NEWS

[ በኢትዮጵያ ሦስተኛዋና ብቸኛዋ የሴት ሜጀር ጀነራል ]

መከላከያ ሰራዊት የአገር አለኝታ የህዝብ ደጀን ነው። ይህንን አለኝታነቱንም በተለያዩ አውዶች ላይ በብቃት አሳይቷል ። አገርን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች በመከላከልም የሚያህለው የለም።

ከድሮ ጀምሮ ባለው አመጣጡ በሙያ ስነ ምግባሩ በወታደራዊ ብቃት ሁሌም የተመሰገነና ተልዕኮውን በብቃት በጥቂት ኪሳራ በአጭር ጊዜ የሚፈጽም ነው።

ይህ ሀይላችን የአገሩን ዳር ድንበር ከመጠበቅ አልፎ በጎረቤት አገራት የሚከሰቱ አለመረጋጋቶች እንዲፈቱ ሰላም አስከባሪ በመሆኑ በተደጋጋሚ አኩሪ ተግባርን ፈጽሞም መጥቷል።

አሁን እንኳን በቅርቡ የጁንታው ቡድን በተኛበት የቃጣበትን ጥቃት ተቋቁሞ ያላሰበበትንና ያልተዘጋጀበትን ውጊያ ገጥሞ ያስመዘገበውን ድል ለማሳያነት ማንሳቱ የሰራዊቱን የቁርጥ ቀን ልጅነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

ሜጀር ጄነራል ጥሩዬ አሰፌ መከላከያ ካፈራቸው ጀግኖች መካከል ይመደባሉ። በልጅነታቸው የጀመሩት የትግል ህይወትም ዛሬ ላይ ከፍ ወዳለ ወታደራዊ ማዕረግ አድርሷቸዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሶስተኛዋና ብቸኛዋ የሴት ሜጀር ጀነራልም ናቸው። ሴቶች እድል እንጂ እውቀት አላጡም ይላሉ ሜጀር ጀነራል ጥሩዬ ። በአሁን ወቅት በመከላከያ ሚኒስቴር የሴቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬትን እየመሩ ይገኛሉ። እኛም ከሜጀር ጀነራል ጥሩዬ ጋር ወቅታዊ ሁኔታዎችን፣ የትግል ተሞክሮአቸውን እንዲሁም የሴቶችን ተሳትፎና ጀግንነት ትኩረት በማድረግ ተወያይተናል፤ መልካም ቆይታ።

  • አዲስ ዘመን ፦ ጀነራል የት ተወልደው አደጉ? ከሚለው እንጀምር?

ሜ/ጀነራል ጥሩዬ ፦የተወልድኩት በቀድሞው ክልል ሶስት ዋግ ህምራ ዞን በሰቆጣ ከተማ ነው። ለቤተሰቦቼ ሁለተኛ ልጅ ስሆን ፤ አስተዳደጌም እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ነው ። ቤተሰቦቼ ግን የንግድ ስራን ከግብርና ስራቸው ጋር አጣምረው የሚሰሩ ስለነበሩ እኛን ልጆቻቸውን በጥሩ ሁኔታ ለማሳደግም ከፍተኛ የሆነ ጥረት ያደርጉ ነበር።

በዚህም እድሜያችን ለትምህርት ሲደርስ ወደ ትምህርት ቤት ይልካሉ ። እኔም እድሜዬ ለትምህርት በመድረሱ ወደ ትምህርት ቤት ገባሁ። ምንም እንኳን አካባቢው ላይ ሴት ልጆች ተወልደው ከፍ ሲሉ ከፍም ባይሉ ገና ጽንስ ላይ ሆነው ጀምሮ ልጅህን ለልጄ የሚባል ነገር ቢኖርም አባቴ ግን ይህንን የሚቀበል አልነበረም፤ በነገራችን ላይ ይህንን ባህላዊ ሂደት አባቴ ብቻ ሳይሆን አያቴም አይቀበልም ነበር። ከዚህ የተነሳም እኛም ብቻ ሳንሆን አባቴና ወንድም እህቶቹ ሳይቀሩ ተምረዋል።

