እነ አቶ ጃዋር ከ38 ቀናት በኋላ የረሃብ አድማቸውን አቋርጠዋል


.
በረሃብ አድማ ላይ ለበርካታ ቀናት መቆየታቸው የተነገረው እነ አቶ ጃዋር መሐመድ ከነገ ጀምሮ የረሃብ አድማቸውን ለማቆም መስማማታቸውን ጠበቆቻቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከነገ ጀምሮ የረሃብ አድማውን የሚያቋርጡት በላንድማርክ ሆስፒታል የሚገኙት አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ሐምዛ አዳነ መሆናቸውን ጠበቆቻቸው አቶ ቱሊ ባይሳ እና አቶ ገመቹ ጉተማ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ጠበቃው አቶ ገመቹ ጉተማ እነ አቶ ጃዋር የረሃብ አድማ ማድረግ ከጀመሩ ዛሬ 38ኛ ቀን መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

እነ አቶ ጃዋር መሐመድ የረሃብ አድማውን እያደረጉ ያሉት በፖለቲከኞች ላይ የሚደርሰውን እንግልት እና እስር፣ እነሱን ለመጠየቅና የችሎት ሂደታቸውን ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት በሚመጡ ሰዎች ላይ የሚፈጸም እስር እና ወከባ እንዲቆም ለመጠየቅ መሆኑን ጠበቆቻቸው ይናገራሉ።

እነ አቶ ጃዋር የረሃብ አድማውን ለማቆም የተስማሙት ከጤና ባለሙያዎቻቸው በተሰጣቸው ምክር እና በፖለቲከኞች፣ የአገር ሽማግሌዎች ሽምግልና መሆኑን ጠበቀው አቶ ገመቹ ተናግረዋል።

“ትናንት ከ20 በላይ የአገር ሽማግሌዎች እና ፖለቲከኞች በሆስፒታሉ ተገኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ወደ ሆስፒታሉ እንዲገቡ አልተፈቀደላቸውም ነበር። ዛሬ ዳግም ወደ ሆስፒታሉ በመምጣት ከሽማግሌዎቹ ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ እና ሱፐር ኢንቴንደንት ሁሴን ሸቦ ወደ ሆስፒታሉ ገብተው የረሃብ አድማውን አንዲያቆሙ ተማጽነዋቸዋል” ብለዋል ጠበቃው አቶ ገመቹ።

እነ አቶ ጃዋር ከዚህ ቀደም በፖለቲከኞች እና በሃይማኖት መሪዎች የረሃብ አድማውን እንዲያቆሙ ተጠይቀው ፍቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው ይታወሳል።

እነ አቶ ጃዋር ከነገ ጀምሮ የረሃብ አድማውን ለማቋረጥ የተስማሙት የረሃብ አድማ ማድረግ የጀመሩበት ጥያቄያቸው ምላሸ አግኝቶ ሳይሆን፤ “ሃኪሞቻቸው፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ፖለቲከኞች ባደረጉት ልመና ጫና በርትቶባቸው ነው። እሺታቸውን ለሽማግሌዎች ሰጥተዋል። ከነገ ጀምሮ የረሃብ አድማቸውን ያቆማሉ” ብለዋል አቶ ገመቹ።

ከአራቱ ተከሳሾች በተጨማሪ በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ሥር የሚገኙት የአቶ ጃዋር መሐመድ ጠባቂዎች እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋዜጠኛ መለሰ ድሪብሳ በተለያየ ጊዜ የረሃብ አድማውን ተቀላቅለው የነበረ ቢሆንም የረሃብ አድማውን ቀደም ብለው አቋርጠዋል።

See also  የፀጥታ ስጋት ዝርፊያና ሌብነት በትግራይ “ከጦርነቱ በላይ የከበደን ዘረፋ ሆኗል”

via- bbc

Leave a Reply