ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ


የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡

የክልሉ መንግሥት የፀጥታ ተቋማቱን ሪፎርም በማድረግ ፤ በአዲስ መልክ ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር ከምንጊዜውም በላይ የህዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ የሚችል ብቃት ያለው ኃይል እየገነባም ይገኛል፡፡

ባለፉት ዓመታትም ሆነ በቅርቡ በተደረገው የህግ ማስከበር የህልውና ዘመቻ ላይ የክልላችን የፀጥታ መዋቅር በህዝባችን ላይ የተቃጣውን ጥቃት በመመከት ፣ በማጥቃትና በማክሸፍ አኩሪ ገድል ፈጽሟል፡፡

በዚህም ምክንያት ከምንጊዜውም በላይ ክልላችን የተቃጡበትን ጥቃቶች በአኩሪ ድል መክቶ ህዝባችን በሰላም ተረጋግቶ የሚኖርበትና ሰላማዊ የሆኑ ዜጎች ሁሉ በነጻነት ተንቀሳቅሰው የሚሰሩበት ሰላማዊ ክልል እንዲሆን አድርጓል፡፡

በክልላችን ውስጥ አልፎ አልፎ በአንዳንድ እኩያን ተንኳሽነት የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት በህዝባችን ውስጥ ለዘመናት አብሮ በኖረው ሰላማዊ የግጭት መፍቻ ዘዴ እንዲፈቱ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ከወጣቱና ከመንግሥት መዋቅር ጋር በጋራ በመሆን የሚፈታበት ሥርዓትም ያለ ነው፡፡

በመሆኑም በህዝቡ ፣ በአመራሩና በጸጥታ መዋቅሩ ጥምረት የትህነግ ቅሪቶች እንዲሁም የትህነግ ተላላኪ የሆኑ ኦነግ ሸኔና መሰሎቹ በየቦታው የሚፈጥሩትን ትንኮሳዎች ሁሉ በአስተውሎትና በሰከነ የትግል ሥልት እያሸነፍን ህዝባችን የሰላም አየር እየተነፈሰ ከድህነት ለመውጣትና ኑሮውን ለማሻሻል መደበኛ ህይወቱ ላይ አተኩሮ የሚሰራበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡

የአሁኑ ግጭት በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጅሌ ጥሙጋ እና በሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ አካባቢዎች የተፈጠረ ሲሆን ሐሙስ መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ጅሌ ጥሙጋ ላይ በግለሰቦች መካከል በተፈጠረ ጠብ ምክንያት አንድ ሰው ህይወት ህልፈትን ምክንያት በማድረግ የተቀሰቀሰ ነው፡፡ በግለሰቦች መካከል የነበረውን ግጭትና የደረሰውን ሞት ምክንያት በማድረግም በሀገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች እርቅ ተፈጽሞ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የኦነግ ቡድንና እሱን መሰል ተባባሪ የሆኑ አካላት በሀገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች እርቀ ሰላም ወርዶ መፍትሔ ያገኘውን ክስተት ምክንያት በማድረግ ከዓርብ መጋቢት 10/2013 ዓ.ም. ጀምሮ አርሶ አደር ይይዘዋል ተብሎ በማይጠበቅ ከባድና የቡድን መሣሪያ ጭምር በመታገዝ የተደራጀና ብዛት ያለው የታጠቀ ኃይል በአጎራባቹ የሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ ከተማና አካባቢው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ነውረኛ የሆነ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡

See also  From the very beginning, terrorist TPLF is bandit, murderer group -Lilay Hailemariam Reda

የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሚያ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ህዝቦች ለዘመናት በሰላም የኖሩና እየኖሩ ያሉ መሆኑ እየታወቀ ሀገር በሰላም ውላ እንዳታድር የሚፈልጉት አንዳንድ ተላላኪዎች በንጹሐን ላይ የፈፀሙት ጥቃት በፍጹም ተቀባይነት የሌለው አደገኛና ከባድ ወንጀል ነው፡፡

በዚህ ጥቃት እጅግ ክቡር የሆነው የዜጎች ህይወት ጠፍቷል፡፡ ንብረትም ወድሟል፡፡ ለጠፋው ህይወትና ለደረሰው የንብረት ውድመትም የክልሉ መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልጻል፡፡