እኔም ብሆን ገና ልጅ ሆኜ ለጋብቻ የሚጠይቁ በርካታ ሰዎች ወደቤታችን ቢመጡም አባቴ የራሱ አቋም እንዳለ ሆኖ እኛ ልጆቹ የምንለውንም ከልቡ ይሰማ ስለነበር ለጋብቻ የጠየቁት ሰዎች ሁሉ ሳይሳካላቸው ነው የቀረው።

አባቴ ምንም እንኳን ተምረን ትልቅ ደረጃ እንድንደርስለት ምኞቱ ቢሆንም እኔ በትምህርቱ መግፋት አልቻልኩም፤ ያልቻልኩበት ዋናው ምክንያት ደግሞ አባቴን ጨምሮ ሌሎች ቤተሰቦቻችን በኢህአፓ ውስጥ ይንቀሳቀሱ ስለነበር ወታደራዊው ደርግ ያሳድዳቸዋል ። በወቅቱም በተደጋጋሚ አያቴን ጨምሮ አብዛኛው የአባቴ ቤተሰቦች እስር ቤት ገብተው ተሰቃይተዋል ።

ይህ ሁኔታ ደግሞ ቤተሰቡ የሚሰራውን የንግድ ስራ እየሰራ ከተማ ውስጥ እንዲቀመጥ ስላላስቻለው ገና በልጅነታችን ወደ በረሃ ለመግባት ተገደድን። በረሃ ከገባንም በኋላ ቢሆን ፎቶግራፎቻችን በከተማና በገጠር እየተበተኑ እነዚህን ሰዎች ያገኛችሁ በገመድ አንቃችሁ ስጡን እየተባለ ፍለጋውና ማሳደዱ ሰፊ ነበር።

እኔ ወደ በረሃ ስገባ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ፡፡ ነገር ግን ማቋረጥ ግድ ሆኖብኝ ነበር፤ ጥሩው ነገር ግን በረሃም ሆነን ትንሽ ጊዜ ሲገኝ ትምህርት መማር ስለነበረ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከፍ ከፍ ያሉት ህጻናቱን እያስተማሩ ብቻ ሁሉም በየደረጃው ለመማማርና ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት ይደረግ ነበር፤ ከዚህ የተነሳ በመደበኛነት የምማረውን ትምህርት ላቋርጥ እንጂ ከእውቀት አልወጣሁም ነበር ማለት ይቻላል።

  • አዲስ ዘመን ፦ በረሃ የገባችሁት ለሽሽት ከሆነ ታዲያ እርስዎ እንዴት ወደ ውትድርና ህይወት ለመቀላቀል ቻሉ ?

ሜ/ጀነራል ጥሩዬ ፦ በረሃ የገባነው ለመሸሽም ቢሆን በወቅቱ ግን መላ ቤተሰቡ ኢህዴን (ብአዴን)ን ተቀላቅሎ ነበር ፤ በዛ ምክንያት ደግሞ እነሱን ደግፈን ደርግን ለመጣል ታጋይ ሆንን ። በነገራችን ላይ እዛ በረሃ ህዳር ትምህርት ቤት የሚባል ተቋቁሞ ህጻናት ልጆች እንዲማሩም እድል ተመቻችቶ ነበር፤ እኔ እንደ አጋጣሚ መግባት ስላልፈለኩ አልገባሁም፤ ሌሎቹ ግን ተምረዋል።

ከዛም ትጥቅ ታጠቅን ደርግንም መውጋት ጀመርን ፤ የተወሰኑ እህቶቻችንና ወንድሞቻችንም በረሃው ላይ ተሰዉ፤ በህይወት የተረፍነው ደግሞ በ 1983 ዓም ከድል በኋላ አዲስ አበባ ገባን። በ1987ዓም የአገር መከላከያን ተቀላቀልኩ።

አዲስ ዘመን ፦ ወታደርነትና ሴትነት መቼም አስቸጋሪ ይመስለኛልና በወቅቱ ልጅም ስለነበሩ የመጀመሪያውን የበረሃ ተጋድሎዎትን እንዴት ያስታውሱታል?

