የጃዋር ቅዠትና የበቀለ የተላላኪነት ፖለቲካ – የለማ ሃዲድ መሳት

አቶ በቀለ ገርባ ከእስር ተፈተው አሜሪካ እስከገቡ፣ ከአሜሪካም ሜኖሶታ ከጃዋር ጋር ጫጉል ቆይተው እስኪወጡ የሚናገሩትንና የሚያደርጉትን የሚያውቁ፣ የሚያመልኩትን አምላክ ተግሳጽ መስማት የሚችሉ፣ በዙሪያቸውም ሆነ በሩቅ ባሉ ክብር ያላቸው ፖለቲከኛ እንደነበሩ ስምምነት አለ።

ይህ ስምምነት ነበር አቶ በቀለን በኢትዮጵያ ለውጥ ቢፈጠር ሁሉንም አቻችለው ወደ በጎ መንገድ እንዲመሩ ከሚታሰቡት መካከል ቀዳሚው አድርጓቸው የነበረው። የዲሲ ነዋሪው ገመቹ በቀለ ከሜኖሶታ “ተሃድሶ” ይለዋል ተመርቀው ሲወጡ “የአንጎል ቀዶ ጥገና ተድርጎላቸዋል” ባይ ነው።

የዘወትር የጎልጉል አስተያየት ሰጪ ገመቹ እንዳብራራው አቶ በቀለ ጃዋር በዝግ ቤት ከሰው ለይቶ ቀዶ ጥገና ካደረጋቸው በኋላ ሙሉ በሙሉ ሌላ የማይታወቁ ሰው ሆኑ። “በቀለ ይፈታ” እያሉ ሲጮሁ የነበሩ ወገኖችን ከነ ባንዲራቸው ገፍትረው “አላውቃችሁም፣ ዞር በሉ” ሲሉ የፖለቲካ ሞት ሞተዋል። ወይም በፖለቲካ የሞት መቃብር አፋፍ ላይ ቆሙ።

የበቀለ ገርባና የጃዋር ወዳጅነት – የሸዋ ፖለቲካን መግዛት

በአብዛኛው የቄሮ ትግል ተዋናያንና መሪዎች የማዕከላዊ ኦሮሚያ ልጆች ናቸው። የሜጫና ቱለማ ትግል ሸዋ ተወልዶ በጋመ ጊዜ ወደ ወለጋ ተወስዶ ሲርመጠመጥ ከአርባ ዓመት በላይ በመቆየቱ የሚበሳጩ፣ የቄሮ ትግል ማዕከላዊ ኦሮሚያ ላይ ሲተከል “ትግሉ ወደ ትክክለኛ ሰፈሩ ተመለሰ” በሚል አስተያየት የሚሰጡ ጥቂት አልነበሩም። የተባለው አልቀረም ትግሉ ከሌሎች ጋር ተጋምዶ በድል አበቃ።

ጃዋር ትግሉን በሚዲያ እንዲያስተባበር በቅጥር የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክን ሲመራ ጎን ለጎን ኔት ወርኩን የግል አደረገ። ይህ የሆነው ለውጡ የማይቀር ስለሆነ ወደ ስልጣን ለማኮብኮብ መሠረቱን ለመጣል ነበር። የትህነግ መወገድ እውነት እየሆነ ሲሄድ ጃዋር በሚዲያ ያወጀውን ንግሥናውን ተግባራዊ ለማድረግ ሸዋ ላይ መልህቅ መጣል እንዳለበት አመነ። ጉዲና ኃይሉ እንዳለው ለጃዋር የጥድፊያ ዕቅድ በቀለ ገርባ የተመቹ ሰው ሆነው ተገኙ።

“የመረራን ፓርቲ የተቀላቀልኩት የሸዋን ድምጽ ለመሰብሰብ ነው”

በሜኖስታ ጃዋር መኖሪያ ቤት ጃዋር በቀለ ገርባን ብቻ ሳይሆን ፓርቲያቸው ኦፌኮንም ተጣባው። የኦፌኮ መሪ ዶ/ር መረራ ላይ በድብቅ ሤራ ተገምዶ ኦፌኮን የመግዛቱ ሩጫ ተጀመረ። በቀለ ገርባ ይህንን አደራ ይዘው አገር ቤት ገቡ። ጃዋርም በከፍተኛ ደረጃና ባልተለመደ መልኩ ለመረራ ፓርቲ ሰፊ የአየር ሰዓት ይሰጥ ጀመር። ኦፌኮና መሪዎቹ በኦኤምኤን ቤተኛ ሆኑ።