ይህ ጥቃት የተፈጸመው የክልላችን የፀጥታ መዋቅር ህግ በማስከበር የህልውና ዘመቻው ላይ ትኩረት እድርጎ እየተንቀሳቀሰ በሚገኝበት ወቅት ላይ ነው። በተለይም ክልላችን ከትግራይ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ተቋርጦ የቀረው የትህነግ ርዝራዥ የተሚተነኩሰውን ግጭት ለመከላከል እቅስቃሴ እያደረገ በሚገኝበት ወቅት ነው።

ይህን ምክንያት በማድረግ በአጣየና አካባቢው ፀረ ኢትዮጵያ እና ሀገር አፍራሽ የሆኑ ኃይሎች ከዚህም ከዚያም ተቀናጅተው የክልላችን ህዝብ እረፍት ለመንሳትና ሀገር ለማተራመስ እያደረጉት ያለ አስነዋሪ ድርጊት መሆኑን የክልሉ መንግሥት በሚገባ ይገነዘባል፡፡

በመሆኑም የክልሉ መንግሥት ይህ ወንጀለኛ ቡድን በንጹሃን ላይ እየፈፀመ ያለውን ጥቃት ለማስቆም ጥቃቱ ከጀመረበት ሰዓት ጀምሮ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን ተጨማሪ የፀጥታ አካላትን ወደ ሥፍራው በማሰማራት ጥቃቱን ለመቆጣጠርና ንጹሐን ዜጎችን ለመታደግ አስፈላጊውን ሁሉ እየሠራ ይገኛል፡፡

በአጣየና በአካባቢው የተፈጸመውን ዝርዝር ጥቃት፣ የደረሰውን ሰብአዊና የንብረት ጉዳት መንግሥት በፍጥነት መረጃውን አጣርቶ ለህዝቡ ይፋ የሚያደርግ ይሆናል፡፡

የክልሉ መንግሥት በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጅሌ ጥሙጋ እና በሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት በንጹሐን ላይ ለደረሰው የህይወት መስዋእትነትና የንብረት ውድመት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በድጋሜ እየገለጸ አጥፊ የወንጀለኞችን ቡድንና በድርጊቱ የተሳተፉት ተባባሪ አካላትን ሁሉ በቁጥጥር ሥር በማዋል ለህግ የሚያቀርብ መሆኑንም ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡

ይህ ጥቃት በተፈጸመበት አካባቢም ሆነ በሌሎች የክልላችን አካባቢዎች የትህነግ ርዝራዦችም ሆኑ የትህነግ ቅሪት ተልእኮ አስፈጻሚና ፈጻሚ የሆኑ ኃይሎች የፈጸሙትንና የሚፈጽሙትን ጥቃት ለመመከት ህዝባችን ከመንግሥት ጎን ሊቆም ይገባል፡፡

እነዚህ ኃይሎች እድሉን ካገኙ ኢትዮጵያን ለማፍረስም ሆነ ለማተራመስ በክልላችንና ከክልላችን ውጭ በሚኖረው ህዝባችን ላይ አሰቃቂ ጥቃቶችን ለመፈጸም እንደማያመነቱ ደጋግመን ተመለክተናል፡፡

See also  በመዲናዋ ከ314 የግል አሰሪና ሰራተኛ ኤጀንሲዎች ባስመዘገቡት አድራሻ የተገኙት 150 ብቻ ናቸው- ጥናት

በተጨማሪም አንዳንድ አፍራሽ ኃይሎች የተፈጠረውን ግጭት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በክልላችን ህዝብ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ግጭቱን ለማባባስ ጥረት ሲያደርጉ ታዝበናል። እነኝህ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የክልሉ መንግሥት በጥብቅ ለማሳሰብ ይወዳል።

ስለሆነም መላው ህዝባችን ከመቸውም ጊዜ በላይ በአንድነት ለሰላማችን በጋራ የምንቆምበት ጊዜ ላይ መሆናችንን ተገንዝቦ በየትኛውም አካባቢ ለፀጥታው ስጋት የሚሆኑ እንቅስቃሴዎች ሲያጋጥመው ለሚመለከተው የመንግሥት አመራርና የፀጥታ መዋቅር መረጃ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
መጋቢት 12 ቀን 2013 ዓ.ም
ባሕር ዳር