ሜ/ጀነራል ጥሩዬ ፦ በእርግጥ በእድሜዬ ትንሽ ስለነበርኩ እግረኛ ሆኜ ሰራዊቱን ያገለገልኩት ለአጭር ጊዜ ነው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ምዕራብ አርማጭሆ (ጎንደር) የሚባል ቦታ ላይ ነው ውጊያ የተካፈልኩት ነገር ግን ያን ያህል ከባድ የሚባል አልነበረም ። ከእግረኛ እንደወጣሁ የኪነት ቡድኑን ተቀላቀልኩ። የቡድኑ ስራ ህዝባዊ ተሳትፎን መቀስቀስና ታጋዩን ማነቃቃት በመሆኑ እኔም የተሰጠኝን ሃላፊነት ስወጣ ቆየሁና ወደሌላ ክፍል ተዘዋወርኩ።

እዚህ ለይ የትጥቅ ትግል ሲባል ውጊያ ብቻ የሚመስለው ብዙ ሰው አለ ፤ ነገር ግን ከውጊያ ውጪ ሰራዊቱን የሚደግፉ የህክምና ስራዎች፣ የህትመት ውጤቶችን የማባዛትና የማሰራጨት፣ ትጥቅ ማዘጋጀት፣ የሬዲዮ መገናኛዎች ብልሽት ሲያጋጥማቸው መጠገንና ሌሎች ተግባራትም ይከናወናሉና እኔም እነዚህን ነገሮች በሚያቀናጀው ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት ውስጥ ጸሀፊ ሆኜ ገባሁ። ከዛ በኋላ ደግሞ ህትመት ራሱን ችሎ ሲቋቋም የብአዴን ህትመት ክፍል ውስጥ መስራትም ጀምሬ ነበር።

አዲስ ዘመን ፦ እርስዎ ወደ በረሃ ገብተው ትጥቅ ትግል ሳይጀምሩ በፊት ግን ሴት ወታደሮች አሉ ብለው ያስቡ ነበር? ከገቡ በኋላስ ተሳትፏቸውን እንዴት አገኙት ?

ሜ/ጀነራል ጥሩዬ ፦ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በረሃ ከመግባታችን በፊት በጣም ህጻናት ሆነን ህወሃቶች ከደርግ ጋር ፍልሚያ እያደረጉ ወደእኛ አገር ይመጡ ነበር፤ በዛን ጊዜ ሴቶች መሳሪያ ይዘው፣ ወታደራዊ ትጥቅን ታጥቀው ሲሄዱ እንደ ተዓምር ነበር የምናያቸው። በጣምም እንደነቅባቸው ነበር። እኛም ወታደር በሆንን የሚል ወኔም ነበረን። በተለይም የእኔ ቤተሰቦች አቅም ያላቸው ብሎም ቤታችንም ሰፊ ስለነበር ብዙ ታጋዮች እንዲሁም አሁን የምታውቋቸው ማዕከላዊ ኮሚቴዎች እንዲሁም እነ ታምራት ላይኔ፣ ተፈራ ዋልዋና ሌሎችም ሌሊት መጥተው ቤት ገብተው ከአጎቶቻችንና ከሌሎችም ቤተሰቦች ጋር ስራዎችን ሰርተው፣ መረጃ ተለዋውጠው ይሄዳሉና ለእኔ ውትድርናና ወታደር አዲስ አልነበረም ።ነገር ግን ውስጤ እነሱን ለመሆን ይመኝ ነበር።

በኋላም በረሃ ከገባን በኋላ ከእግረኛ ተዋጊ እስከ ከፍተኛ አዋጊና አመራር ብሎም በሌሎች ስራዎች ላይ ሁሉ የተሰማሩ በርካታ ሴቶች ነበሩ።


አዲስ ዘመን ፦በወታደራዊ አመራር ውስጥ ሴቶች የተሻሉ ናቸው ሲባል በተደጋጋሚ ይሰማልና ይህ ከምን አንጻር ነው?

