የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከካናዳው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርክ ጋርኒው ጋር በስልክ ተወያዩ፡፡

በውይይታቸው ወቅትም ስለትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፥ በክልሉ ለሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦትና ለመገናኛ ብዙሃን ተደራሽነት መሰጠቱን አብራርተዋል፡፡

አያይዘውም መንግስት በትግራይ ክልል ከቀረበው ሰብአዊ ድጋፍ 70 በመቶ መሸፈኑን ጠቅሰው፥ ከዚህ ጋር በተያያዘም እስካሁን ለ3 ነጥብ 8 ሚሊየን ዜጎች ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች ማድረግ መቻሉን አውስተዋል፡፡

በተጨማሪም መንግስት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በክልሉ መልሶ ግንባታ እና በራስ መተማመን ለመገንባት በትብብር የሚያደርጉትን ጥረት እያሳደጉ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በክልሉ አለ ከተባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘም ጉዳዩን ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር የማጣራት ስራ እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ መንግስት የሚፈጸም የሰብአዊ መብት ጥሰትን እንደማይታገስና እጃቸው አለበት የተባሉ አካላትን ለህግ እንደሚያቀርብም ጠቁመዋል፡፡

ከቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ ነጻ፣ ፍትሃዊና ግልጽ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጁ መሆኗን አውስተዋል፡፡ የካናዳው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነው መንግስት የሚያደርገውን ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያግዙ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም የካናዳ መንግስት በትግራይ ክልል የሚደረገውን ሰብአዊ ድጋፍ የሚያግዙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እንደሚመድብም አንስተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ተወያዩ፡፡ ፕሬዚዳንቷ በኬንያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ነው፡፡ በጉብኝታቸውም ከፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡ በተለይም በሃገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነትና በቀጠናው አጠቃላይ ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

source Fana 

Leave a Reply