ጃዋር በአዲስ አበባ  – ሁለት መንግሥት

ትግሉን መረጃ በማደራጀት በሚዲያ እንዲመራ የተቀጠረው ጃዋር በተገኘው አጋጣሚ የቀድሞው ኦህዴድ መዋቅር ውስጥ የመፈንጨት ዕድል አጋጥሞት ስለነበር አዲስ አበባ እንደገባ “ሁለት መንግሥት አለ” የሚል መፈክር ጀመረ።

ወደ ፖለቲካ ሲመጣ “በሜንጫ አንገት እንቆርጣለን” በማለት የሃይማኖት ታፔላ ያነሳው ጃዋር ሸዋ ላይ ልብ የሰጠው ባለመኖሩ በአቶ በቀለ ገርባ አማካይነት ኦፌኮን ጭራውን እየቆላ ገንዘብ አሳይቶ ተቀላቀለ። ፖለቲካ ለምኔ ሲል የነበረው ጃዋር ያልተረጋጋው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ በፈለፈላቸው ሚዲያዎች እንዳሻው መርዝ እየረጨ አገሪቱን አዛላት።

See also  በሕገወጥ የመሬት ወረራ በተሳተፉ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች አካላት ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው

ጎን ለጎን መርራና በቀለን እየያዘ ኦሮሚያን በመዞር የመንግሥትነት ህልሙን ያውጅ ጀመር። በዚህ ዘመቻ ውስጥ ድንገት ከታዩት አቶ ድንቁ ደያስ በቀር ሌሎቹ ሂደቶች የዕቅዱ አካላት ስለነበሩ በኦፌኮ የመካከለኛ አመራሮች ዘንድ ውስጥ ውስጡ ቅሬታ ይሰማ ጀመር።

ድንቁ ደያስና ጃዋር

ቅሬታው ሳይሰፋና ወደ ውጭ ሳይወጣ ጃዋር ኦፌኮን ገዛው። ለድርጅቱ ቅርብ የሆኑ እንደሚሉት አሁን በቀለና ጃዋር መታሰራቸው እንጂ ቅሬታው ይፈነዳ ነበር። የዚህ ቅሬታ ድምርና እነጃዋር እስር ቤት ሆነው መንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር በሚል ድርጅቱ ምርጫ መወዳደር እንዳይችል መደረጉ ቅር ያሰኛቸው “መረራ ዛሬ ላይ አምቦ እንኳን መመረጥ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል” እያሉ ነው።

ጃዋር ኦፌኮን ከገዛው በኋላ በኦፌኮ ታሪክ ተሰምቶ የማያውቁ የፖለቲካ ጨዋታዎች ተጀመሩ። ” የዲቃላ ፖለቲካ” ሚስትና ባልን፣ ቤተሰብን እንዲያፈርስ የሚያዝ ሆኖ መጣ። ይህ ሲባልና መድረክ ላይ ሲቀነቀን መረራ፣ ጃዋርና በቀለ ገርባ ሲስቁና በኩራት የትግሉ መሪ መሆናቸውን በሚያሳይ የእብለት ኩራት ውስጥ መሆናቸውን በሚያጋልጥ ገጽታ በቲቪ ይታዩ ጀመር።

የ”ዲቃላ” ጨዋታው ጠንክሮ ብሄር እየተጠቀሰ “አትግዛ፣ አትሽጥ፣ አታናግር፣ አትመልስ…” በሚል በቀለ ቀለም ቀቢ ሆኑ። ይህኔ ኦፌኮ የፖለቲካ ሞት ሞተ። አቶ በቀለም ቆመውበት ከነበረው የፖለቲካ ሞት ጫፍ ተንሸራተው አሁን ያሉበት ቦታ እንደገቡ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች ያምናሉ። እርሳቸውም ቢሆን ጸጸት እንደጀመራቸው እየተሰማ ነው። አስከሬን አግቶ ስልጣን ለመያዝ እስከመገዳደል መድረስ ከሃይማኖተኛው በቀለ ከቶውንም የሚጠበቅ ባይሆንም ከእነ ቤተሰባቸው አደረጉት። ጃዋር የትኛውን የልቦናቸውን ብሎን ፈቶ እንደጣለው ባይታወቅም በቀለ እንዲህ መሆናቸው በርካታ የሚያውቋቸውን ሰዎች ዛሬ ድረስ የገሃድ ታሪክ መስሎ አይታያቸውም። በተለይ ከእምነት መሠረታቸው አንጻር ሲታይ ጉዳዩን ዝቅጠቱ የበለጠ ያጎላዋል።