ሜ/ጀነራል ጥሩዬ ፦ ሴቶች በግዳጅ ቦታም ይሁን በወታደራዊ ስራዎች የተሻሉ የሆኑበት ዋናው ሚስጥር እስከ ዛሬ አትችሉም ተብለው መቆየታቸው የፈጠረባቸው እልህና በራስ መተማመን ይመስለኛል።

ሴቶች በእኛ አገር እንደሚችሉ እየታወቀ እንኳን አቅማቸውን እንዲያሳዩ እድል ተነፍጓቸው ነው የቆየው ፤ ይህ ደግሞ ገድቧቸው ቆይቷል። ነገር ግን በሆነ ምክንያት እድሉን ሲያገኙ ደግሞ አቅማቸውን ማሳየት ይፈልጋሉ ፣ጥንካሬና ውጤታማነታቸውም ከዚህ የሚነሳ ነው።

“አትችይም” የሚለውን ከተቀበልሽው እንኳን በውትደርና ዓለም ይቅርና በማንኛውም መስክ ላይ ጎልቶ መውጣቱ በጣም ከባድ ነው፤ ነገር ግን እድሉ ከተገኘ መስራትና ማሳየት በጣም አስፈላጊ ነው።

አዲስ ዘመን ፦ አሁን በቅርቡ በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ራሱ በርካታ ሴት ወታደሮች ትልልቅ ጀብዱዎችን ፈጽመው ጎልተው የመታየታቸው ምስጢር ዕድል ማግኘታቸው ብቻ ነው ?

ሜ/ጀነራል ጥሩዬ ፦ ሴቶች የተለየ ተሰጥኦ አላቸው

ብዬ አስባለሁ፤ ይህም ማለት የተሰጣቸውን ሀላፊነት ሰፋ አድርጎ የማየት፣ የማመዛዘን ውጤቱን ቀድመው የመገመት አቅማቸውም የተሻለ ነው። ግብታዊነትም አይታይባቸውም። ይህ ደግሞ ከእልህና እችላለሁ ከሚል ስሜት ጋር የሚያያዝ ነው።

እንዳልሽውም በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ብዙ ሴቶች ትልልቅ ጀብዱዎችን ፈጽመዋል። ከወንዶች በላይ ሆነው በዱር በገደሉ ተዋድቀዋል፣ ትልልቅ የጦር መኮንኖችን ማርከው አሳይተውናል። ይህ ደግሞ የሴቶቹን ብቃትና ጀግንነት ከማንም እንደማያንሱ ማሳያ ነው።

ለምሳሌ ከማህበራዊ ሚዲያው ጀምሮ የግልና የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ሲያሳዩአት የነበረችው ተራ ወታደር ኮሎኔሉን አለቃዋን ማርካ ትጥቁን አስፈትታ በባዶ እግሩ ሌሊቱን ሙሉ ብቻዋን ተጉዛ እንዳስረከበችው አይተናል። ይህ ሰው ለዚህች ተራ ወታደር የተንበረከከው ወዶ እንዳይመስልሽ ፤ ጀግንነቷን፣ ቆራጥነቷን፣ አልታዘዝ ቢል ምን እንደምታደርገው ስለሚያውቅ፣ ስለሚያውቃትም ጭምር ነው። ይህንን እንግዲህ ሴቶች በማንኛውም መስክ ላይ እድሉን ካገኙ አሸንፈው ጎልተው ለመውጣት የሚያስችል የተሰጣቸው ጥበብ እንዳለ ነው።

