የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ በዋስ መፈታታቸው ተሰምቷል። ፖሊስ ለችሎት እንዳስረዳው ወይዘሮዋ የተፈቱት ቀዳሚ ምርመራ እስኪሰማ ድረስ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 28 መሰረት ነው።  

ፋና ችሎቱን ጠቅሶ እንደዘገበው ወይዘሮ ኬሪያ ቀዳሚ ምርመራ እስከሚሰማ ድረስ የሚቆዩት በሰርቪስ ማረፊያ ነው። የህግ ማስከበሩ ሲጀመር ሌሎች ሲሸሹ መቀሌ ሆነው እጃቸውን የሰጡት የቀድሞ አፈ ጉባኤ፤ እጃቸውን ከሰጡ በኋላ ክስ ሳይመሰረትባቸው መቆየቱ ይታወሳል።

ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም እንዴት ወደ መቀሌ ሄዱ?

አፈጉባዔዋ ወደ መቀሌ የሄዱት ከአዲስ አበባ ተገፍተው መሆኑንን ጉዳይን በወጉ ሲከታተሉ የነበሩ ይናገራሉ። ኬሪያ ሃላፊነታቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ከማስታወቃቸው በፊት ከአቶ ጃዋር ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዲመሠርቱ ተደርጎ ነበር።  

ለጃዋር ሳሎን ቅርብ የሆኑ ኬሪያን በተደጋጋሚ እዚሁ ሳሎን እንዳዩዋቸው ምስክርነት ይሰጣሉ። የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ መረጃ የሚቀበላቸው የኦፌኮ ሰዎች እንዳሉት አፈጉባዔዋ ወደ መቀሌ ሊሄዱ ሰሞን በጃዋር ከፍተኛ ግፊት ይደረግባቸው እንደነበር አመራሮቹ ሲናገሩ መስማታቸውን አረጋግጠዋል።

ጃዋር መሀመድ ለምን ጫና ሊፈጥርባቸው እንደቻለ ሲያስረዱ “ወቅቱ የመንግሥት ፍጻሜ በመሆኑ ወ/ሮ ኬሪያ እጅግ ተፈላጊ ሚና መጫወት እንዳለባቸው በትህነግና በእነጃዋር ታምኖበት ነበር” ሲሉ ይጀምራሉ። አክለውም “ኬሪያ ወደ መቀሌ የመሄድ ብዙም ፍላጎት እንደሌላቸው ሲታወቅ ጃዋር መንግሥት እንደሚቀየር በማሳመን ከፓርቲያቸው መለየት እንደሌለባቸው በማስገንዘብ እንዲሄዱ ገፍቷቸዋል” ብለዋል።

“መንግሥት የመንግሥትነቱን ዕድሜ ጨርሷል” የሚለው ቅስቀሳ በትብብርና በቅንጅት ሲጀመር፣ ጎን ለጎን የትህነግ ሰዎችና አፈቀላጤዎች አጠር ባለ ጊዜ መንግሥትን በኃይል ለማስወገድ ማቀዳቸውን በቃል፤ ወታደራዊ ዝግጅቱን በተግባር እያሳዩና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጦርነት ለማስነሳት ዕቅድ መኖሩን በአጋሮቻቸው አማካይነት ያስነግሩ እንደነበር ይታወሳል።

ምርጫ መደረግ እንደሌለበት ሲሰብኩ የነበሩት እነ ልደቱ አያሌው ሳይቀሩ በመናበብ “መንግሥት ከመስከረም 30 በኋላ የለም” የሚለውን ዘመቻ ሲያራግቡ ወ/ሮ ኬሪያ በእነ ጃዋር ግፊትና ትዕዛዝ አስፈጻሚነት ወደ ትግራይ አቅንተው መንግሥትን በገሃድ ተቃወሙ። የህገ መንግሥት ተርጓሚ አካል የሆነውን ትልቁን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣን መልቀቃቸውን ይፋ ሲያደርጉ ጃዋር የሚመራቸው ሚዲያዎች፣ የትህነግ ልሳኖችና በውጭ አገር ያሉ ተከፋይ ሚዲያና ወስዋሾች ዜናውን በስፋት አዳርሰውት ነበር።  

በወቅቱ ወ/ሮ ኬሪያ መቀሌ ተገደው እላፊ መናገራቸው ሲሰማ የትግራይ ቲቪ የመዝናኛ ክፍለጊዜ አዘጋጅቶ ኬሪያ ደስተኛ እንደሆኑ ለማስመለስ ተሞክሮ ነበር። በወቅቱ ጎልጉል በደረሰው መረጃ ግን ኬሪያ ተገደው ትግራይ ከሄዱ በኋላ ደስተኛ አልነበሩም።

