በለጠ ሞላ የአብን ሊቀመንበር


የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ሊቀመንበር በለጠ ሞላ በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ዙሪያ ከፍትኅ መጽሔት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለእናንተ በሚመጥን መልኩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ!

ፍትሕ፡ አብን የፊታችን ግንቦት የሚደረገውን አገር አቀፍ ምርጫ በተመለከተ ያደረገው ግምገማ፣ ትንተና እና በአጠቃላይ የደረሰበት አቋም ምን ይመስላል?

አቶ በለጠ፡ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ውስጥ ያለች አገር መሆኗ የሚካድ አይደለም፡፡ ሰዎች በማንነታቸው ብቻ ከተለያዩ ክልሎች ተገፍተውና ተፈናቅለው ድንኳን ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ በየጎዳናው የወደቁም አሉ፡፡ ትግራይ ውደስጥ የሕግ ማስከበሩ ሥራ ገና መቋጫ አላገኘም፡፡ የአገራችን ሉዓላዊነትና ዳር-ድንበር በሱዳን ተደፍሯል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በወለጋ የታጣቂዎችን እንቅስቃሴ እና በቤኒሻንጉል መተከል ዞንን ጨምሮ፤ በኢትዮጵያ ሰፊ ቦታዎች ዜጎች ላይ የሕይወት አደጋ የጋረጡ፣ የመኖር ሕልውናቸውን የፈተኑ አያሌ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ጊዜው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ነፃ ምርጫ ለማካሄድ ምቹ አይደለም ወደሚል መላምት መውሰዳቸው አይቀርም፡፡

የሆነው ሆኖ፣ ይህ መንግስት ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው ካለመሆኑ አኳያ እና ምርጫ ይደረጋል ብሎ ከመዘጋጀቱ አንፃር ሕብረተሰቡ በምርጫው ተሳትፎ ይመራኛል ብሎ ያመነበትን መንግስት መመስረት አለበት፡፡ እኛም የካቲት 14 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ይፋዊ የምርጫ ቅስቀሳዎችን በአደባባይ ትዕይንት ሕዝብ በማካሄድ ላይ እንገኛለን፤ ይህም ጥሩ መነቃቃት ፈጥሯል ብለን እናምናለን፡፡

ፍትሕ፡ የጠራችሁት ሰልፍ ቀዝቃዛ ነበር ይባላል?

አቶ በለጠ፡ በነገራችን ላይ ያዘጋጀነው የወረዳና የክፍለ ከተማ አመራሮቻችንና የተወሰኑ አባሎቻችን የተሳተፉበት ይፋዊ የምርጫ ቅስቀሳ መርኃ ግብር እንጅ የድጋፍ ሰልፍ አልነበረም፡፡ ከዚህ አኳያ ሲመዘን ደማቅ ፕሮግራም ነበር፡፡

ፍትሕ፡ ከአማራ ክልል ውጭ ባሉ አካባቢዎች ያለው ዝግጅታችሁ እና እንቅስቃሴያችሁ ምን መልክ አለው?

አቶ በለጠ፡ በአዲስ አበባ፣ በድሬድዋ፣ በሐረርና በቤኒሻንጉል አካባቢ ጠንካራ የሆነ መዋቅር አለን፡፡ በተለይ በአዲሳ አበባ ከአማራ ክልል የማይተናነስ መዋቅር አለን፡፡ ብዙ የአማራ ተወላጆች በሚኖሩበት የኦሮሚያ ክልልም በርካታ ቦታዎች ላይ ለመወዳደር ብንፈልግም በጸጥታ ችግር ምክንያት የተውናቸው ይበዛሉ፡፡ ለምሳሌ ናዝሬት ላይ ቢሯችን በጥይት ተደብድቦ፣ የሰቀልነው ባነር ተገንጥሎብናል፡፡ ወለንጭቲና አህላ ላይም ተመሳሳይ ችግር ከማጋጠሙም በላይ በአባላቶቻችን ላይም ግልፅ ማስፈራራት እየደረሰባቸው ነው፡፡ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ለሕዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤት ለመወዳደር እጩዎችን ለይተን አስመዝግበናል፡፡ ይህ ኹኔታም በየአካባቢዎቹ ያለውን የአማራ ተወላጅ ችግር በቅርበት ለመፍታት እንዲያስችለን ነው፡፡ የተሻለ ውጤት እናገኛለን ያልንበት ቦታዎች ላይ እጩዎችን መድበናል፡፡

ፍትሕ፡ በርካታ የአማራ ተወላጆች በሚኖሩበት ኦሮሚያ ክልል መወዳደሩ፣ በሁለቱ ብሔሮች መካከል ውጥረት ወይም ግጭት አይፈጥርም ወይ?

አቶ በለጠ፡ ኦሮሚያ ውስጥ አብን ስለተወዳደረ ውጥረትም ግጭትም ሊፈጠር አይችልም፡፡ በርግጥ መንግስታዊ መዋቅሩ ራሱ አጥቂ እና ተጠቂ ብሎ የከፈላቸው ማኅበረሰቦች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ እኛ ለግጭቶች መነሾ የሆኑት ችግሮች ያሉት ሕዝቡ ውስጥ ነው ብለን አናምንም፡፡ «አማራ ጨቋኝ ነው!» የሚል የተሰሳተና የፈጠራ ትርክት በስፋት ተሰራጭቷል፡፡ አማራ፤ ሕወሓት በፈጠረው ክልል ውስጥ በፓራሹት አልገባም፡፡ ለምሳሌ የአሩሲ ኦሮሞ እንዳለ ሁሉ፤ የአርሲ አማራም አለ፡፡ ይህንን የኦሮሚያ መንግስት እንዲያውቅና እንዲገነዘብ እንሰራለን፤ እንጥራለን፡፡ ጊዜ እንደሚፈልግ ደግሞ እናውቀን ከረጅምና ከአጭር ጊዜ አኳያ ሊሰሩ የሚገባቸውን ችግሮች በመለዬት እየሰራን ነው።

ፍትሕ፡ የንቅናቄያችሁ ፕሮግራም ትኩረት የሚያደርገው ዜግነት ወይስ ብሔር ላይ ነው?

አቶ በለጠ፡ እኛ አንዱን ለመምረጥ ይቸግረናል፡፡ ብዙ ጊዜ የብሔር ፖለቲካ ሲባል፣ ሰው የሚያስበው ትሕነግና ኦነግን ነው፡፡ የእኛ ከእንዲህ አይነቱ አወቃቀር በፍፁም ይለያል፡፡ ከ30 ዓመት በኋላ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብሔር ተኮር ነው፡፡ መሪ የሆኑት ተወደደም ተጠላም አንድ ብሔርን ወክለው የቆሙ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በዚህ ሁሉ ትርምስና መገፋፋት አማራው በዜግነት ፖለቲካ ተስፋ ሳይቆርጥ ሲታገል ነበር፡፡ ብዙ መስዋዕትነትም ከፍሏል፡፡ እጅግ በጣም የበዛ በደልም ተፈፅሞበታል፡፡ ከዚህ አንፃር ለዜግነት ፖለቲካ ተስፋ ሳይቆርጥ፤ ነገር ግን በሌሎች በብሔር በተደራጁ ቡድኖች ጉዳት እንዳይደርስበት ወደ ራሱ ተመልሶ፣ አቅሙን ገንብቶና ራን በሚገባ አደራጅቶ መምጣት እንዳለበት አምነን ነው እየሰራን ያለነው።

ፍትሕ፡ ከባልደራስና መኢአድ ጋር አብሮ ለመስራት ያስማማችሁ ምሰረታዊው ጉዳይ ምንድነው?