ውትድርና ቀላል አይደለም። ውጊያ ላይ ሲኮን ደግሞ ሁሉም ነገር በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፤ የሚጠጣ ውሃ የማይገኝበት አጋጣሚ ብዙ ነው፣ ሴቶች ተፈጥሮ የሰጠን ጸጋ አለ፤ ያንን ሁሉ ተቋቁሞ ማለፍ የግድ ነው ። ሌሊትም ቀንም በእግር መጓዝ ፣ ከድንጋይ ጋር መላተም፣ በሾህ መወጋቱ ሁሉ ነገር አለ ፤ ግን ሴቶች ራሳችንን ካላሰነፍን አቅም እንዳለን አሁንም ከዚህ ቀደምም በነበሩ አውዶች በሚገባ የታየ ሀቅ ነው።

አዲስ ዘመን ፦ እርስዎ እንግዲህ ከታዳጊነት እድሜዎ ጀምሮ በውትድርና አለም ነው ያለፉት፤ ያን ጊዜ የነበረው ተጋድሎ የደርግ ስርዓትን ለማስወገድ ነበር፤ በወቅቱ ያንን ማሳካት ተችሏል ፤ አሁን ደግሞ የህግ ማስከበር ጦርነት ወስጥ ገብተን ነበርና እንደው ጦርነቱን እንዴት ተመለከቱት ?

ሜ/ጀነራል ጥሩዬ ፦ ቀደም ሲል የነበረው ዘመቻ ጠላት ተብሎ የተፈረጀውን የደርግ ሰራዊት ለማስወገድ ነበር ፤ ህዝቡም የዴሞክራሲ የእኩልነት ጥያቄን አንስቶም ስለነበር ጦርነቱም የህዝብ ጥያቄ እንዲመለስ ማድረጊያ ነው። በዚህም ህዝቡ ጫፍ እስከ ጫፍ የተሳተፈበት ዓላማ ተብሎ የተያዘ ስትራቴጂክ እቅድ ያለው ጉዞውም ስለነበር ደርግን ለመደምሰስ የተሄደበትና የታወቀ ነበር።

አሁን በትግራይ ክልል ያጋጠመን ትንኮሳና ኋላም የተሄደበት የህግ ማስከበር ዘመቻ ከዛኛው ፍጹም የተለየ ነው፤ ሊነጻጻር የሚችልም አይደለም። ጁንታው ቡድን ያን የሚዘገንን ክህደት የፈጸመው ባሳደጋቸውና በሚመራቸው ልጆቹ ላይ ነው። ራዕይ እያሳየ ፣እያሰለጠነ፣ ማዕረግ እየሰጠ ፣እየኮተኮተ ያሳደገ አለቃ (አባት) ቢሆንም ከአባት በማይጠበቅ ስነ ምግባር ልጆቹን በተኙበት ጨፍጭፏል። ይህንን የሚያደርገው ደግሞ ጠላት እንጂ በተለያዩ መስኮች አብሮ የተሰለፈ ፣የበላ፣ የጠጣ፣ ከጎንህ የነበረ ሰው ሲፈጽመው ከባድ ነው። እኔ የተሰማኝ ለካ ከጠላት ጋር ነው እየኖርን የነበረው የሚል ስሜት ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ሲደረግ የነበረው ቅስቀሳ ከባድ ከመሆኑም በላይ ጀግንነቱ እነሱ ጋር ብቻ ያለ እስኪመስል ድረስ እራሳቸውን ወዳለማወቅ ወስዷቸው ነበር ። ነገር ግን ያ ሁሉ ፉከራና ሽለላ በአጭር ጊዜ በተፈጸመው ግዳጅ ፍጻሜውን ማግኘቱ የሰራዊቱን አትንኩኝ ባይነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ፤ በጣም የሚያስገርም ነው።

አዲስ ዘመን ፦ የመከላከያ ሰራዊቱ ይህንን ጥቃት ክህደት ተቋቁሞ ያስመዘገበውን ውጤትና የተፈጸመውን ጀግንነት እንዴት ይገልጹታል?

