ጠብታ ማር እና ጠብታ ስብከት

(በእውቀቱ ስዩም)

ሊዎ ቶልስቶይ የሚወዳት አንድ የምስራቃውያን ተረት አለች፤ በጣም አሳጥሬ ሳቀርባት ይህን ትመስላለች’

የሆነ ሰውየ የሆነ ቦታ ሲሄድ አንበሳ አባረረው ፤ ሮጦ ዛፍ ላይ ወጣ ፤ የዛፉ ቅርንጫፍ እባብ ተጠምጥሞበታል፤ ሰውየ ዝቅዝቅ ሲያይ ከዛፉ ስር ሀይቅ ተመለከተ፤አንድ ግብዳ አዞ አፉን ከፍቶ ይጠብቀዋል፤ እዚች ቅርናጫፍ ላይ ተንጠልጥሎ ለማደር ወስኖ እንደገና ዝቅ ብሎ ሲያይ ምድር ላይ የሚርመሰመሱ የዱር አይጦች በጥርሳቸው የዛፉን ስር ይገዘግዙታል፤ ሰውየው በዚህ ሁሉ ጭንቅ መሀል ከዛፉ ጫፍ ላይ ከተሰቀለው ቀፎ ላይ ማር ሲንጠባጠብ አስተዋለ፤ ዛፉ ተገርሶሶ የአዞው አፍ ላይ እስኪጥለው ድረስ የማሩን ጠብታ እየላሰ ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ወሰነ፤

ተረቱን ሲጨመቅ የሚከተለው የተጣራ ሀሳብ ይገኛል;- ህይወት በመከራ ወደ መከራ የሚደረግ ሽግግር ሲሆን የሚጠናቀቀው በሞት ነው፤ በዚህ መሀል ግን የምናጣጥማት ሚጢጢ ደስታ ትኖራለች ፡፡

ግን ተረቱ የሁሉን ህይወት ይገልፃል? የሁሉን አገር ህይወት ይወክላል?

የአሜሪካ ዜግነት ያለሽ የካዛንቺስ ልጅ ነሽ እንበል፤ ባለፈው አመት ኮቪድ አባርሮሽ ቤትሽ ተደበቅሽ ፡፡ መስርያ ቤትሽ ከስራ ቀነሰሽ ፡ ሰርግሽን ሰረዝሽ ፤ በመጎለት ብዛት በስጋ ላይ ስጋ ጨመርሽ ፤ ከእለታት አንድ ቀን ዶክተር ላይ ሄደሽ ስትመረመሪ አዲስ ብራንድ ደምብዛት እንደተገኘብሽ ተነገረሽ ፤ “ አሁን ይሄኑሮ ነው? እያልሽ በምታማርሪበት ጊዜ ፕሬዚንዳንቱ እንዲህ ሲል ትሰሚያለሽ ” ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ያልሰራሽበትን ደመወዝ በኪስሽ፤ ክትባት ደግሞ በክንድሽ አኖራለሁ”

የፕሬዜዳንቱ ቃል በመከራ ዛፍ ላይ የተገኘች ጠብታ ማር መሆኑዋ ነው!

ኢትዮጵያዊ ነህ! ዳር አገር ውስጥ እያረስህ ወይ እየነገድህ ስትኖር ፤ ሌት በደመና ቀን በጨረቃ ገስግሶ መጥተው ቤተሰብህን ይገድሉብሃል፤ ለወሬ ነጋሪ ተርፈህ ወደ አዲሳባ ትመጣለህ፤ የፉርሽካ እንጀራ እየበላህ ፍልጥ እየተፀዳዳህ ትንሽ ትፍገመገማለህ፤ አንድ ቀን ድንጋይ ስትፈልጥ አምሽተህ ወደ ቤትህ ስትመለስ ሶስት ጠብደሎች ይከቡሀል ፤” ወገኖቼ! ሞባይሌን እምትፈልጉ ከሆነ ሳትደበድቡኝ እሰጣችሁዋለሁ” በማለት ትማፀናቸዋለህ ፤ እነሱም ትንሽ ይመካከሩና “ከነጋ አስር ሞባይል ዘርፈናል፤ ግን ከነጋ አንድም ሰው ስላደበድብን የሌለ ደብሮናል! ለዛሬ ስልኩን ምረንህ በስሱ ብንቀጠቅጥህ ምን ይመስልሀል?” ይሉሃል፤ ታክመህ ስትድን ታሪክህን ላንዱ ዩቲውበር ትነግረውና በበሁለት ክፍል አቅርቦ ይሸቅልበታል፤ ፤ እሱ አምሳ ሺህ ብር ሲያገኝበት ላንተ አምሳ ሺህ አስተያየት ያስተርፍልሀል ! የሆኑ ጀለሶች በስምህ ጎፈንድደው በሚያገኙት ገቢ ሬስቶራንት ይከፍቱብታል፤ በመጨረሻ የሰራ አከላትህ ላይ ጋዝ አርከፍክፈህ ራስህን ለማቃጠል ቤኒዝን ማደያ ላይ ትሰለፋለህ ፤ ሰልፉ ቀለል እስኪል የሆነ ካፌ ገብተህ የመጨረሻውን ቡና ስትጠጣ ከቲቪው ላይ እንዲህ የሚል ወፍራም ስብከት ሲወጣ ትሰማለህ:-
” ኢትዮጵያ ባሁኑ ጊዜ የምትገኝበት ሁኔታ ምጥ ላይ እንደተያዘ ሴት ነው! ከምጡ በሁዋላ ደስታ ይሆናል”

See also  "አብይ እንዲኮበልሉ አሜሪካ ጫና ስታደርግ፣ 'አታስቡት ወረራውን እንቀለብሰዋለን' ብለዋቸዋል" - ዛሬ ለስራ ከግንባር ቱርክ ገብተዋል

“ላገኝ ነው በማለት አለቅሁ በሰቀቀን
ሂዶ ሂዶ አለቀ የምጠብቀው ቀን “ ያለው ገበሬ ፥እንዲህ አይነት ነገር ገጥሞት መሆን አለበት

Leave a Reply