1 Comment

  1. ኦነግ የእነ አብይ አህመድን እና የእነ ለማ መገርሳ የመከላከያ ሹሞችን በመጠቀም የአማራ ልዩ ኃይልን ያዛል ያለው ያሳዝዛል በአሁኑ ወቅት። የመከላከያ እና የአማራ ልዩ ኃይል ህወሀት ላይ ማበር ኦነግ ደጋፊ የመከላከያ ሹማምንት መከላከያንም እና የአማራ ልዩ ኃይልን ሰርገው ገብተው እንዲያደናቅፉ እድላቸውን በእጅጉ አስፍቶላቸዋል። መከላከያ እና የአማራ ልዩ ኃይል ውስጣቸውን በቶሎ ካላፀዱ ዕልቂቱ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ይደርሳል። ኦነግ በጣም ከፍተኛ የውትድርና ስልት እና መረጃ ሰብሳቢዎች ምሁር አዋቂዎች አሉት። በደርግ በበቂ ሁኔታ ሠልጥነው የነበሩ እውቀታቸውን እስከ ዛሬ ሶስት አመት ድረስ በኤርትራ አስተምረዋል ለቄሮ ለበታቾቻቸው።

    ወያኔ በእውር ድንብሩ አዲስ አበባን ይዞ መንግስትን ሲቆጣጠር ሁሉንም የደርግ ወታደሮች አለአዋቂ ናቸው ብሎ በትግራይ ተወላጆች ህወሀት የውትድርና ስልት አስተማሪዎች ብቻ መከላከያን በማስቀጠሉ የውትድርና ስልት ዕውቀት የሌላት ሀገር ሆናለች ኢትዮጵያ ፡፡በመቀጠልም ህወሀት ለውይይት የእንግሊዝኛ ቋንቋ እንኳን የማይሰሙትን ህወሀቶች ከአሜሪካኖች እና ከሌሎች ሀገራት የውትድርና ስልት ምሁሮች በእንግሊዝኛ ተማሩ እና ለማስተማር በቁ እያለ የግብር ውጣ የውትድርና ስልት ሥልጠና እና ሰርቲፊኬት እየለቃቀሙ ስለሰነበቱ ለኢትዮጵያ ወታደር ድድብና ሲያስተምሩ እድሜያቸውን ገፍተዋል ። የውሸት ውትድርና ምሁሮች ተመልሰው እነ አብይ አህመድን የውትድርና ስልት አሰለጠንን ሲሉ ለሀያ ሰባት አመታት የከረሙ መሀይሞች ስለሆኑ እነ አብይም ምንም የውትድርና ስልት እውቀት ሳይኖራቸው የኖሩ ስለሆኑ የህወሀት ወታደሮችም ሆኑ የመከላከያ ወታደሮች ኦነግ ከሚያሰማራቸው ቄሮዎች ጋር ሲወዳደሩ በውትድርና ስልት ዕውቀት አተገባበር ያነሱ ናቸው በአሁኑ ወቅት።

    ኦነግ የመሳሪያ እና የገንዘብ እጥረት አለው እንጂ በውትድርና ስልት እውቀት ከህወሀትም እና ከየትኛውም የክልል ልዩ ኃይል ወይም ከመከላከያ በላይ መሆኑ ታምኖበታል።

    ለማ መገርሳም ብዙ ኦነጎችን በመከላከያ በሹመት ስለሰገሰገ ኦነግ መከላከያን ለማሳዘዝ በቅትዋል። መከላከያ ዳግም በትግራይ ጦርነት ሰበብ የአማራ ልዩ ኃይልን ለማዘዝ በቅትዋል። ይህም ማለት ኦነግ ነው የአማራ ልዩ ኃይልን ከቀሚሴ ዙሪያ እንዲለቅ ያሳዘዘው በአሁኑ የአጣዬ ጥቃት ክስተትም እንደ ሌሎችም ተመሳሳይ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሲያስብ መከላከያን ከአከባቢው እንዲለቅ ሲያሳዝዝ እንደከረመ ሁሉ።
    በጎንደር ውስጥ በቅማንት እና በአማራ ነዋሪዎች መሀከል ግጭት እንዲፈጠር ኦነግ አዝዝዋቸው በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አይሻ መሀመድ ሙሳም መከላከያን ያለ ወቅቱ አስወጥተው አማራዎችን እንዳስጨፈጨፉ ተነግርዋል።
    በመላው ኦሮሚያም በተለይም በወለጋም ፣ ደቡብም እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝም መከላከያ ለቀቀ ወይም አይቶ እንደአላየ ሆነ እየተባለ አንዳንዴም መከላከያ እየተባበረ የአማራ ዘር ማጥፋት ሲፋፋም ይኸው ሶስት አመት አለፈው።

Leave a Reply