ሜ/ጀነራል ጥሩዬ፦ በጣም የሚገርም ነው፤ ውጊያ ዝግጅት ያስፈልገዋል፤ ወደ ውጊያ ሲገባ ማሰብ፣ መዘጋጀት፣ ትጥቅና ስንቅ ማሟላትና ሌሎች በርካታ ነገሮች ያስፈልጋሉ። ሰራዊቱም በስነ- ልቦና መገንባት አለበት፤ በእርግጥ ሰራዊት ይሆናልን አስቦ የሚንቀሳቀሰ በመሆኑ ሁሌም ዝግጁ ነው። ምን ጊዜም ልምምድ ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴውንም ሳያቋርጥ ይሰራል። ይህም ቢሆን ዝግጅት የግድ ነው።

የእኛ ሰራዊት እንግዲህ ሳያስበው ጦርነት አለብኝ ብሎ ምንም ዓይነት የስነ ልቦና ዝግጅት ባለደረገበት ሁኔታ በተኛበት ጥቃት ሲገጥመው ቢደናገጥም ራሱን አቋቁሞና ቆም ብሎ አስቦ ወትሮም ዝግጁ ነበርና ድሉን በአጭር ጊዜ ውጊያ በእጃችን እንድናስገባ አድርጓል። ይህ እንግዲህ የሚያሳየው የተገነባበት የስነ- ልቦና ጥንካሬ ፣ ሰራዊቱ ህዝባዊ መሆኑን እምነቱን ነው።

አዲስ ዘመን ፦ ድሮ በቤተሰቦቾ ቤት በተለይም የጁንታውን ከፍተኛ አመራሮች በቅርበት ያውቋቸዋልና በወቅቱ ደርግን ጥለው ነጻነትን ለማምጣት ካካሄዱት ተጋድሎ ጋር አሁን የፈጸሙትን ተግባር ሲያነጻጽሩት ምን ይሰማዎታል?

ሜ/ጀነራል ጥሩዬ፦ እንግዲህ እነርሱ ጋር ያለው ስሜትም ሆነ ፍላጎት የስልጣን ጥማት ይመስለኛል። የስልጣን ጥማት ባይሆንና ህዝብን ያስቀደመ ቢሆን ኖሮ የገነቡትን ሰራዊት አብሯቸው ብዙ መከራን ያየ ላለፉት በርካታ ዓመታት ክልሉንና አገርን ሲጠብቅ ለነበረ ወታደር ይህንን መሰሉን ክህደት ለመፈጸም መነሳሳቱ አይኖርም ነበር።

ሰራዊት ማለት በየትኛውም አገር ላይ አገር ጠባቂ፣ ለአገሩ ክብርና አንድነት የሚሰዋ፣ አካሉን የሚሰጥ ፣ ደሙን የሚያፈስ ነው ።ይህንን መምታት ማለት ህዝብን አለማክበር፣ ስልጣንን ብቻ መሻት፣ ራስን መውደድና ስግብግብነት እንጂ ሌላ ምንም ሊባል የሚችለው ነገር የለም።

በመሆኑም አግባብ ያልሆነ የስልጣን ጥማት መገለጫውም ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። እነሱ ያልተረዱት ወይም ለመረዳትም ያልፈለጉት ነገር ተሳክቶላቸው እንኳን ስልጣን ቢይዙ ያለ ሰራዊት የትም መድረስ እንደማይችሉ ነው። ሰራዊት የሌላት አገር አገር ሆና መቀጠል የማትችል ከመሆኗም በላይ የከሸፈች ነው የምትሆነው። ከዚህም አንጻር ማየት ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን አልሆነም ፤ ራሳቸውን ማስቀደማቸው የፈጠረባቸውን ውድቀት አብረን እያየን ነው።

አዲስ ዘመን ፦ ለውጡን ተከትሎ ትልቅ የሪፎርም ስራ ከተሰራባቸው ተቋማት መካከል መከላከያ አንዱ ነው፤ ይህ ሪፎርም በተለይም የሴቶችን ተሳትፎ ከማሳደግ አንጻር ምን ለውጥ አመጣ?

