የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ ከሱዳን ሕዝብ ፍላጎት በተቃረነ መልኩ ለሶስተኛ ወገን ጥቅም እየሰራ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር


የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ የሱዳንን ሕዝብ ፍላጎት በተቃረነ መልኩ ለሶስተኛ ወገን ጥቅም እየሰራ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለፁ። ቃል አቀባዩ በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብትና በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ወቅታዊ አበይት ክንውኖች ላይ ያተኮረውን ሣምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በፖለቲካ ዲፕሎማሲ መስክ የአፍሪካ ኅብረት የሠላም ጥበቃ ምክር ቤት የቨርቹዋል ውይይት፣ የአሜሪካ መንግስት ሴናተር ክሪስ ኩንስ የኢትዮጵያ ቆይታና ሌሎች ሁነቶችን ለአብነት አንስተዋል።

የአሜሪካው ሴናተር ኩንስ በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና ከሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ሃላፊ ጋር እንደተወያዩ ገልጸዋል።

በውይይታቸውም በሰሜን ኢትዮጵያ በተደረገው የሕግ ማስከበር መነሻና አሁናዊ ሁኔታ፣ የሠብዓዊ መብትና ሠብዓዊ እርዳታ አቅርቦትና በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር እንዲሁም በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ውጤታማ ውይይት ስለማካሄዳቸው ተናግረዋል። በምጣኔ ሃብታዊ ዲፕሎማሲ ረገድም በአሜሪካ፣ በካናዳና በባህሬን ስለተከናወኑ የኢንቨስትመንትና የቢዝነስ ስራዎች አስታውሰዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድርን በተመለከተ የድርድሩ መሪ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበርነት ከደቡብ አፍሪካ ወደ ኮንጎ መዛወሩን ተከትሎ በሂደት ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል። በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ አቋሟን የምትቀያይረው ሱዳን በዋናነት የግድቡ ጥራትና መረጃ መለዋወጥ ላይ ሁለት ጥያቄዎች እንደምታነሳም ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የሕዳሴው ግድብ ጥራቱ በተረጋገጠ መንገድ የተሰራ እንደሆነ ማረጋገጧን፣ በመረጃ መለዋወጥ በኩልም ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል። ይህ ሆኖ እያለ ግን የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ ከሱዳን ሕዝብ ፍላጎት በተቃርኖ መቆሙን ነው ያመለከቱት።

ግድቡ በተለይም በደለል ለሚጥለቀለቀው የሱዳን ሕዝብ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ራሳቸው የሱዳን ባለስልጣናት እንደሚያምኑ ገልጸው፤ ያም ሆኖ አቋማቸውን እንደሚቀያይሩ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

See also  ጠቁሙ 25% ውሰዱ‼

Leave a Reply