አቶ በለጠ፡ አብን ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ለመታደግ የሚያስችል የበጎ ኃይሎች ጥምረት መመስረት አለበት ብሎ ያምናል። እኛ ብዝኃነት ባለበት እንደ ኢትዮጵያ አይነት አገር ልዩነትን አጥብቦ በአንድነት ለመስራት ሁሌም ክፍት ነን፡፡ ከኢትዮጵያውያን ወንድም እህቶቻችን ጋር በጋራ ለመስራት እንፈልጋለን፡፡ በፖለቲካው ዓለም የግድ በሁሉም ነገር መስማማት አይጠበቅም፡፡ ለምሳሌ፡ ከባልደራስ ጋር «አዲስ አበባ የሁሉም ከተማ ናት!» በሚለው አቋም እንስማማለን፡፡ ከመኢአድ ጋር ደግሞ ብሔራዊ ፓርቲ ስለሆነ፣ እኛ እንዳንሳተፍ ጫና የደረሰብን አካባቢዎች ላይ የሕዝባችን ድምፅ እንዳይባክን አብሮ መስራቱ ይረዳናል፡፡ ስምምነታችን ግን እስከምን ድረስ እንደሆነና ወደ ምርጫ ስንገባ እንዴት እንደሚሆን እስካሁን አልወሰንም፤ ገና እየተማከርን ነው፡፡ ስለዚህም በግርድፉ ከምናገር ዝርዝር ኹኔታዎችን ጨርሰን ከቋጨናቸው በኋላ፣ ለሕዝብ በዝርዝር የምናሳውቅ ይሆናል፡፡

ፍትሕ፡ ምርጫው ለአገራችን ምንይዞ ይመጣል ብለው ያስባሉ? ተስፋ ወይስ ስጋት?

አቶ በለጠ፡ ምንም ባልተለወጠ ስርዓት ተዓምራ መሻሻልም ሆነ በጣም የተለየ ነገር አንጠብቅም፡፡ ነገር ግን ይህ ምስቅልቅል ማብቃት እነዳለበት እናምናለን፡፡ በአገራችን አሳዳጅና ተሳዳጅ መኖር እንደሌለበት እናምናለን፡፡ የምርጫ ሜዳው ፍትኃዊ ሆኖ ሕዝባችን በነፃነት እስከወሰነ ድረስ እኛ እንደ አብን በሕዝባችን ለመዳኜትና የምርጫውንም ውጤት በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ ነን። አብን በምርጫው የተሸነፈው ውጤቱን በፀጋ ተቀብሎ፤ ለአሸናፊው መልካም እድል ተመኝቶ በቀጣይ ተጠናክሮ ለመምጣት መስራት አለበት ብለን እናምናለን፡፡

ፍትሕ፡ እንደ ፓርቲያችሁ እምነት ስልጣን የያዘው ገዢው ፓርቲ ቢሸነፍ ውጤቱን በፀጋ የሚቀበል ይመስላችኋል?

አቶ በለጠ፡ ሕዝቡ እጣ ፋንታን የሚወስንበትን የራሱን ድምፅ እንዲጠብቅ እናነቃለን፡፡ ከየትኛውም በኩል የሚመደቡ የምርጫ ታዛቢዎችም፣ የሕዝብን ድምፅ ማስከበር እንዳለባቸው እናስተምራለን፡፡ ሆኖም የብልፅግና መንግስት የሕዝቡን ውሳኔ ላለመቀበል ካንገራገረና የአሁን ቀደሙ እብሪታዊና ኢ-ዲሞክራሲያዊ አካሄድን ለመድገም የሚያስብ አካል ካለ መጨረሻው ከትሕነግ የባሰ መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን።

ፍትሕ፡ በእናንተ ግምገማ የምርጫ ቦርድ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ በለጠ፡ ምርጫ ቦርድ እንደ ተቋምና እንደ ግለሰብ ይለያያሉ፡፡ ቦርዱ በአንዳንድ ስራዎቹ ለመንግስት ሲመች እያየነው ስለሆነ፣ አሁንም ችግር አለ፡፡ የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ እናም እርሳቸው ላይ የደረሰው በሌሎች ላይ እንዲደገም አይፈልጉም ብለን እናምናለን፡፡ እርሳቸው ስለሚመሩት ወደፊት የሚቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ እኛም ግብዓት እየሰጠን እንደሚያስተካክሉት እናምናለን፡፡ አብን ምርጫ ቦርድ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ መሆኑን ተረድቶ በቀጣዩ ምርጫ የሚኖረው ሚና ነገ በታሪክ ፊት ሲቆም ድንክ የማያደርገው ሥራ ይሰራል ብለን እናምናለን፤ ተግባሩን አብረን የምናየው ይሆናል።

ፍትሕ፡ ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።

አቶ በለጠ፡ እኔም ስለሰጣችሁኝ እድል ከልብ አመሰግናለሁ።

Leave a Reply