ሜ/ጀነራል ጥሩዬ፦ አዎ ሪፎርሙ በመከላከያ ላይ ብዙ ለውጦችን አምጥቷል ። ሴት የመከላከያ ሰራዊት ከከፍተኛ ማዕረግ ጀምሮ ድጋፍ ሰጪ እስከሚባለው ክፍል ድረስ ባሉበት በበለጠ ተግተው አገር የጣለችባቸውን አደራ በተሻለ መልኩ እንዲፈጽሙ ለአገራቸው ዘብ እንዲቆሙ አድርጓቸዋል።

አሁን ላይ ደግሞ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ሰራዊቱን እየተቀላቀሉ በየትኛውም የሰራዊቱ የስራ ክፍል እግረኛ ጦርን ጨምሮ የሴቶች ተሳትፎ ጎልብቷል። በተለይ ሴቶች የጦር መሪዎች ሁሉ እየሆኑና እያዋጉ ይገኛሉ። በመሆኑም ሪፎርሙ በተሻለ ሁኔታ የሴቶች ተሳትፎ እንዲያድግና እንዲጎለብት አቅም ፈጥሯል።

አዲስ ዘመን፦ እርስዎ ለአገራችን ሶስተኛዋ ሴት ሜጀር ጀነራል ኖት፤ ይህ ደግሞ ትልቅ የጦር ሹመት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በስራ አጋጣሚ የገጠሞትና የማይረሱት ሁኔታ ይኖር ይሆን?

ሜ/ጀነራል ጥሩዬ ፦ በተለየ አጋጠመኝ የምለው ነገር የለም። ምክንያቱ ደግሞ ገና በታዳጊነት እድሜዬ በረሃ በመግባቴ በዛም ብዙ ችግሮችን አልፌ እዚህ በመድረሴ ሴት ነኝ፣ አልችልም የሚለው ሃሳብ በራሱ ወደጭንቅላቴ መጥቶ አያውቅም። ከዚህ የተነሳ ደግሞ የትም ቦታ ስንቀሳቀስ እኔ ሴት ነኝ፣ ይህንን ማድረግ አልችልም ብዬ አላውቅም።

ምን ጊዜም እየሰራሁ እያደረኩ እየተማርኩና እያስተማርኩ የመጣሁ በመሆኑ በግሌ የደረሰብኝ ተጽዕኖ የለም።

አዲስ ዘመን፦ ለሴት የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሚያስተላልፉት መልዕክት?

ሜ/ጀነራል ጥሩዬ፦ መከላከያ ሰራዊት በተለይም የአገርን ሉአላዊነት እጠብቃለሁ፣ ለህዝቤ አለኝታና ደጀን እሆናለሁ ብላ ለምትመጣ ሴት ምን ጊዜም ክፍት ነው። ስለዚህ ሴቶች በበለጠ ወደ ሰራዊታችን እንዲቀላቀሉ ጥሪዬን እያቀረብኩ አሁን በሰራዊቱ ውስጥ አባል ሆነው ያሉ ሴቶችም ለበለጠ ሀላፊነትና ግዳጅ ሁሌም ራሳቸውን አዘጋጅተው እንዲጠብቁ እነግራቸዋለሁ።

አዲስ ዘመን የካቲት 29/2013

Categories: NEWS

Tagged as:

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s