አሜሪካ እጅግ አስገራሚ መግለጫ አሰራጭታለች። አማራ ከትግራይ ክልል ይውጣ ብላለች። በትግራይ ግፍ መፈጸሙን አምናለች። ግን ለሜሪካ ” ግፍ” ምንድን ነው? አሜሪካኖች ስለ ግፍ የማውራት ሞራል አላቸው? የሰው አገር ገብተው ሰው እያነቁ የሚገሉ፤ ከመሰላቸው አገር በአንድ ጀንበር የሚያፈርሱ፣ አገር የሚበትኑ፣ ሃጢያታቸው ሰማይ የነካ ሆነው ሳለ “ግፍ” አስጨነቀን እያሉን ነው። ለመሆኑ ጋምቤላ፣ ማይካድራ፣ ራያ፣ በደኖ፣ሆራ ኢሬቻ፣ ዋተር… የተካሄደው ምን ነበር? አልሰሙም? አላዩም? ሳተላይታቸው የዛኔ ትኩስ አፈርና ብስባሽ መለየት አይችልም ነበር? ቴክኖሎጂው የላቸውም ነበር?

እንዲያም ሆኖ አሜሪካኖች ግፍን የሚለኩበት ሚዛን ምን ይሆን? አሁን ማይካድራ የተፈጸመው የሰሞኑ ግፍ ብቻውን የትህነግ ሰዎችን ወንጀለኛ አያደርጋቸውም? ታሉበት ታድነው ለህግ እንዲቀርቡ በዓለም ደረጃ አዋጅ አያስወጣም? የማይካድራ ጭፍጨፋ ግፍ ላለመባል ምን ይጎለዋል? ሰው እንደበግ የታረደበት ማስረጃና መረጃ እያለ ለምንስ ዝም ተባለ? መከላከያን መጨፍጨፍስ የጦር ወንጀል አይደለምን? አሜሪካና እስራዔል አንድ ወታደር ግልምጫ ደረሰበት ብለው ወይም በወሃ ቀጠነ አይደለም እንዴ አገር ከሰማይ፣ ከምድርና ከአየር አገር የሚያነዱት? ይህ ሲታሰብ እነሱን ተወት አድርጎ አሁን ምን ይሁን ብሎ ወገብን ጠበቅ ማድረግ ግድ ነው። ረሃብም ከሆነ መራ ግድ ይላል።

” ግፍ በትግራይ ክልል” በሚል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለርህራሄው ብዛት የሚመጥነውን ርዕስ መርጦ በተለያዩ ወገኖች የሚፈጸም ግድያ፣ ማፈናቀልን፣ የጾታዊ ጥቆቶችና ማናቸውም ያልተገቡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አጥብቆ እንደሚያወግዝ ይፋ ያደረገው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣውን ሽንቁር የበዛበት መግለጫ ተከትሎ ነው።

መንግስት መግለጫውን ባልተሟላ መረጃ የቀረበ መሆኑንን አስታውቆ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ ልዩ አጣሪ ቡድን አቋቁሞ ተፈጽሟል የተባለውን የመብት ጥሰት እንደሚያጣራ ይፋ አድርጎ ሳለ ነው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድርጊቱ በገለልተኛ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲጣራና ጥፋተኞች ተጠያቂ እንደሚሆኑ ያስታወቀው። አሜሪካ ይህንን ባትልም ጉዳዩ የማይመለከታቸው ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ከደረሰ ዜጎች ባይሆኑም በአግባቡ ሊጣራ ይገባል።

አንቶኒ ብሊንክን ከቀን በፊት ባወጡት መግለጫ ከመንግስት ጋር በተደጋጋሚ መነጋገራቸውን አውስተዋል። በትግራይ ክልል ያለው ቀውስ በሚቆምበት፣ ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ ውይይት ማድረገቸውን ያስታወቁት ሚኒስትሩ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ መርማሪ ቡድን እንዲገባ መጠየቃቸውንም አክለው ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል እንዳሉት ለውጡን እንደሚደግፉ አጽንዖት ሰጥተው የጠቆሙት ነገር የለም። ይልቁኑም በመግለቻቸው መጨረሻ ኢትዮጵያዊያን ላይ ተሳልቀዋል።


