ግብጽ በምስራቅ አፍሪካ የውሃ ግጭት እንዲቀሰቀስ እየሰራች መሆኗ ተገለጸ

የወንዙ ውሃ በተለያየ መጠን ከአስሩም ሃገራት የሚመጣ ቢሆንም፣ ግብጽ አሁንም የወንዙ ብቸኛ ባለቤት እንደሆነች በመግለጽ ላይ ናት ያለው ካውንስሉ፣ ሌሎቹ የወንዙ ተጋሪ ሃገራት ምንም አይነት የልማት ስራዎችን እንዳያከናውኑ እንቅፋት ስትፈጥር ቆይታለች ብሏል ድርጅቱ በመግለጫው።

በ1929 እና በ1959 ስምምነቶች የብቸኛ ባለቤትነት መብት ያገኘችው ግብጽ ውሉን ሌሎቹ ሃገራት የውሃ ሃብቱን እንዳይጠቀሙበት የሚያደርግ ማሰሪያ ያደረገች ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ2010 ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ታንዛንያና ርዋንዳ የተፈራረሙትን ስምምነት በበጎ ካለማየቷም በላይ የህልውናዋ ስጋት አድርጋ መቁጠሯ ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ለመውጣት ፍላጎት እንደሌላት ማሳያ ነው ብሎታል።

ኢትዮጵያ ለበርካታ ጊዚያት በወንዙ ላይ የልማት ስራዎችን ለመስራት ባሰበችባቸው ጊዜያት ሁሉ የግብጽ ተቃውሞ እንደነበር ያነሳው ድርጅቱ አንዋር ሳዳት የተባሉት የግብጽ ፕሬዝደንት “በውሃ ጥም ከምንሞት ኢትዮጵያ ሄደን ህይወታችን ብታልፍ እንመርጣለን” በማለት ጦርነት ቀስቃሽ ንግግር ማድረጋቸውንም አስታውሷል።

በከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ያለችው ኢትዮጵያ እጅግ አንገብጋቢ የሃይል እጥረት ያለባት በመሆኑ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን በማጠናቀቅ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እያደረገች መሆኑን ያብራራው ካውንስሉ፣ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ ግብጽ ከነበረችበት የኢኮኖሚ ሁኔታ በመነሳት የአስዋንን ግድብ ልትገነባ ብትችልም የሌሎቹን የአፍሪካ ሃገራት ልማት አጥብቃ መቃወሟ ሁልጊዜም የበላይ ሆኖ የመቆየት ፍላጎት እንዳላት ማሳያ ነው ብሏል።

ግብጽ ያለ ማንም ከልካይ ውሃን በመጠቀም በርሃ ላይ የጥጥ እርሻዎችን በማልማት በአመት እስከ ሰባት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የምታገኝ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም በራሷ መንገድ የምታስበውን ልማት ተግባራዊ የማድረግ መብት እንዳላት ሊዘነጋ አይገባም ብሏል ዘገባው።

በዚህም የዓባይ ወንዝ አሁን ካለው ክፍፍል በተሻለ ሁኔታ ለየሃገራቱ ይከፋፈል ቢባል ግብጽ ውሃን ከሚያባክነው የግብርና ዘዴዋ ወጥታ የግድ መዋቅራዊ ለውጥ እንድታደርግ ያስገድዳታል ብሏል።

ውሃ በሚያባክን መንገድ ግብጽ ትላልቅና አዳዲስ ከተሞች ያሉባቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እያካሄደች መሆኑን ያብራራው ድርጅቱ፣ የውሃ አጠቃቀም ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣና ቁጠባን የሚያስተምር አዲስ አካሄድን ግብጻውያን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚኖርባቸውም መክሯል።

ድርጅቱ አክሎም ከቀድሞ የግብጽ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ሙርሲ እስከ አሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ድረስ ኢትዮጵያ ላይ ሁሉንም አይነት ጫናዎች ለማሳደር የተደረገው ሙከራ እስካሁን ያለመሳካቱን የተገነዘቡት የግብጽ ባለስልጣናት በትግራይ ክልል በተከሰተው አለመረጋጋት ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ ጉዳዩ ይበልጥ ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆን ያለመታከት በመስራት ላይ እንደሆኑ አስነብቧል።

See also  ኤርትራ "ትንኮሳ ሰልችቶኛል" ስትል አስጠነቀቀች

ከዚህ ጋር ተያይዞ የህወሃት ሃይሎች ያሉበትና የሱዳን ወታደራዊ ባለስልጣናት የሚመሩት የሱዳን ጦር በኢትዮጵያ ላይ ያደረገው ወረራ እንዲሁም የሱዳን ባለስልጣናት የሚያደርጓቸውን ተንኳሽ ንግግሮች የግብጽ ጣልቃ ገብነት አንዱ ማሳያ አድርጎ ማቅረቡን ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply