ኢዜማን ወክለው በአዲስ አበባ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሚወዳደሩት እጩዎች የታወቁ ሲሆን፤ ባልደራስ ከመኢአድና አብን ጋር በምርጫው እርስ በእርስ ላለመፎካከር ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
በዘንድሮ ምርጫ ኢዜማን ወክለው በየወረዳው ለፓርላማ ከሚወዳደሩት 23 እጩዎች መካከል የፓርቲው መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ የፓርቲው ም/መሪ አንዷለም አራጌ፣ አቶ ግርማ ሰይፉ፣ የኢኮኖሚ ምሁሩ ፕ/ር በፈቃዱ ደግፌና አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን ተጠቃሽ ናቸው።
ፓርቲውን ወክለው ለፓርላማ የሚወዳደሩ 23 እጩዎች በየወረዳው ሲደላደሉም፣ ምርጫ ወረዳ 1/9 አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን፣ ምርጫ ወረዳ 2/14 አቶ ደረጀ ተክሌ፣ ምርጫ ወረዳ 3 ዶ/ር ጥላሁን ገብረ ሕይወት፣ ምርጫ ወረዳ 4 አቶ ተክሌ በቀለ፣ ምርጫ ወረዳ 5 አቶ አበበ ተሻለ፣ ምርጫ ወረዳ 6 አቶ ግርማ ሰይፉ፣ ምርጫ ወረዳ 7 ወ/ት ናርዶስ ስለሺ፣ ምርጫ ወረዳ 8 ከውሰር ኢድሪስ፣ ምርጫ ወረዳ 10 አቶ ዘላለም ወርቅአገኘሁ፣ ምርጫ ወረዳ 11 አቶ የጁ አልጋው ጀመረ፣ ምርጫ ወረዳ 12/13 አቶ አንዷለም አራጌ፣ ምርጫ ወረዳ 15 ዶ/ር በላይ እጅጉ፣  ምርጫ ወረዳ 16  ዶ/ር አንማው አንተነህ፣ ምርጫ ወረዳ 17 ዶ/ር ዳዊት አባተ፣ ምርጫ ወረዳ 18  አቶ ወንድወሰን ተሾመ፣ ምርጫ ወረዳ 19 አቶ በላይ ደስታ፣ ምርጫ ወረዳ 20  አቶ ባንትይገኝ ደስታ፣ ምርጫ ወረዳ 21/22  አቶ ብርሃኑ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ምርጫ ወረዳ 23  ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ፣ ወረዳ 24 ፕ/ር በፍቃዱ ደግፌ፣ ምርጫ ወረዳ 25 አቶ እንዳልካቸው ፈቃደ፣ ምርጫ ወረዳ 26/27 ዶ/ር መለስ ገብረጊዮርጊስ፣ ምርጫ ወረዳ 28  ዶ/ር ባንትይገኝ ታምራት መሆናቸው ታውቋል።
አዲስ አበባ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ኢዜማ፤ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ካቀረባቸው 138 እጩዎች መካከል ታዋቂው የኢኮኖሚ ተንታኝና የፓን አፍሪካ ንግድ ም/ቤት ፕሬዚዳንት፣ አቶ ክቡር ገና  ተጠቃሽ ናቸው።
አዲስ አበባ ራሷን የቻለች ክልል መሆን አለባት በሚል የሚሟገተውና በእስር ላይ በሚገኘው አቶ እስክንድር ነጋ የሚመራው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በበኩሉ፤ ለአዲስ አበባ ም/ቤት 138 እንዲሁም ለፓርላማ 23 እጩዎች ማዘጋጀቱን ገልጾ፣ዝርዝራቸውን ከሰሞኑ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቋል።
ባልደራስ፤ ከመኢአድና አብን ጋር እርስ በእርስ ባለመፎካከር፣ በአንጻሩ በምርጫው  በትብብር  ለመስራት የፓለቲካ ስምምነት ላይ  መድረሳቸውን  የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት ባልደራስ እጩ ባቀረበባቸው ወረዳዎች የአብንና የመኢአድ ድርሻ ድጋፍ መስጠት ሲሆን፤ ባልደራስ በማይወዳደርባቸውና አብንና መኢአድ በሚወዳደሩባቸው አካባቢዎች ደግሞ ባልደራስ ትብብርና ድጋፍ እንደሚያደርግ ሃላፊው አብራርተዋል፡፡

Leave a Reply