RELATED POST


በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ስለተፈጸሙ ግፎችና ግፍ ፈጻሚዎቹን አስመልክቶ መግለጫው ያለው ነገር የለም። በጉልበት ማንነታቸውን ተነጥቀው ሲገደሉ፣ ዘራቸው ሲጠፋና ባህላቸው ሲደመሰስ ስለኖሩ የራያ፣ የወልቃይትና ጠገዴ አማሮች በመረጃ ለተደገፈ ግፍ አጣሪ ቡድን እንዲመደብ አሜሪካ አልጠየቀችም። ወይም ትዝ አላላትም። አለያም በነሱ የግፍ መስፈርት ” ግፍ ” እንዲባል ምን እንደጎደለ ኢትዮጵያና የአማራ አንቂ ተብዬዎች አልጠየቁም።

በቅርቡ በማይካድራ በገጀራ ስለታረዱት ንጽሁሃን ዜጎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጫ የተነፈሰው ነገር የለም። በተኛበት ክህደት ተፈጽሞበት በግፍ ስለተጨፈጨፈው የአገር መከላከያ ሰራዊት አሁንም የተባለ ነገር የለም። ወይም የአገር መከላከያ ሰራዊት ነብስ ተደርጎ እንደማይወሰድ አለገለጸም። ወይም እነሱ ሲጨፈጭፉና ሲያስጨፈጭፉ ትክክል ፣ ሲነኩ የጦር ወንጀል ተፈጸመ እንደሚሉት የትህነግ ፍልፈሎች ተመሳሳይ ቋንቋ አላሰሙምም።

መንግስት ለሰብአዊ ድጋፍ ሰጪዎች በሩን መክፈቱን፣ ለዓለም ዓቀፍ አጣሪዎችና ለጋሾች ፈቃድ መስጠቱን ያደነቀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መግለጫ አገራቸው ከላይ የተዘረዘረው ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ከማናቸውም አካላት ጋር አብራ እንደምትሰራ አስታውቋል። አያይዞም የአማራ ልዩ ሃይልና የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ ክልል እንዲወጡ ያሳሰቡት ” ቅድሚያ” መሆን እንደሚገባው በማሳሰብ ነው። እንገዲህ ቅድሚያ እንዲሆን የተባለው ትዕዛዝ ኤርትራን ብንተዋት እንኳ አማራ ይውጣ የተባለው ከራያ፣ ከወልቃይት ጠገዴና አካባቢው ነው። ይህ ማለት ማይክድራ ከጭፍጨፋ የተረፉት ሰዎችን ጨመሮ ላለፉት 30 ዓመታት ተዘግቶባቸው ግፍ ሲፈጸምባቸው የነበሩ ዜጎች ዳግም ወሃኔ ላይ ይወደቁ ማለት መሆኑንን አሜሪካኖች አላወቁም ማለት አይደለም።

በትግራይ ያለውን ቀውስ አስመልክቶ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ አፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ከአሜሪካ ጎን እንዲሰለፉ የጠየቀው መግለጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያላግጣል። ሲያላግጥም “The United States remains committed to building an enduring partnership with the Ethiopian people.” አሜሪካ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ዘላቂነት ያለው ወዳጅነትን ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኗን ያስታውቃል” በሚል ነው ። በአሜሪካን እሳቤ ” የኢትዮጵያ ሕዝብ” ስሊሉ ማንን እንደሆነ አይታወቅም።

ጆን ባይደን ሲመረጡ አብዛኛ ኢትዮጵያዊያን በስሜት ይዘሉ ነበር። መረጃ ያላቸው ግን ትራምፕን ከተራ ፉካራቸው በቀር ፓርቲያቸው ፓርቲያቸው ተደጋጋሚ ክህደት ኢትዮጵያ ላይ እንዳልፈጸመ በተሻለ ደረጃ ከዴሞክራት አብልተው ያስቀመጡታል። አሜሪካ አሁን ስልጣን ላይ ባሉት ዴሞክራቶች አማካይነት በሶማሌ ጦርነት ወቅት ክህደት፣ በክሀደቱ ሳቢያ ወረራ ተፈጽሞባታል። ገንዘቧን ከፍላ የገዛችውን መሳሪያ ተከልክላ ጭፍጨፋ አስተናግዳለች። በ1983 ለንደን ድርድር አሜሪካ በገሃድ ሪፐብሊካን ቢሆኑም በኮሆን አማካይነት የተጠና ዝግጅት ያለው ክህደት ተፈጽሞባታል። ትህነግን ኢትዮጵያ ላይ የጫኑትና የጎሳ ፖለቲካ መሞከሪያ፣ ከዛም ሃያ ሰባት ዓመታት ግፍና ዝርፊያ እየተፈጸመ ሲኖር አሜሪካ ዝምታን የመረጥችው፣ ይልቁኑም ከፍተኛ ሃብትና የስለላ መሳሪያ እያስታጠቀች ትህነግን ስልጣን ላይ ያቆየችውን አሜሪካንን የሚመሩት ዴሞክራቶች ነበሩ። ልክ ዛሬ የትህነግ ደጋፊዎች እንደሚጮሁት ዜጎች ሁለት አስርት ዓመታት ሲጮሁ አይሰሙዋቸውም ነበር። ዛሬ ግን ስልታን በያዙ ማግስት ሰሙ።ከኢትዮጵያ ቆዳ የተገፈፈው ሃብት እየተረጨ …

በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ጊዜ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲካሄድ እንዳልሰሙ፣ እንዳላዩ ሆነው የህዝብ ጩኸትና ለቅሶ ላይ ተኝተው ትህነግን ሲያግዙ የነበሩት የዛሬዎቹ ባለስልጣናት ዴሞክራቶች ናቸው። ዴሞክራቶች በታሪክ ቢዘረዘር ኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተና የተዛባ አቋም በመያዝ ይታወቃሉ። ዛሬም በሪፐብሊካን ዘመን ፊት የተነሱትን ትህነጎች ከመቃብር አውጥተው ሊያነግሱ እየሰሩ ነው። ማንገስ ብቻ ሳይሆን ለምን ተከላከላችሁ በሚል በጅምላ ትህነግን ውስጡ ሆነው የመነገሉትን ሃይሎች ሊበሏቸው ዓለምን ከዳር እስከዳር እያስተባበሩ ነው። አገር ወዳድ መሪዎችን የሚጠየፉትና ቶሎ የሚያስወግዱት አውሬዎቹ ዛሬም ልክ ግብጽ ላይ ሙርሲን እንዳደረጉት ተንበርካኪ አምሯቸው ይሆን? የምናየው ይሆናል።

“አማራ ከትግራይ ክልል ይውጣ” ሲሉ ምን ማለት እንደሆነ የማይገባው ዜጋ ዛሬ እርስ በርሱ ይባላል። በዩቲዩብ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች እየተነዳ ዳግም ለሃፍረት ራሱን ያዘጋጃል። በትንሽ ድል ፉከራና ቀረርቶ ሲበዛ አማራ ላይ ክልል ተቆልፎበት የተፈጸመው በደልና ግፍ ምርቃት ሆነ። በጥቃቅን ልዩነትና በስልጣን ጥማት፣ አንዳንዴም በውክልና የውስጥ ተኩላዎች አጭበርባሪነት ” የትግራይ ህዝብ ሁሉ ትህነግ ነው” እያሉ አማራውን በገሃድ ለሚያፈርሱት ጆሮ በመስጠት መሰራት ያለበትን ተዘነጋ።

