በስምሪት መስመራቸው አገልግሎት በማይሰጡ ታክሲዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል – የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ

SOCIETY

በተሰጣቸው የስምሪት መስመር የትራንስፖርት አገልግሎት በማይሰጡ ታክሲዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

ዛሬን ጨምሮ ባለፉት ቀናት በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች የታክሲ አገለግሎት ችግር ተስተውሏል።

የትራንስፖርት እጥረቱ የተከሰተው አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች በመደበኛ የስምሪት መስመራቸው ተገኝተው ሥራቸውን ባለማከናወናቸው መሆኑን ከከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አረጋዊ ማሩ የትራንስፖርት እጥረቱን መንስኤና በቀጣይ የሚወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተ ለኢዜአ ባደረጉት የስልክ ገለጻ÷ “የጎላ ውጥረት ውስጥ እንዳይገባ ሲባል ጥፋት ፈጽመው የተገኙ የታክሲ አሽከርካሪዎች በማስጠንቀቂያና በምክር ሲታለፉ ቆይተዋል” ብለዋል።

ይሁን እንጂ የትራንስፖርት እጥረት እንዲከሰት በማድረግ የአገልግሎት መስተጓጎል እንዲፈጠር እያደረጉ በሚገኙ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የትራንስፖርት እጥረት ችግሩን ለማቃለል የሸገር ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶች አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል ብለዋል።

ኅብረተሰቡ መሰል የትራንስፖረት እጥረት ሲከሰት አማራጭ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎቶችን እንዲጠቀምም መክረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የመዲናዋን የትራንስፖርት እጥረት ለማቃለል ከ3 ሺህ በላይ የብዙሃን ትራንስፖርት ሰጪ አውቶቡሶችን በሚቀጥሉት ዓመታት ወደ ሥራ እንደሚያስገባ ነው አቶ አረጋዊ የጠቆሙት።

የትራፊክ ሕግ መተላለፍ ቅጣት ክፍያ በባንክ መሆን፣ የስምሪት ጥያቄዎችና የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች መጥበቅ የተወሰኑ የታክሲ አሽከርካሪዎች ሥራ ለማቆም እንደምክንያት ያቀረቧቸው ሃሳቦች መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በመዲናዋ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት እየተስፋፋ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የክትትልና ቁጥጥር ሥራው መጠናከር ለአሽከርካሪዎች ምቾት እንዳልሰጣቸው ነው የተናገሩት።

አሽከርካሪዎች በማኅበራት በኩል በገቡት የሥራ ውል መሰረት አገልግሎት የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የታክሲ አሽከርካሪዎች በበኩላቸው÷ የተሰጣቸውን ሕዝባዊ ኃላፊነት በማይወጡ አንዳንድ የትራፊክ ተቆጣጣሪ አካላት ያልተገባ ቅጣት እንደሚጣልባቸው ቅሬታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

የሚመለከተው የትራንስፖርት ተቆጣጣሪ ተቋምም የተለየ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የሚደርስባቸውን ያልተገባ የቅጣት ውሳኔ ለይቶ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በማይወጡ የትራንስፖርት ተቆጣጣሪ አካላት ላይ ክትትል በማድረግ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጧል።

Via FBC

Related posts:

“የአዲስ አበባ ህንፃዎች ግራጫ ቀለም ሊቀቡ ነው በሚል የሚናፈሰው መረጃ ከዕውነት የራቀ ነው” ኮሙኒኬሽን ቢሮ
«የግል የትምህርት ተቋማት የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሚታደልባቸው እየሆኑ መጥተዋል»
መንግስት የኑሮ ወድነትን ለማሻሻልና የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ተከታታይ እርምጃ አንደሚወስድ ተገለጸ
ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት መኖር እና የሚያስከትለው ውጤት
በመኪና አደጋ አራት የጤና ባለሙያዎችን ህይወት አለፈ
የሞት ቅጣት የሚያሰጋቸው ጀማል እና ሀሰን
"ሃያ አንዱ ማኅበራዊ ሕግጋት ●●●
የአቅመ ደካሞችን ጣሪያ መድፈንም ያስወግዛል?
በኦሮሚያ ቦረና ዞን - ገበሬዎች ራሳቸው ሞፈር እየጎተቱ እያረሱ ነው
ከደሴ ከተማ ቤተ-እምነቶች እና ህዝባዊ ተቋማት ህብረት የተሰጠ መግለጫ
«በትግራይ መንግሥት እርዳታ በትክክል ለተጠቃሚዎች እንደሚደርስ ይቆጣጠራል»
የአስር ዓመት ልጅን በሽተኛ በማስመሰል በሶስት ሚኒባስ ተደራጅተው ሲለምኑ የነበሩ ተያዙ
ከ33 ሺህ በላይ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ
“ምግቤን ከጓሮዬ”
“ባለፉት 6 ወራት ብቻ 231 ሀሰተኛ የሰነድ ማስረጃዎች ተይዘዋል”

Leave a Reply