ከ24 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የሀገር ሀብት ከምዝበራ መታደጉን ፖሊስ ገለጸ


ባለፉት ስምንት ወራት አንድ ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው ገቢና ወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንና ከ24 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የሀገር ሀብት ከምዝበራ መታደጉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ፡፡

በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ እንዳስታወቁት፣ በተለይ ህገ-ወጥ የኮንትሮባንድ ዝውውርን ለመግታት በተደረገው ጥረት ባለፉት ስምንት ወራት ከአንድ ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው ገቢና ወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን ገልፀዋል፡፡

የከበሩ ማዕድናት፣ቡና፣ሰሊጥና የዱር እንስሳት በህገ ወጥ መንገድ ከሀገራችን እንደሚወጡና በምትካቸው ደግሞ ወደ ሀገራችን የሚገቡት ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች፣ልባሽ ጨርቅ እንዲሁም ምግብና የመሳሰሉት ቁሳቁሶች በተደረገባቸው ቁጥጥር መቀነሳቸውን ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ ገልፀዋል፡፡

የኮንትሮባንድ እቃዎቹ በሀገር ኢኮኖሚና በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ በመሆናቸው ከቁጥጥር አኳያ መጠነ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ በጉምሩክና በታክስ ማጭበርበር ወይም ስወራ ወንጀል ላይ ባደረገው ምርመራ ከ24 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የሀገር ሀብትን ከምዝበራ መታደግ መቻሉን በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴ መናገራቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡ (ኢ ፕ ድ)

See also  የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያልተሟላ ጥሪ አቀረበ

Leave a Reply