሃት “በዓባይ ወንዝ ጎጃም ከሚለማ የሲና በረሃ ቢለማ ይሻላል” በማለት የትግራይን ህዝብ ከኢትዮጵያዊነት ለመነጠል ‘አክሱማዊያን ኢትዮጵያዊያን አልነበሩም’ የሚል የሀሰት ድርሰት በመጽሀፍ አዘጋጅቶ ሲሰብክ እንደነበር የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አባል ገለጹ። መንግስትና የመገናኛ ብዙሃን ይህን የፈጠራ ታሪክ ማስተካከል የሚያስችል ስራ መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የትግራይ ክልል ሰሜናዊ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሙሉብርሃን ኃይሉ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ ላይ “ህወሃት የትግራይንም ሆነ የኢትዮጵያን ህዝብ ታሪክና ስብዕና የማይመጥን የዘራፊዎች ስብስብ መሆኑን ባሳለፋቸው 45 ዓመታት አሳይቷል” ብለዋል፡፡

የአክሱም ዘመነ መንግስት የመላ ኢትዮጵያዊያን የጋራ የስልጣኔና የታሪክ አምድ ሆኖ ሳለ ህወሃት ‘አክሱማዊያን ኢትዮጵያዊያን አልነበሩም’ የሚል የፈጠራ ድርሰት አዘጋጅቶ ህዝብ ሲያሳስት እንደነበር አውስተዋል።

ከዚህም ባለፈ “በዓባይ ወንዝ ጎጃም ከሚለማ የሲና በረሃ ቢለማ ይሻላል” እያሉ ትግራዊያንን ከኢትዮጵያዊነት ማማ ለማውረድ ሲታትሩ ነበር በማለት ተናግረዋል፡፡

አቶ ሙሉብርሃን እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያዊያን ላይ የነበረውን አምባገነናዊ ስርዓት ለመጣል በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ህወሃትን የመሰረቱ ታጋዮች በወደቁበት ቀርተዋል፡፡

እንደ ገሰሰው አየለ (ስሁል) ያሉ ጀግኖች ከኢትዮጵያዊነታቸው ፈቅቅ ባለማለታቸው የህወሃት የበቀል በትር አርፎባቸው በሞቱበት አስክሬናቸው እንዳልተነሳና ስማቸውን የሚያስጠራ ሀውልት እንዳልቆመላቸው ተናግረዋል፡፡

አብዛኛው የትግራይ ህዝብ የህወሃትን ሴራና ተንኮል ጠንቅቆ ያውቃል የሚሉት አቶ ሙሉብርሃን ነገር ግን በ45 ዓመታት በተዘራው የተዛባ ትርክት ሰለባ የሆኑ ወጣቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

“የህወሃትን የ17 ዓመት ትግል ጊዜን ጨምሮ በአጠቃላይ የ45 ዓመታት ጉዞውን ከህዝቡ ጋር ስንገመግም በትግሉ ታሪክ ውስጥ የተገለጹ ትርክቶች የተዛቡና ለህዝቡ ባዕድ መሆናቸውን አይተናል” ብለዋል።

ህወሃት ለትግራይ ህዝብ ‘እንኳን ከእናንተ ተፈጠርኩ አንተ የተከበርከው የትግራይ ህዝብ’ ከሚል የወረቀት ላይ ጽሁፍ ውጭ ምንም ጥቅም እንዳላስገኘለት ገልጸዋል።

“ትግራይ በተለያዩ የተፈጥሮ ማዕድናትና ጸጋዎች የከበረች ብትሆንም ሀብቱ ወደ ጁንታው አባላት ኪስ ይገባል እንጂ የትግራይ ወጣቶችን ከህገ-ወጥ ስደትና የባህር ሰለባ ከመሆን አላዳናቸውም” ብለዋል፡፡

መንግስት በህወሃት ላይ በወሰደው ህግ የማስከበር ዘመቻ የጁንታው ቤተሰብ አባላት የመሰረቱት የትግራይ ሚዲያ ሀውስን ጨምሮ ሌሎች በውጭ ያሉ የትግራይ ተወላጆች ተቃውሞ የሚያሰሙት “የትግራይን ነባራዊ ሁኔታ ስለማያውቁ ወይም ከግል ጥቅማቸው ውጭ ሌላ የማይታያቸው ግዴለሾች በመሆናቸው ነው” ብለዋል አቶ ሙሉብርሃን፡፡

“በትግራይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ለመገንዘብም የመገናኛ ብዙሃንም ወደ ክልሉ መጥተው እውነቱን መዘገብ ይችላሉ” ብለዋል፡፡

መንግስትም ታች ድረስ ወርዶ በየአካባቢው ካለው ህዝብ ጋር መወያየትና የተሻለ የመፍትሄ ሃሳብ ማምጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

(ኢዜአ)


Leave a Reply