የጸጥታው ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ጎን እንዲቆም ተጠየቀ

ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በኒውዮርክ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል ። ሰልፈኞቹ የጸጥታው ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ጎን እንዲቆም በደብዳቤ ጠይቀዋል።

የሰልፉ አስተባባሪዎች በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ ሰልፉ ቀደም ባሉት ቀናት የተካሄዱ ተመሳሳይ ሰልፎች አካል ነው ። ዋና አላማውም አሁናዊ በሆነው የኢትዮጵያ ጉዳይ የጸጥታ ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ጎን እንዲቆም የሚጠይቅ ነው ።

ሰልፈኞቹ በእለቱ የጸጥታው ምክር ቤት የወሩ ፕሬዚዳንት ለሆኑት የአሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት ቀሚ መልዕክተኛ አምበሳደር ግሪን ፊልድ ባስገቡት ደብዳቤ÷ የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ገንቢ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጠይቀዋል ።

ሰልፈኞቹ በደብዳቤያቸው ሀገሪቱት ላለፉት ሦስት ዓመታት በህወሓት ቡድን ከፍ ያሉ የሰላምና መረጋጋት አደጋዎች ውስጥ ገብታ እንደነበር አስታውቀዋል ።ቡድኑ በኢትዮጵያ ህዝብ የተሰጡትን የሰላምና እርቅ እድሎች በማምከን ሀገሪቱም ወደ ግጭት መክተቱን አመልክተዋል። በዚህም ሀገሪቱንና ህዝቦቹን ያልተገባ ዋጋ ማስከፈሉን ገልጸዋል ።

ቡድኑ በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከፍ ያሉ ወንጀሎችን መፈጸሙን በመግለጽም፣ ቡድኑ የአገርን ሉዓላዊነት አደጋ ውስጥ በከተተበት ወቅት መንግሥት እንደመንግሥት ሊወስድ የሚጠበቅበትን እርምጃ መውሰዱን በደብዳቤያቸው አመልክተዋል።

ቡድኑ የመንግሥትን ህጋዊ እርምጃዎች በተሳሳቱ መረጃዎች በማጠልሸት ውስጥ እንደሚገኝ ፣ በዚህም ዓለም አቀፉን ህብረተሰብ ለማደናገር ሰፊ ዘመቻ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ህዝብ ከብዙ ትግል በኋላ ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት ማግኘት መቻሉን በደብዳቤያቸው የዘረዘሩት ሰልፈኞቹ ፣ ምክር ቤቱ ይህንን ተጨባጭ እውነታ በአግባቡ እንዲረዳው ጠይቋል። ከህግ ማስከበር ዘመቻው ማግስት ጀምሮ መንግሥት ኃላፊነት በሚሰማው መልኩ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም አመልክተዋል ።

ምክር ቤቱ በሀገሪቱ ከህግ ማስከበር ዘመቻው በፊት ሆነ ከዘመቻው በኋላ ያለውን ተጨባጭ አገራዊ እውነታ በአግባቡ በመረዳት ከኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግሥት ጎን በመቆም ገንቢ አስተዋጽኦ እንዲያበረክትም ጠይቀዋል።

አዲስ ዘመን መጋቢት 3 ቀን 2013 ዓ.ም

See also  "የመንግስትና ኦነግ ድርድር በሰላም የድል ዜና ለሕዝብ ይፋ ይሆናል"

Leave a Reply