ለማ መገርሳና በቀለ

ለማ መገርሳና በቀለ ገርባ ወዳጅ እንዲሆኑ ሲደረግ ሆን ተብሎ እንደነበር ስለ ጉዳዩ የሚያውቁ ይናገራሉ። የአንድ አካባቢ ሰዎች እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሁለቱ ፖለቲከኞች በተፈጠረው አጋጣሚ ለመግባባት ጊዜ አልወሰዱም።

አቶ በቀለ ጃዋር ባስቀመጠው ሥሌት መሰረት ለማ መገርሳን ከኦህዴድ ለመለየትና አዲስ በሚቋቋም የኦሮሞዎች ድርጅት ውስጥ መሪ እንዲሆኑ አስማሙ። ብልጽግና የሚባል ፓርቲ እንዳይቋቋም አቋም እንዲይዙና ቢቻላቸው ኦህዴድ ውስጥ ይህን አካሄድ የሚቃወሙ ኃይሎች እንዲበረክቱ የቤት ሥራ እንዲሰሩ ሆኑ። ለሳቸው ይህ የቤት ስራ እየተሰራ በጃዋር ሚዲያዎች “ሚስጢር” ወይም “ሰበር ዜና” እየተባለ የኦህዴድ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ውጤቶች ዜና እንዲሆኑ ይደረግ ነበር።

አቶ ለማ የውስጥ ለውስጡ ትግል አልሆን ሲላቸው በገሃድ ከወዳጃቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተለዩ። አቶ በቀለ የገፏቸው ለማ ልዩነታቸውን አደባባይ አወጡ። ሚዲያው ዜናውን አራባው። ወቅቱ እነ በቀለ ገርባና ፕ/ር ሕዝቅኤል ገቢሣ መቀሌ እየተመላለሱ ከትህነግ ጋር የሚዶልቱበት በመሆኑ የትግራይ ሚዲያዎች “እረኛውን ግደል፤ በጎቹ ይበተናሉ” ለሚለው ዘመቻቸው ነዳጅ ሆነላቸው። በቀለ ገርባና ባልደረቦቻቸው ኦህዴድ ውስጥ ያለውን ልዩነት ትግራይ ሆነው ይተነትኑ ጀመር። ዛሬ ሁሉም እንደታሰበው ሳይሆን በሌለ ውጤት ለማ አሜሪካ፣ በቀለ ቂሊንጦ ናቸው።

See also  ዕርድታ የተሸከሙ 47 ተሽከርካሪዎች ወደ መቀለ አቀኑ፤ ትህነግ በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች እንዲለቅ ተዘዘ

ድንቁ ደያስ – ጌታቸው አሰፋ – ጃዋር

ለማ መገርሳ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዲለዩ ሲሰራና ድርጅቱን አፍርሰው አዲስ በሚቋቋመው የኦሮሞዎች ድርጅት ውስጥ መሪ ሆነው ብቅ እንደሚሉ ቃል ገብተው ነበር። ኦህዴድን ለማፍረስ የተወጠነው ውጥን ከፈረሰ በኋላ በሚደንቅ መረጃ ግንባር የሆኑት የጃዋር ወዳጅ ድንቁ ደያስ ናቸው።

የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርስቲ ባለቤት አቶ ድንቁ ደያስ ከትህነጉ የደህንነት ማሽን ጌታቸው አሰፋ ጋር በቀጥታ ይገናኝ ነበር። ጉዳዩን በቅርብ ሲከታተሉ የነበሩ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አቶ ድንቁን ጨምሮ በርካታ የክልሉ ባለሃብቶችን ሰብስበው “ውርድ ከራስ ነው” በማለት ከትህነግ ጋር ባይልከሰከሱ እንደሚሻል አሳስበው ነበር። ሥራቸውን አርፈው እንዲሠሩ ከአንዴም ሁለቴ መክረውዋል።

አቶ ድንቁ ጃዋር በ-ጎፈንድሚ-እና በሌሎች ዓይነት ድጋፎች የሚያገኘውን ሃብት በኢትዮጵያ ብር እየቀየሩ በመስጠት፣ እነጃዋር ከትህነግ ጋር በመሆን በአጭር ጊዜ መንግሥት ለመሆን ላወጡት ዕቅድ የሚውል በጀት ከጌታቸው አሰፋ ሲለቀቅ ያንን ለማከፋፈል አቶ ድንቁ ሚና ወስደው ይሰሩ እንደነበር ደኅንነቱ ሙሉ መረጃ እንደደረሰው ሲታወቅ አገር ጥለው ሄዱ።

