አየርላንድ የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ እንዲወያይና አለም አቀፍ ጫና እንዲደርስባት ሰርታለች – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አየርላንድ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ እንዲወያይ ማድረጓ እና አለም አቀፍ ጫና እንዲደርስባት መስራቷ አስከፍቶናል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በአየርላንድ የሚገኝ አምባሳደሯን ለመመካከር ጠርታለችም ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳምንቱ የተከናወኑ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን ለመገኛኛ ብዙሀን ያብራሩት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ ኢትዮጵያ እና አየርላንድ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ወዳጅነት እንደነበራቸው አስታውሰው፤ ይሁን እንጂ አሁን ላይ አየርላንድ ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ጫና እንዲደርስባት መስራቷ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

በሳምንቱ በሰሜን አሜሪካና አውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ደግፈው መውጣታቸው በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድም ሌላ እይታ እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል፡፡

ሳምንቱ ከ40 ሃገራት የተውጣጡ አምባሳደሮች ወደ ትግራይ እንዲጓዙ መደረጉንና አምባሳደሮቹም በክልሉ የተመለከቱትን ለወከላቸው ሀገር እንደሚያሳውቁ ተገልጿል፡፡

በየመን እስር ቤት ውስጥ በተፈጠረ አመፅና የእሳት አደጋ 43 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ የኢትዮጵያውያን ማንነትን ለማጣራት መንግሥት እየሰራ ይገኛልም ነው የተባለው፡፡
(በመስከረም ቸርነት) (ዋልታ)

Leave a Reply