የማይካድራውን ግፍ የአማራ ቴሌቪዥን ሲያቦካው ቢውል ለውጩ ማህበረሰብ ዋጋ እንደሌለው እየታወቀ የውጭ ሚዲያዎች እንዲዘግቡት አልተደረገም። ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲደርስ አልሆነም። ወያኔ ተውኔት እየሰራች ዓለምን በገዛቻቸው ሃይሎች አማካይነት ስታስት፣ እውነት ላይ መሰረት ያደረገ ግፍ እጅ ላይ ተይዞ ቀረርቶ፣ ፍትጊያና የስልጣን ጥማት ተመረጠና ሃሰት አሸነፈች። ዛሬ አማራ ከትግራይ ይውጣ ሲባል እንደወትሮ በዩቲዩብ መሰዳደብና መወነጃጀል ወይስ ትግሉን ከፍ አድርጎ፣ ጊዜያዊ ልዩነትን አስወግዶ፣ ጠንካራ ደጀን ፈጥሮ፣ በጉልበትም በዲፕሎማሲውም መጋፈጥ? አለያስ ? ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ትራምፕ ያባረራቸው የሻገቱ የትህነግ ወዳጅ ዲፕሎማቶች ገና ያሳዩናል። ባይደን እየጎተታቸው ያሉት ቅሪተ መለሶች በበሉት መጠን የሚጮሁ ተከፋይ ጋዜጠኞች፣ በብሄራቸው ምች የተመቱ ዘጋቢዎች ተዳምረው …

ኢትዮጵያ የተቀነባበረ ቀውስ እየተደገሰላት ነው። ገና ጦርነት የሚባል ነገር ሳይታሰብ የለውጡን አመራሮች “ሄግ እንገትራቸዋለን” እያሉ ይነገሩን ነበር። ይኸው ዛሬ አምነስቲ ጠየቀ። አሜሪካ ደገመች። ቪኦኤ ትናንት ይህንኑ ሲዘግብ አምነስቲ ያወጣው ሪፖርት በቂ ሆኖ ሳለ ሪፖርቱን እንድያብራሩ ሪፖርቱን የሰሩት የአድዋ ሰው እንግዳ ሆኑ። የአድዋ ሰው፣ አደዋን ጠይቆ፣ ራሱ የፈረደበትን ጥናት ብሄራቸው የበለጠባቸው አጮሁት። ማጮህ ብቻ ሳይሆን ሪፖርቱ፣ የአድዋው ሪፖርት አቀናባሪ ትንተና ያነሰ ይመስል ከዚህ ቀደም የተላለፈ በሚል ለቅሶ ቀረበ። ይህ ሁሉ አላበቃም። ሰላም አስከባሪ 15 የመከለከያ አባላት ኑዛዜ ብቻውን ቀረበ። 35 የትግራይ ልጆች ከ115 ተመላሽ ወታደሮች ጋር ሆነው ወደ አገራቸው መመለሳቸው ለዜና አቅራቢዎች እንስቶች ዜና አልነበረም። ኢትዮጵያ ባበላቻቸውና ባተጣቻቸው፣ ባሳደገቻቸው እየተበለተች ነው። ገና ኦሮሚያን ማፍረስ ይቀጥላል። በዚህ አሳሳቢ ጉዳይ መምከርና አንድ አቋም መያዝ ግድ ነው። አለያ ዳግም ትደቆሳለህ። ባንዳዎቹ ለዳግም ባርነት በየቦታው እያሟሟቁ ነው።

2 thoughts on ““አማራ ከትግራይ ክልል ውጣ” አሜሪካ ግን “ግፍ” ታውቃለች? ጋምቤላ፣ ማይካድራ፣ ራያ፣ በደኖ፣ሆራ፣ዋተር …ምን ተደርጓል?”
  1. Correction
    1991 ( 1983 E.C) George H Bush was the President and he is a rebulic
    an and Herman Choen is a life Time Republican

    1. ስለ ጥቆማው አመሰግናለሁ። በጥቅሉ አማካይ መረጃ ለማሳየት ነበር የታሰበው። ቢሆንም ግን ለማስተካከል ሞክሬያለሁ

Leave a Reply