ድንቁ ደያስ ለዚህ አስተዋጽኦዋቸው የለገደንቢ ወርቅ ማምረቻን እንዲገዙ እንደሚመቻችላቸው “መንግሥት እንሆናለን” የሚሉት እነ ጃዋር ቃል ገብተውላቸው እንድነበር ራሳቸው ለሚቀርቧቸው ወገኖች መናገራቸውን ገልጸዋል። መንግሥት ሳይሆኑ ሃብት ክፍፍልና ሽያጭ ውስጥ የገቡት እነ ጃዋር ድንቁ ደያስ የሚያሰማሯቸው አካላት ዛሬ በጀት ደርቆባቸዋል። እንደሚሰማው ከሆነ መንግሥት የድራማውን ሙሉ መረጃ ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ እየሠራ ነው። ያ እስከሚሆን ድረስ ግን እነ ጃዋር እንዲፈቱ ሽምግልና ለሚመጡ አካላት መንግሥት መረጃውን አሳይቶ ሽማግሌዎቹ ደንግጠው መንግሥትን ይቅርታ ጠይቀው እንደወጡ ተሰምቷል።

ሲጠቃለል …

ጃዋር፣ በቀለ ገርባ፣ ለማ መገርሳና ተባባሪዎች በድንቁ ደያስ የበጀትና የሥልጠና ሎጂስቲክ አቅራቢነት፣ በሚዲያዎች አጃቢነት ዳግም ወደ ቤተመንግሥት ይከንፍ የነበረው የትህነግ ባቡር ተሰበረ። በዚህ ሰንሰለት ውስጥ ከነበሩት የትህንግ ዋና መርዝ አከፋፋዮች ባሉበት መከኑ። የተቀሩት ተማረኩ። ጥቂቶች ወደ ዋሻ አምርተው የዘረፉትን ሃብት በመርጨት 27 ዓመታት ያስራቡትን ህዝብ ለዳግም ፖለቲካ ማገገሚያ አዋሉት።

See also  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ

የትህነግ መጫወቺያ ካርድ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትና በኦሮሞ ህዝብ ደምና አጥንት ላይ ሆነው ዳግም ከትህነግ ጋር አዲስ ፍቅር መሥርተው ሲደንሱ የቆዩት እነ ጃዋርና በቀለ ገርባ ራሳቸውን ወህኒ ከተቱ። ዛሬ በርካቶች እንደሚሉት መረራም ሆነ እስር ቤት ያሉት የኦፌኮ አመራሮች ከትህነግ ጋር የጀመሩት አዲስ ዳንኪራ ከማይወጡት የፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ ከቷቸዋል።

ጃዋር ኦፌኮን በበቀለ ገርባ አሻሻጭነት ከሸመተ በኋላ ኦፌኮ በማይታወቅበት የኦሮሞ ልጆችን በሚከፋፍል፣ ዲቃላ እያለ ደረጃ በሚመድብ፣ ከዚያም በላይ ኦሮሞን በምድር ላይ ባለ ሁሉም ዓይነት የግፍ መርዝ ዘፍዝፎ ሲያሰቃይ ከነበረው የትህነግ ጭራቅ አመራር ጋር ዳግም አሸሼ ገዳሜ ማለቱ ኦሮሞዎችን አንገት አስደፍቷል። እነ ጃዋር ብቻቸውን የቀሩትም ለዚሁ ነው። ሌላው ኦሮሞን ያሳፈረው የአርቲስት ሃጫሉን አስከሬን በማገት ሞቱን ሠርግና የስልጣን እርካብ መጨበጫ ለማድረግ የተፈጸመው አጸያፊ ተግባር ነው። ከሞቱና አሟሟቱ በላይ የገዛ ወገኖቹ አስከሬኑንን ክብር ከልከለው መታየታቸው፣ ሞቱን ተከትሎ ባወጁት አዋጅ የደረሰው እልቂትና የንጹሃን ደም ኦሮሞን አስከፍቷል። ይህንን ሁሉ የግፍና የውርደት ቡሉኮ ወደ ምርጫ መምጣትና ማሸነፍ ይቻላል?


ምንጭ ጎልጉል

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።


Leave a Reply