በኢትዮጵያ ያለው የኮሮናቫይረስ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ሲል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስጠንቅቋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ እንዳለው በበሽታው የሚያዙ፣ በጽኑ የሚታመሙና ህይወታቸውን የሚያጡ ዜጎች ቁጥር ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል።

በትላንትናው ዕለት ለኮቪድ-19 ምርመራ ናሙና ከሰጡ 7,659 ሰዎች መካከል 1,981 ሰዎች (26%) ኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው ተረጋግጧል፡፡

ይህ ማለት በኢትዮጵያ እያንዳንዱ ሰው በሚያደርገው የዕለት ተለት እንቅስቃሴ ከሚያገኛቸው ሶስት ግለሰቦች አንዱ ኮሮናቫይረስ ሊኖርበት ይችላል፡፡

በትናንትናው ዕለት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አዳዲስ ታማሚዎች ተመዝግበዋል፡፡

ለአብነትም፡-
*በአዲስ አበባ ናሙና ከሰጡ 5‚964 ሰዎች መካከል 1,499ቱ (25%)
*በኦሮሚያ ናሙና ከሰጡ 465 ሰዎች መካከል 199ኙ (42%)
*በድሬዳዋ ናሙና ከሰጡ 96 ሰዎች መካከል 42ቱ (43%)
*በሲዳማ ናሙና ከሰጡ 165 ሰዎች መካከል 112ቱ (67%) ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

በተጨማሪ በኮሮናቫይረስ ተይዘው በፅኑ ሕሙማን ክፍል ከሚገኙ 752 ሰዎች 94ቱ በሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ እየተነፈሱ ያሉ ናቸው፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ኮቪድ-19 ሕክምና ማዕከል ከመጡ ታካሚዎች መካል በተለያየ መጠን ኦክስጅን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር 61 ሆኖ ተመዝግቦ ነበር፡፡

በአሁኑ ሰዓት ወደ ኮቪድ-19 ሕክምና ማዕከል ከሚገቡት 100 ሰዎች 79 የሚሆኑት በተለያየ መጠን ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡

ስለዚህ እያንዳንዱ ግለሰብና ተቋም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የኃላፊነት ስሜት የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ በመተግበር እና በማስተግበር የወረርሽኙን የስርጭት መጠን ለመግታት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥሪ አቅርቧል።

Leave a Reply