በወቅቱ በትህነግ፣ እነጃዋርና ሌሎች ተባባሪዎች አማካይነት መንግሥት በኃይል ሲወገድ የውጭ ማኅበረሰብና መንግሥታትን ቅቡልነት ለማግኘት ወ/ሮ ኪሪያ አስፈላጊና ቁልፍ ሰው በመሆናቸው ነው ወደ ትግራይ እንዲሄዱና እንዲከዱ የተደረጉት የሚሉት የጎልጉል መረጃ ምንጭ፣ ትግራይ ከገቡ በኋላ ህገ መንግሥት እንደተጣሰ፣ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ህጋዊ እንዳልሆነ ጠቅስው መረጃ እንዲያሰራጩ ተደርጓል። ይህ ዓለምን የዞረ መግለጫና መረጃ ከተሰራጨ በኋላ መንግሥት በኃይል ሲቀየር የዓለም አቀፍ ተቋማትንና አገራትን ቅቡልነት ለማስገኘት የሕገመንግሥት ተርጓሚው ምክርቤት አፈጉባዔ የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ ተዘጋጅተው እንደነበር የመረጃው ምንጭ የኦፌኮን ከፍተኛ አመራሮች ጠቅሰው ተናግረዋል።

የታሰበው ሳይሆን ቀርቶ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ወዲያው ትህነግን ከድተው እጅ የሰጡት ኬሪያ እነ ስብሃት ነጋ ታስረው እስኪመጡ ድረስ ክስ ሳይመሰርትባቸው መቆየታቸው ይታወሳል። በዚሁ ቆይታቸው ምን መረጃ እንደሰጡና ለህግ ማስከበሩ ዘመቻ የሚጠቅም ግብዓት እንዳበረከቱ በግልጽ የተቀመጠ መረጃ የለም። ዛሬ በዋስ ከላይ በተቀመጠው መሰረት መፈታታቸውን ተከትሎ አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች ተቃውሞ ሲያሰሙ እየታየ ነው።

ጎልጉል ያነጋገራቸው የመንግሥት ኃላፊ ከላይ በተዘረዘሩት ጉዳዮች ላይ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ጠሰው “ተቃውሞ በመረጃና በጭብጥ ላይ መከራከሪያ በማቅረብ ሲሆን አግባብ ነው፤ ከዚያ ውጭ አንድ ነገር ሲሆን በጥቅል መሳደብ፣ ማውገዝ፣ እኔን ስሙኝ ብሎ መወራጨት ህግን መጣስ ብቻ ሳይሆን ንግግር ከማብዛት የሚመጣ የልብ መደፈን ነው” ሲሉ በሰሙት ለጆሮ የሚቀፍ ስድብ ማዘናቸውን አስታውቀዋል። አግባብነት ያለውና መሰረታዊ መከራከሪያ የሚቀርብበት ትችት አስፈላጊ መሆኑንን ጠቅሰው “አሁን አሁን እላፊ መሳደብና እኔ እኔ … የሚል የትህነግ አይነት አመለካከት መግራት አስፈላጊ እየሆነ ነው” ብለዋል።

አንድ የህግ ባለሙያ “ወ/ሮ ኬሪያ አልተፈቱም። ወይዘሮ ኬሪያ ቀዳሚ ምርመራ እስከሚሰማ ድረስ የሚቆዩት በሰርቪስ ማረፊያ ነው። ውጭ ሆነው ክሳቸውን መከታተላቸው ሃጢያት የለውም። ነጻ አልተባሉም። የቤት ውስጥ እስር አይነት ወይም በረጅም ገመድ ማሰር እንደማለት ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። አያይዘውም “በነጻ ቢለቀቁም መንግሥት ምን ያገባዋል? ጣልቃ ገብነት ይቁም እየተባለ እንደገና በፍርድ ቤት ሥራ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ መጋበዝ አያስኬድም፣ ወይስ ጣልቃ ገብነቱን የምንቃወመው እኛ “ንጹህ ነው” ባልነው ሰው ላይ ሲፍጸም ብቻ ነው” ብለዋል።

በዛሬው ችሎት የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት ወይዘሮ ሕርቲ ምህረተአብ እና የክልሉ መንግሥት አማካሪ የነበሩት ወልደጊዮርጊስ ደስታ፣ እንዲሁም በእነ አባይ ወልዱ የክስ መዝገብ ላይ ከሚገኙ ተከሳሾች ውስጥ አምደማርያም ተፈራ በ30 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ መወሰኑ ተሰምቷል

Via – በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply